በኩባ "ለማኝ የለም" ያሉት ሚኒስትር በበረታባቸው ጫና ከስልጣን ለቀቁ

ሚኒስትር ማርታ ኢሌና

የፎቶው ባለመብት, X

የምስሉ መግለጫ, ሚኒስትር ማርታ ኢሌና

ኩባ ውስጥ "ለማኝ የለም" ብለው የተናገሩት የአገሪቱ የሠራተኛ ሚኒስትር ማርታ ኢሌና ፌይቶ ካብሬራ በደረሰባቸው ጫና ምክንያት ከሥልጣን ለመልቀቅ መገደዳቸው ተገለጸ።

በኩባ "ለማኝ" የሚባል ነገር የለም ያሉት ሚኒስትሯ በቆሻሻ ገንዳ ማጠራቀሚያዎች የሚታዩ ግለሰቦች በመሠረቱ ይህንን የሚያደርጉት "በቀላሉ ገንዘብ ለማግኘት" በመምረጣቸው ነው ብለዋል።

ሚኒስትሯ ይህንን አስተያየት በፓርላማ ስብሰባ ላይ መስጠታቸውን ተከትሎ በአገር ውስጥ እና በውጭ በሚገኙ ኩባውያን ከፍተኛ ትችት እና ውግዘት ደርሶባቸዋል።

ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሚጌል ዲያዝ ካኔል ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ሚኒስትሯም ወዲያውኑ ከሥልጣናቸው ለቀዋል።

ኩባ ከከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር እየታገለች ከመሆኑ አንጻር የምግብ እጥረት እና ድህነት ተባብሷል።

ሚኒስትሯ ፌይቶ ካብሬራ ትችት ያስከተለባቸውን አስተያየታቸውን የሰጡት በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በነበረ ብሔራዊ ጉባዔ ላይ ነው።

"ኩባ ውስጥ ለማኞች የሉም። በቀላሉ ገንዘብ ለማግኘት የሚሞክሩ እና አስመሳይ ለማኞች ናቸው" ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል።

የሚኒስትሯንም በኩባ ለማኞች የሉም አወዛጋቢ ንግግር ተከትሎ የኩባው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ፔድሮ ሞንሪል በኤክስ ገጻቸው ላይ "በሚኒስትርነት ሸፋን የተቀመጡ ሰዎች አሉ" ሲሉ ተችተዋቸዋል።

ኩባውያን በቆሻሻ ገንዳ አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፌቶ ካብሬራ በቆሻሻ መጣያ ገንዳ ላይ እቃዎችን የሚፈልጉትን "ሕገወጦች" ሲሉ ወርፈዋል።

ሚኒስትሯ አስተያየታቸው ከሕዝቡ ይህንን ያህል ቁጣና ውርጅብኝ የሚያስከትልባቸው ያልመሰላቸው ሲሆን፤ በርካቶችም አስተዳደሩ ኩባውያን እያለፉበት ካለው የኑሮ ትንቅንቅ ጋር የተፋታ፣ የምጣኔ ሃብቱን ቀውስ እውነታ ያልተረዳ የሚሉ ትችቶች እንዲከተሉ ምክንያት ሆነዋል።

በርካታ የኩባ ተሟጋቾች እና ምሁራን ሚኒስትሯ በአስተያየታቸው "የኩባን ሕዝብ ተሳድበዋል" በሚል ከሥልጣን እንዲወርዱ ደብዳቤ ጽፈዋል።

የኩባው ፕሬዚዳንት በፓርላማው ስብሰባ ላይ የሚኒስትሯን ስም ሳይጠቅሱ የተቿቸው ሲሆን፣ የሕዝብን እውነታ ግምት ውስጥ ያላስገባ ብለዋል።

ሚኒስትሯ ያስገቡት የሥራ መልቀቂያ በኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ እንዲሁም በመንግሥት ተቀባይነት አግኝቷል።

የኩባ መንግሥት ከልመና ጋር የተያያዙ አሃዞችን ይፋ ባያደርግም በኢኮኖሚ ቀውስ በምትናጠው ኩባ የሚለምኑ ሰዎች ቁጥር መጨመር ታይቷል።