በቡራዩ በጅብ ተበልቶ እግሮቹን ያጣው ወጣት

ብርሃኑ ዳባ

የፎቶው ባለመብት, tena temesgen

የምስሉ መግለጫ, ብርሃኑ ዳባ

ብርሃኑ ዳባ ቤተሰቦቹ የሚኖሩት ቡራዩ ለኩ ከታ መንደር ነው።

ባላፈው ሳምት ነሐሴ 04/2014 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት ከሚኖርበት ሞጆ ወደ ቤተሰቦቹ ዘንድ የሄደው ጉዳይ ለማስፈፀም ነበር።

ነገር ግን አልተሳካለትም፤ በማግስቱ ሞጆ ተመልሶ የሥራ ገበታው ላይ መገኘት ያሰበው ብርሃኑ ወደ ጓደኛው ዘንድ ደወለ።

“ሌሊቱን ወደ ሞጆ የሚሄዱ መኪኖች አሉ። ስለዚህ ወደ ዊንጌት ሄጄ እነርሱን ለመያዝ ነበር ያሰብኩት” ሲል ያክላል።

“የዚያን ዕለት ቡራዩ ቤተሰቦቼ ጋር ሄጄ ነበር። ያሰብኩት ጉዳይ አልተሳካልኝም። የሥራዬ ቦታ ደግሞ ሞጆ ስለሆነ አንድ የማውቀው ሰው ጋር ደወልኩኝ። እና ዛሬ ማታ ስለምወጣ አብረን ተጉዘን ነገ ሥራ መግባት ትችላለህ አለኝ” ይላል አደጋው ከመድረሱ በፊት የተፈጠረውን ሲያስታውስ።

ብርሃኑ የደወለለት ወዳጁ ‘ዊንጌት እጠብቅሃለሁ’ ስላለው ከቡራዩ ከታ ወደ አስኮ እየተጓዘ እያለ በተለምዶ በግ ተራ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ጅብ ማየቱን ያስታውሳል።

ነገር ግን ብርሃኑ ያሰበበት ቦታ ከመድረሱ በፊት መንገድ ላይ ጅቦች ተተናኮሉት። በዚያም የተነሳ ሁለት እግሮቹን አጣ።

“በግ ተራ አካባቢ ቁልቁለቱን እየወረድኩ፣ አንድ ጅብ ሲመጣ አይቻለሁ። ከዚያ በኋላ የሆንኩትን ነገር አላስታውስም። በማግስቱ አምስት ሰዓት ላይ ራሴን ሆስፒታል ውስጥ አገኘሁት፝።”

ብርሃኑ የተለያዩ የአካል ክፍሎቹ በጅብ ተነክሷል።

ጀርባው እጁ እንዲሁም እግሮቹ ላይ ከንክሻው የተነሳ ጉዳት ደርሶበታል።

ከሁሉም ግን እግሮቹ ላይ የደረሰው ጉዳት የከፋ ነበር።

“ስነቃ ሆስፒታል ውስጥ ተኝቻለሁ። ከጉልበቴ በታች ያለው አካሌ የለም። ቤተሰቦቼ የተኛሁበትን አልጋ ከብበው ቆመዋል።”

ከገባበት ሰመመን ሲነቃ ራሱን ሆስፒታል ውስጥ ተኝቶ ያገኘው ብርሃኑ ስለገጠመው ነገር በቅጡ የሚያስታውሰው የለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ወደ ሆስፒታል ያመጣህ የፖሊስ አምቡላንስ ነው ይሉኛል እንጂ በትክክል ማን እንዳመጣኝ አላውቅም። ስነቃ ራሴን ሆስፒታል ውስጥ ተኝቼ ነው ያገኘሁት” ይላል ብርሃኑ።

“ከጉልበቴ በታች ተጎድቷል። አንደኛው እግሬ ከቁርጭምጭሚቴ በታች የለም። የቀኝ እግሬ ደግሞ ተንጠልጥሎ ነበር። ከዚህ በላይ ደም ከፈሰሰህ ትሞታለህ ስላሉኝ ተቆረጠ” ሲል ያክላል።

ብርሃኑ በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው አቤት ሆስፒታል ሕክምናውን እየተከታተለ ይገኛል።

ወደ ሆስፒታል ሊጠይቁት የመጡ ሰዎች በቅድሚያ ቡራዩ ጤና ጣቢያ የመጀመርያ እርዳታ ከተሰጠው በኋላ፣ ለተጨማሪ ሕክምና ወደ አቤት ሆስፒታል መምጣቱን እንደነገሩት ለቢቢሲ ገልጿል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፖሊስ ባልደረቦች ብርሃኑን ጉዳት ከደረሰበት ስፍራ አንስተው ወደ ሕክምና ተቋም የወሰዱት የአካባቢው የፀጥታ አባላት መሆናቸውን ይናገራሉ።

ኢንስፔክተር መልካሙ አሰፋ፣ በቡራዩ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ናቸው።

በዕለቱ እኩለ ሌሊት ላይ የፀጥታ አካላት ብርሃኑ የወደቀበት ስፍራ እንዳገኙት ለቢቢሲ ገልፀዋል።

“ስንደርስ አንድ እግሩ ሙሉ በሙሉ ተበልቷል። ሁለተኛው እግሩ ደግሞ ከቁርጭምጭሚቱ በታች ተበልቷል። ግራ ጎኑ ደግሞ ተቦጭቋል።”

የፀጥታ አባላቱ በስፍራው ሲደርሱ የጅብ ጩኽት ይሰማ እንደነበር የሚናገሩት ኢንስፔክተሩ፣ ብርሃኑን አንስተው በፖሊሰ መኪና በቅርብ ወደ ሚገኘው የቡራዩ ጤና ጣቢያ መውሰዳቸውን እና ከዚያ በኋላ ወደ ሆስፒታል እንዲሄድ ድጋፍ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

ወደ ቡራዩ ፖሊስ ከተመደቡ ቅርብ ጊዜያቸው መሆኑን የሚናገሩት ኢንስፔክተር መልካሙ በከተማው እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች አልፎ አልፎ ሲከሰቱ እንደቆዩ መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል።