ድምጽ ለመስጠት የወጡ ኬንያውያን ቁጥር ከተጠበቀው በታች ሆነ

ኬንያውያን ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቷን የሚመራትን ፕሬዝዳንት ለመምረጥ በዛሬው ዕለት ማክሰኞ ነሐሴ 03/2014 ዓ.ም. ወደ ምርጫ ጣቢያዎች አቅንተዋል። አራት ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ለፉክክር ቀርበዋል። ከ22 ሚሊዮን በላይ መራጮች ለተመዘገቡበት ለዚህ ምርጫ ማካሄጃ ደግሞ አገሪቱ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ በጀት መድባለች።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኬንያ የድምጽ መስጫ የምርጫ ጣቢያዎች ተዘጉ

    ኬንያዊ ምርጫ

    ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 03/2014 ዓ.ም. ማለዳ ጀምሮ ሲካሄድ የዋለው የኬንያ ብሐራዊ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ተጠናቀቀ።

    የኬንያ ገለልተኛ የምርጫ እና የድንበር ኮሚሽን ድምጽ የሚሰጠው ከንጋት 12 ሰዓት ላይ እስከ አመሻሽ 11 ሰዓት ነው ማለቱን ተከትሎ አዲስ ወደ ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የሚሄዱ ድምጽ ሰጪዎች አይስተናግዱም ተብሏል።

    ይሁን እንጂ ድምጽ ለመስጠት ተሰልፈው የሚገኙ መራጮች ድምጻቸውን መስጠት ይችላሉ።

    እስካሁን ድረስ ድምጻቸውን ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የሄዱ ኬንያውያን መራጮች ቁጥር ከተጠበቀው በታች መሆኑ ቀደም ሲል ተዘግቧል።

    የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን እስከ እኩለ ቀን ድረስ ከተመዘገቡ መራጮች ድምጻቸውን የሰጡት 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነው ብሎ ነበር።

    ለአምስተኛው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 22 ሚሊዮን ኬንያውያን ድምጻቸውን ለመስጠት የተመዘገቡ ቢሆንም፣ እስከ እኩለ ቀን ድረስ 6.2 ሚሊዮን የሚሆኑት ብቻ ድምጽ ሰጥተዋል።

  2. የኬንያን ምርጫ እየታዘቡ ያሉ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች

    ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች

    የፎቶው ባለመብት, IGAD, WILIYAAM RUUTOO, Prof Merera

    ኬንያ እያካሄደች ያለችውን አምስተኛውን ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመታዘብ ሦስት ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ተገኝተዋል።

    የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የቀድሞ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እና ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የኬንያን 2022 ምርጫ ለመታዘብ ተገኝተዋል።

    አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገውን 'ብሬንትረስት ፋውንዴሽን'ን በመወከል ምርጫውን እየታዘቡ ናቸው።

    አቶ ኃይለማርያም በሚመሩት ልዑክ ውስጥ እውቁ ኡጋንዳዊ ፖለቲከኛ እና ሙዚቀኛ ቦቢ ዋይን ይገኝበታል።

    የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ታዛቢ ቡድንን በመምራት ኬንያ ናቸው።

    ኢጋዳ 10 ወደሚጠጉ የኬንያ ግዛቶች የምርጫ ታዛቢዎቹን አሰማርቶ የምርጫውን ሂደት እየተከታተለ ነው።

    የተቃዋሚው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ መሪ እና አንጋፋው ፖለቲካኛ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናም እንዲሁ የኬንያን ምርጫ በመታዘብ ላይ ናቸው።

    ፕሮፌሰር መረራ በኬንያዋ የወደብ ከተማ ሞምባሳ ተገኝተው የምርጫውን ሂደት እየታዘቡ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

  3. ከአገር ውጭ ያሉ ኬንያውያን ድምጽ እየሰጡ ነው

    ኬንያውያን በለንደን በሚገኘው የኬንያ ከፍተኛ ኮሚሽን ተገኝተው ድምጽ እየሰጡ ነው
    የምስሉ መግለጫ, ኬንያውያን በለንደን በሚገኘው የኬንያ ከፍተኛ ኮሚሽን ተገኝተው ድምጽ እየሰጡ ነው

    ከአገር ውጭ ያሉ ኬንያውያን አገሪቱን የሚመራውን አምስተኛውን ፕሬዝዳንት እየመረጡ ነው።

    የኬንያ ገለልተኛ የምርጫ እና ደንበር ኮሚሽን በ12 አገራት የሚገኙ ዳይስፖራ ኬንያውያን ለምርጫው ድምጻቸውን ይሰጣሉ ብሏል።

    ከእነዚህ መካከል ስድስቱ የአፍሪካ አገራት ናቸው።

    ኬንያውያኑ ድምጽ እየሰጡ ያሉባቸው አገራት ቡሩንዲ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ አሜሪካ፣ ኳታር እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ናቸው።

  4. ድምጽ ለመስጠት የወጡ ኬንያውያን ቁጥር ከተጠበቀው በታች ሆነ

    መራጮች

    በኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እስካሁን ድምጻቸውን የሰጡት መራጮች ቁጥር ከተጠበቀው በታች ነው ተባለ።

    የኬንያ ገለልተኛ የምርጫ እና የድንበር ኮሚሽን በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር እስከ እኩለ ቀን ድረስ ከተመዘገቡ መራጮች ድምጻቸውን የሰጡት 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነው ብሏል።

    ለአምስተኛው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 22 ሚሊዮን ኬንያውያን ድምጻቸውን ለመስጠት የተመዘገቡ ቢሆንም፣ እስከ እኩለ ቀን ድረስ 6.2 ሚሊዮን የሚሆኑት ብቻ ድምጽ ሰጥተዋል።

    የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ንጋት 12 ሰዓት ላይ የጀመረ ሲሆን አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

    ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች መራጮች ወጥተው ድምጻቸውን እንዲሰጡ ቢጠይቁም፤ በተጠበቀው ልክ ሕዝቡ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች አልወጣም።

    ለዚህ ምክንያቱ እስካሁን ባይገለጽም፣ ኬንያ ከሶማሊያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች የአል ሻባብ ማስፈራሪያን ተከትሎ የመራጮች ቁጥር ሳስቶ ታይቷል።

    በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ አካባቢዎች የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው በሰላም ምርጫ እየተካሄደ ቢሆንም፣ መራጮች በአል ሻባብ ታጣቂዎች ወከባ እና ማስፈራሪያ እየደረሳቸው መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል።

    ከዚህ በተጨማሪም የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን ከምርጫ ካርድ ህትመት ስህተት ጋር ተያይዞ በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍል የሚደረጉ ምርጫዎችን አግዷል።

    ምርጫ የማይደረግባቸው አካባቢዎች ሞምባሳ እና ካካሜጋ የሚባሉ ግዛቶች የሚገኙባቸው ሲሆን፣ በእነዚህም ስፍራዎች በቀጣይ እስኪገለጽ ድረስ የአስተዳዳሪዎች ምርጫ አይካሄድም።

  5. የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የተቃና እንደነበር ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የሥልጣን ዘመናቸው የተጠናቀቀው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በማዕከላዊ ኬንያ ውስጥ ባለችው የትውልድ ስፍራቸው ኪያምቡ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ድምጽ ሰጥተዋል።

    ፕሬዝዳንት ኬንያታ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ይህ ምርጫ ነፃ እና ፍትሃዊ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፣ የምርጫው ሂደትም የተቃና ነበር" ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ማማ ንግና በመባል ከሚታወቁት የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤትና ከእናታቸው ንጊና ኬንያታ በኋላ ነው ድምጻቸውን የሰጡት።

    አባታቸው ጆሞ ኬንያታ ኬንያ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ቀንበር ነጻ ከወጣች በኋላ የአገሪቱ የመጀመሪያው መሪ ነበሩ።

    ፕሬዝዳንት ኬንያታ በሕገ መንግሥቱ መሰረት የሁለተኛውና የመጨረሻው የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ማብቃቱን ተከትሎ ሥልጣናቸውን ለቀጣዩ ፕሬዝዳንት ያስረክባሉ።

    ምክትላቸው ዊልያም ሩቶ እርሳቸውን ለመተካት ቢፈልጉም ኡሁሩ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና በአንድ ወቅት ተቀናቃኛቸው የነበሩትን ራይላ ኦዲንጋን እየደገፉ ነው።

  6. የዕጩ ፕሬዚዳንት ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች ያሳዩት ድጋፍ

    እጩ ፕሬዚዳንት ራይላ ኦዲንጋ ኪቤራ ሲደርሱ

    ከኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች አንዱ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ በመዲናዋ ናይሮቢ ኪቤራ የምርጫ ጣቢያ ደርሰው ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

    በናይሮቢ ከሚገኙት የተጎሳቆሉ ሰፈሮች አንዷ በሆነችው ኪቤራ ሲደርሱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎቻቸው በደስታ ተቀብለዋቸዋል።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    ሁሉም የድምጽ መስጫ ሰልፎች የተስተጓጎሉ ሲሆን በርካታ ደጋፈዎቻቸው ደስታቸውን በዘፈን፣ በጩኸትና በጭብጨባ ሲገልጹ ፖሊሶች ሕዝቡን መቆጣጠር እንዳልቻሉም ተነግሯል።

    እጩ ፕሬዚዳንት ራይላ ኦዲንጋ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በኪቤራ እና በአካባቢው በመቶዎች የሚቀጠሩ መራጮች የጠዋቱ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ሳይበግራቸው ከሌሊቱ አስር ሰዓት ጀምረው የምርጫ ጣቢያዎች እንዲከፈቱ በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።

    ከእነዚህም መካከል ልጆች ያዘሉ እናቶች እንዲሁም በድጋፍ የመጡ የእድሜ ባለጸጎች ነበሩ። ሰልፎቹም እስከ 2 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ እንደነበራቸው ቢቢሲ ተመልክቷል።

    ድምጽ የመስጠት ሥርዓቱ ከአመሻሹ 11 ሰዓት ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ በየጣቢያዎቹ የተገኙ መራጮች ከዚያ ሰዓት በኋላም ቢሆን እንዲመርጡ ይፈቀድላቸዋል።

    መራጮች በኪቤራ የጣቢያ ማዕከል ላይ
  7. ከሶማሊያ ጋር በሚዋሰነው አካባቢ መራጮች በአል ሻባብ ማስፈራሪያ እየደረሳቸው ነው

    በድንበር አካባቢ ያሉ መራጮች

    በአብዛኛው የሰሜን ምሥራቅ ኬንያ አካባቢዎች የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው በሰላም ምርጫ እየተካሄደ ቢሆንም፣ በአንዳንድ ቦታዎች በአል ሻባብ ታጣቂዎች ወከባ እንዲሁም መራጮች ማስፈራሪያ እየደረሳቸው መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል።

    ክልሉ ለሶማሊያ ድንበር ያለው ቅርበት ለአል ሻባብ ጥቃት የተጋለጠ የሚያደርገው ሲሆን፣ አል ሻባብ በክልሉ በአውሮፓውያኑ 2015 የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ላይ የፈጸመው ጥቃት የሚታወስ ነው።

    ሰኞ ምሽት በማንዴራ ግዛት በድንበር አካባቢ በሚገኙ መንደሮች እና ሰፈሮች ላይ ተጠርጣሪ ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸማቸው ተሰምቷል።

    አጠቃላይ የስልክም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎቶች በአካባቢው የተቋረጡ ሲሆን፣ ከማንዴራ ከተማ በስተምሥራቅ 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው አረብ ከተማ ኢላማ እንደተደረገችም ይታመናል።

    በድንበር አካባቢ ያሉ መራጮች

    በድንበሩ አካባቢ ያሉና ግንኙነት ያልተቋረጠባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ለመነጋገር ፍቃደኛ አይደሉም።

    ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በተለይም በምርጫ ወቅት የአል ሻባብ ስጋቶች ከበድ ተደርገው እንዳይነሱ የሚፈልጉ የመንግሥት የፀጥታ አባላትን እንዲሁም ከአል ሻባብ ሊደርስባቸው የሚችለውን የበቀል ጥቃት በመፍራት ነው።

    በምሥራቅ ዋጂር ድንበር አካባቢ ነዋሪዎች ወደየምርጫ ጣቢያዎቻቸው እንዳይሄዱ መከልከላቸውንም ዘገባዎች ጠቁመዋል።

    በቀርሳ መንደር ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ነዋሪዎች ታጣቂዎች ተሳፋሪ መራጮች ከሚጓዙበት መኪና ላይ እንዲወርዱ ትዕዛዝ እንደሰጡ እና በኋላ እንዳቃጠሉት ገልጸዋል።

    ታጣቂዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች በምርጫው እንዳይሳተፉ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ መቆየታቸውም ይናገራሉ። አስተያየት እንዲሰጡን የዋጂር ግዛት ፖሊስ ኃላፊ ሂላሪ ቶሮይች ቢጠየቁም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።

    የምርጫ አስፈፃሚዎች የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶችን ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ከመላክ እንዲዘገዩ ያስገደዱ ክስተቶች እንደተፈጠሩ ተነግሯል።

    • በምሥራቅ ዋጂር ኮንቶን መንደር ከአል ሻባብ ተዋጊዎች ነው ተብሎ የሚታመን ጥይት ከጫካ እየተተኮሰ ነበር።
    • ከዋጂር ከተማ በስተምዕራብ በምትገኘው ኤልዳስ የምርጫ ክልል፣ የፓርላማ ተወዳዳሪ ደጋፊዎች የምርጫ አስፈፃሚዎች እንዳይገቡ እየከለከሉ እንደሆነና ብጥብጥ እንዳለ ተነግሯል።
    • በኤልዳስ የምርጫ ክልል 72 የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ መስጠት አልተጀመረም። በኤልዳስ ከተማ ሰኞ ማምሻውንም የተኩስ ድምጽ ይሰማ የነበረ ሲሆን፣ ነገርግን ቢቢሲ ምን እንደተፈጠረ ማረጋገጥ አልቻለም።
  8. የኬንያ ምርጫ ከሌሎች አገራት በተለየ ለምን ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ ሆነ?

  9. የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን በአራት አካባቢዎች ምርጫ እንዳይካሄድ አገደ

    የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን ከፍተኛ ኃላፊ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን ዛሬ ነሐሴ 03/2014 ዓ.ም. ለሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ አራት አካባቢዎች ላይ የሚደረጉ ምርጫዎችን አግዷል።

    የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ዋፉላ ቼቡካቲ እንዳሳወቁት፣ ይህ እገዳ የተጣለው ከምርጫ ካርድ ህትመቶች ጋር በተፈጠረ ስህተት ነው።

    ምርጫ የማይደረግባቸው አካባቢዎች ሞምባሳ እና ካካሜጋ የሚባlኡት ግዛቶች የሚገኙባቸው ሲሆን፣ በእነዚህም ስፍራዎች በቀጣይ እስኪገለጽ ድረስ የአስተዳዳሪዎች ምርጫ ታግዷል።

    ሌሎቹ ፖኮት ሳውዝ እና ካቺሊባ ግዛቶች ናቸው ምርጫ የማይደረግባቸው። የታቱሙት ካርዶች የያዟቸው ዕጩዎች ዝርዝርና ምስሎች የተሳሳቱ ናቸው ተብሏል።

    ከበድ ያለ ውድድር ይጠበቅባቸዋል እንዲሁም በርካቶች በጉጉት ይጠብቋቸው የነበሩ ስፍራዎች ላይ ምርጫ መሰረዙን በዋዜማው ማሳወቃቸው ለኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ጥሩ ዜና አልነበረም ተብሏል።

    ሊቀ መንበሩ ዋፉካ ቼቡካቲ ከአምስት ዓመታት በፊት ሲመሩት የነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተሰርዞ በድጋሚ ከተካሄደ በኋላ የአመኔታ ችግር ገጥሟቸው ነበር።

    በዛሬው ዕለት የሚደረገው ምርጫ ከዚያ ቀውስ ነፃ የሚያወጣቸው ነው ተብሎ ቢገመትም የእግዱ ዜናን ተከትሎ ሥራቸውን አክብዶታል።

  10. ጥቂት ስለዛሬው ምርጫ፦

    በዛሬው ምርጫ መራጮች የሚመርጧቸው

    ከ22 ሚሊዮን በላይ ኬንያውያን ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ ሲሆን ቢያንስ ስድስት ድምጽ መስጠት አለባቸው።

    መራጮች የሚመርጧቸው፦

    • ፕሬዚዳንት
    • የክልል አስተዳዳሪ
    • ሴናተር
    • ብሔራዊ የምክር ቤት አባል
    • በብሔራዊ ምክር ቤት የሴቶች ተወካይ
    • የክልል ሕግ አውጪ አባል
  11. ለኬንያ ፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት እነማን ናቸው?

    የኬንያ እጩ ፕሬዚዳንቶች

    የፎቶው ባለመብት, AFP/ REUTERS

    ኬንያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት አራት ዕጩዎች ቀርበዋል፤ ስለ ዕጩ ፕሬዚዳንቶች በጥቂቱ፡

    • ዴቪድ ሙዋሬ፦ የኬንያ አጋኖ ፓርቲ፣ በሙያቸው ጠበቃ እንዲሁም ሰባኪ የሆኑት ዴቪድ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ያሰቡት በአውሮፓውያኑ 2013 ነበር። በኋላ ግን በውድድሩ ተሳታፊ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በዘንድሮው ምርጫ አገሪቱን ለቀጣዩ አምስት ዓመት ለመምራት እየተፋለሙ ይገኛሉ።
    • ራይላ ኦዲንጋ፦ የአዚሚዮ ላ ኡሞጃ ጥምረት፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እና አንጋፋው ፖለቲከኛ፣ አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ለአምስተኛ ጊዜ ሙከራቸውን እያደረጉ ነው።
    • ዊሊያም ሩቶ፦ የተባበሩት ዲሞክራቲክ አሊያንስ፡ አገሪቷን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ለሚመሩት ዊልያም ሩቶ ይህ የመጀመሪያ የፕሬዝዳንትነት ምርጫቸው ነው።
    • ጆርጅ ዋጃኮያ፦ የኬንያ ሩትስ ፓርቲ፣ ጠበቃውና ፕሮፌሰሩ ዋጃኮያ ለየት ባለ ሃሳባቸው ለፕሬዝዳንትነት ለመጀመሪያ ጊዜ እየተወዳደሩ ነው።
  12. በዓለም ከፍተኛ ወጪን ካስወጡ ምርጫዎች አንዱ

    የድምጽ መስጫ ሳጥኖች

    ዛሬ የሚካሄደው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በአገሪቱ ታሪክ ከባድ ፉክክር የሚደረግበት እንደሚሆን ይጠበቃል። በተለይ በምክትል ጠቅላይ ፕሬዝዳንቱ ዊሊያም ሩቶ እና በተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ መካከል የሚደረገው ፉክክር ምርጫውን ተጠባቂ አድርጎታል።

    ለሁለት አምስት ዓመታት በተከታታይ አገሪቱን የመሩት ኡሁሩ ኬንያታ ምክትላቸውን ገሸሽ አድርገው ለተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ ድጋፍ መስጠታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

    የእዚህ ዓመቱ የኬንያ ምርጫ ከሁሉ የተለየ የሚሆነው በዓለም ከፍተኛ ገንዘብ ካስወጡ ምርጫዎች መካከል አንዱ መሆኑ ጭምር ነው።

    ከ22 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ለመምረጥ ብቁ ከሆኑ ከ5 ኬንያውያን 4ቱ በመራጭነት ተመዝግበዋል።

    ለምርጫው የተመደበው ገንዘብ ከ383 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው። በዚህም ለእያንዳንዱ መራጭ 17 ዶላር ወጪ ይደረጋል ማለት ነው። ይህም በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ከተመደበው ገንዘብ ከፍተኛው ነው።

    በዛሬው ዕለት መራጮች ከፕሬዝዳንት በተጨማሪ 47 አገረ ገዢዎችን፣ 47 የምክር ቤት አባላትን፣ 290 የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትን፣ 47 የብሔራዊ ምክር ቤት የሴት ተወካዮችን እና 1450 የግዛቶች ምክር ቤት አባላትን ይመርጣሉ።

    ለዚህም በመላዋ አገሪቱ 290 የምርጫ ክልሎች ያሉ ሲሆን፣ ከ46,000 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች ተዘጋጅተዋል።

  13. በአሸናፊነት የምንወጣበትን ቀን በጉጉት እየጠበቅኩ ነው - ዊሊያም ሩቶ

    ዊሊያም ሩቶ ድምጽ ሲሰጡ
    የምስሉ መግለጫ, ዊሊያም ሩቶ ድምጽ ሲሰጡ

    የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ዛሬ በማለዳው በትውልድ አካባቢያቸው ሪፍት ቫሊ ውስጥ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ እንደተናገሩት በፕሬንታዊው ምርጫ አሸናፊ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

    ሩቶ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “የድል ቀናችንን በጉጉት እየጠበቅኩ ነው” ብለዋል።

    “የኬንያ ሕዝብ አገራችንን ወደ ቀጣዩ ዘመን ወደፊት የሚወስደውን ምርጫ እንደሚያደርጉ እርግጠኛ ነኝ... ስለዚህም ሁላችንም የሕዝቡን ምርጫ ልናከብር ይገባል።”

    የ55 ዓመቱ ዊሊያም ሩቶ ለ10 ዓመታት በአሁን ወቅት በአመለካከት ከተለያዩት የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምክትል ሆነው የሠሩ ሲሆን፣ ለፕሬዝዳንተንት ሲወዳደሩ የመጀመሪያቸው ነው።

    ዋነኛው ተቀናቃኛቸው የቀድሞው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይና ኦዲንጋ ለረጅም ጊዜ በተቃዋሚ ፓርቲ መሪነት የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት ለ5ኛ ጊዜ ነው።

  14. ኬንያውያን ፕሬዚዳንታቸውን ለመምረጥ ድምጽ መስጠት ጀመሩ

    ኬንያውያን ድምጽ በመስጠት ላይ

    ኬንያውያን ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቷን የሚመራውን ፕሬዚዳንታቸውን ለመምረጥ በዛሬው ዕለት ነሐሴ 03/2014 ዓ.ም. ወደ ምርጫ ጣቢያዎች አቅንተዋል።

    በመላው አገሪቱ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱ ሲሆን ድምጽም መስጠት ተጀምሯል።

    በኬንያ ሪፍት ቫሊ ክልል በሚገኘው ኮሳሼይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለፕሬዚዳንትነት እየተወዳደሩ ያሉት የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ድምጽ ሰጥተዋል።

    የፕሬዚዳንት ዕጩ ራይላ ኦዲንጋ ጋር አብረው እየተወዳደሩ ያሉት ማርታ ካሩዋ በኬንያ ማዕከላዊ ግዛት ኪሪያኒጋ ግዛት ውስጥ ውስጥ ድምጽ ሰጥተዋል።

    የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች እስከ አመሻሹ 11 ሰዓት ድረስ ክፍት ሆነው የሚቆዩ ሲሆን፣ ድምጹን ለመስጠት በሰልፍ ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ድምጽ እንዲሰጥ ይፈቀድለታል።

    ቢቢሲ አማርኛ ከኬንያ ምርጫ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በቀጥታ ዘገባ ገጹ ያቀርባል።