በጣሊያን የሰፈነው ዘረኝነት ለምን በአፍሪካውያን ላይ የከፋ ሆነ?

አሊካ ኦጎቹዉ

የፎቶው ባለመብት, EPA

አሊካ ኦጎቹዉ በግፍ ተገደለ። ናይጄሪያዊ ነው። መሐረብ ቸርቻሪ ነበር። በጣሊያን ጎዳና በአንድ ነጭ በጠራራ ፀሐይ ተገደለ፤ ይህ የሆነው በቅርብ ነው።

ለትውልደ ኤርትራዊቷ ፊልም ባለሙያ አሪያም ተክሌ ይህ ግድያ የለየለት የዘረኝነት ጥቃት ነው።

የአካባቢው ፖሊስ ግን ግድያው ዘረኝነት ነው ብሎ አያምንም፤ ወይም ለማመን አይፈልግም።

ይህ የመሐረብ ቸርቻሪ የ39 ዓመት ናይጄሪያዊ ነበር።

ሟች የባሕር ዳርቻ በሆነችው ሲቪታኖቫ ማቼ ነዋሪም ነበር። ኑሮን ለማሸነፍ ይታትርም ነበር።

በመሐረብ ችርቻሮ ሕይወቱን ሊለውጥ።

እንደሚባለው ይህ ናይጄሪያዊ ገዳዩን እና አብራው የነበረችውን ጓደኛውን ሳንቲም ካላችሁ እያለ ይለምናቸው ነበር።

ቸግሮት ስለነበረ እየተከተለ ለመናቸው።

ድንገት ነጩ ሰው ተቆጣ። ናይጄሪያዊውን አሳደደው፣ ደበደበው፣ ደብድቦትም አልረካም።

በጠራራ ፀሐይ ገደለው።

ይህ ሲሆን ሰዎች፣ በርካታ ነጭ ጣሊያናዊያን ዳር ቆመው እያዩ ነበር። አንዳቸውም ጣልቃ ገብተው የናይጄሪያዊውን ሕይወቱን ለማትረፍ አልሞከሩም።

ደግነቱ ይህ ሲሆን በካሜራ ተቀረፆ ነበር።

ተጠርጣሪው ፍሊፖ ክላውዲዮ ጁሴፔ ፈርላዞ ይባላል። አሁን በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራው ቀጥሏል።

ምናልባት በካሜራ ባይቀረጽ የናይጄሪያው ሞት ትዝ የሚለውን ላይኖር ይችል ነበር።

አሁን ግን ቁጣን ቀስቅሷል። በርካታ የተቃውሞ ሰልፎችም እየተደረጉ ነው።

ጆርጂያ ሜሎኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጆርጂያ ሜሎኒ ፓርቲ የአክራሪ ነጮችን ድጋፍ ለማግኘት እንደሚጥር ይከሰሳል

የአክራሪ ነጮች እንቅስቃሴ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዚህ መሐረብ ቸርቻሪ ናይጄሪያዊ ሞት ግን በጣሊያን ዘረኝነት ውስጥ ተምሳሌት ይሆን ይሆናል እንጂ ብቸኛው ጉዳይ አይደለም።

በ2016 ሌላ ናይጄሪያዊ በተመሳሳይ ሁኔታ ተገድሏል።

ይህ ሟች ቺዲ ናመዲ ይባላል። የተገደለው በማዕከላዊ ጣሊያን ፌርሞ ከተማ ነበር። ሟች ሚስቱን ከዘረኞች ጥቃት ሲከላከል ነው የተገደለው።

ሌላም ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሟል። ከሁለት ዓመታት በፊት።

አንድ ነጭ አክራሪ ድንገት የተኩስ እሩምታ ጥቁሮች ላይ ከፈተና ስድስት አፍሪካዊያንን አቆሰለ።

ፖሊስ በቁጥጥር ሲያውለው ይህ አክራሪ “ጣሊያን ለዘላለም ትኑር” እያለ ጭንቅላቱን በጣሊያን ባንዲራ ሸፍኖ ይጮኽ ነበር።

ሁሉንም ጥቁሮች መጨረስ እንደሚፈልግም ይናገር ነበር።

ይህ ጥቁሮች የሚገደሉትበት የጣሊያን አካባቢ ከ2020 ጀምሮ ‘ፍራቴሊ ዲ ኢታሊያ’ በሚባለው የአክራሪ ነጮች ፓርቲ ነበር ሲመራ ነው የቆየው።

የዚህ ፓርቲ መሪ ጂርጂያ ሜሎኒ ናት። በመስከረም በሚካሄደው ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ልትሆን ትችላለች ተብሎ ተሰግቷል።

ያን ጊዜ በመላው ጣሊያን ጥቁሮች ላይ ሊደርስ የሚችለው ነገር ከወዲሁ ስጋት ሆኗል።

አርያም ተክሌ ጥቁሮች በጣሊያን የዘረኝነት ጥቃት ሲደርስባቸው ነው የኖረው ትላለች።

አሁን ደግሞ የአክራሪ ነጭ ብሔረተኛ ፓርቲዎች ማቆጥቆጥ ጥቃቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ አድርሶታል ብላም ታምናለች።

እነዚህ ፓርቲዎች ዘረኝነትን የዋዛ ተደርጎ እንዲታይ አድርገዋል ስትል ትከሳለች።

በደምሳሳው በርካታ ጣሊያናዊያን ዘረኝነት አስቀያሚ ነገር እንደሆነ ተረድተው አይደለም የሚያድጉት።

“ሁልጊዜም የሆኑ ሰዎች የድንቁርና ድርጊት እንደሆነ ሊያስረዱህ ይሞክራሉ፤ ወይም ደግሞ በአሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደም የባሰ ነው ይሉሃል፤ በጣሊያን ዘረኝነት እንዳለ ማመን ራሱ አይፈልጉም።”

አርያም የተወለደችውና ያደገቸው በጣሊያን ሚላን ነው።

ቤተሰቦቿ በጣሊያን ለአምስት ዐሥርታት ኖረዋል። ሆኖም ጣሊያናውያን ከእነርሱ አንዷ እንደሆነች አድርገው ሊመለከቷት በፍጹም አይፈቅዱም።

“በሚላን ዘዬ እያናገርኳቸው ከየት አገር ነሽ? ይሉኛል።”

ጣሊያን ለስደተኛ ፈተና ናት።

አፍሪካውያን ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጣሊያን ያሉ አፍሪካውያን እየጠነከረ የመጣው የቀኝ አክራሪ ነጮች እንቅስቃሴ ያሳስባቸዋል

እንደ ጣሊያናዊ የመታየት ፈተና

ሜዲትራኒያንን ሲሻገሩ የምትገኝ አገር ናት። በዚህ ብዙ ስደተኛ መግቢያ ሆናለች። ይህ ለነጭ አክራሪ ብሔረተኞች በጥቁሮች ላይ ጥላቻን ለመንዛት ሳይመቻቸው አልቀረም።

ጣሊያን ሁልጊዜም በስደት ከመጡ ቤተሰቦች የሚወለዱትን ሕጻናት ዜግነት እንዳያገኙ መንገዱን ከባድ ታደርግባቸዋለች።

በጣሊያን ምድር ስለተወለዱ ብቻ ጣሊያናዊ አይሆኑም። 18 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ታስጠብቃቸዋለች።

አለሲያ ሬይና ተማሪ ናት።

የፀረ ዘረኝነት ቡድን አባልም ናት።

ተወልዳ ያደገችው በጣሊያን እምብርት ቢሆንም፣ ጣሊያናውያን ግን እንደማይቀበሏት ታስረዳለች።

ሬይና በሮም ነው የተወለደችው። ከአፍሪካዊ አሜሪካዊ አባት እና አፍሮ ፔሯዊ እናት ነው የተገኘችው።

አባትና እናቷ በዝነኛው ኮሎሲየም ደጅ ላይ ተገናኝተው ተፋቅረው በፍቅር ከተማ ሮም እሷን ወለዱ። ሮም ግን እሷን መቀበል አልፈቀደችም።

ሚላን አቅራቢያ ወደምትገኝ ትንሽ ከተማ ሄደች። ትምህርቷን በዩናይትድ ኪንግደም ተከታተለች።

ይሁንና ጣሊያናውያን በቃ ከእነርሱ አንደ አንዳቸው አድርገው ሊያይዋት ይተናነቃቸዋል።

“ጣሊያናውያን መዋቅራዊ ዘረኝነት እንዳለባቸው ማመን አይፈልጉም” ትላለች።

ጣሊያናውያን መዋቅራዊ ዘረኝነት እንዳለ አምነው ችግሩን ለመፍታትም ዝግጁ እንዳይደሉ ትናገራለች።

ለዚህ ዋቢ የምታደርገው የቢዩቲ ዴቪስን ጉዳይ ነው።

ቢዩቲ ዴቪስ ናይጄሪያዊት አስተናጋጅ ናት። የሠራችበትን ሒሳብ ስለጠየቀች ብቻ በአሰሪዋ በጥፊ መመታቷን እንደማሳያ ታነሳለች።

ይህ ድርጊት ደግሞ ለብዙ ጣሊያናውያን ችግር ሆኖ ሁሉ አይሰማቸውም።

“የሠራችበትን ስለጠየቀች ነው በጥፊ የተመታችው። ነጭ ሰው ብትሆን በጥፊ መመታቷ በዋዛ አይታለፍም ነበር።”

ሽልማት ያገኘችው ኡባ ክርስቲና አሊ ፋራህ ስመጥር ትውልደ ሶማሊያዊት - ጣሊያናዊት ደራሲ ናት።

በርካታ ጣሊያናውያን ስለ ቅኝ ግዛት ዘመን ታሪካቸው ዕውቀት እንደሌላቸው ታወሳለች።

ጣሊያን በሊቢያ፣ በሶማሊያ እና በኤርትራ ቅኝ ገዥ ነበረች።

በኢትዮጵያም ለአምስት ዓመታት ቆይታለች። ይህን የቤኔቶ ሞሶሎኒን ዘመን ብዙ ጣሊያናውያን ወጣቶች አያውቁትም ወይም ማወቅ አይሹም።

የአሊ ፋራህ ቤተሰብ በጣሊያን ለግማሽ ምዕተ ዓመት ኖሯል። ይህ ግን እንደ መጤ ከመታየት አላተረፋቸውም።

ደራሲ አሊ ፋራህ አሁን በአገሯ ጣሊያን ስለተንሰራፋው ዘረኝነት ስታስረዳ ይህን ትላለች።

“እኛን የቅኝ ግዛት ታሪክ ያስተሳሰረንን እንኳ ጣሊያናውያን ዕውቅና ለመስጠት አልደፈሩም። በባሕር ተሻግረው ለሚመጡ ጥቁሮች እንዴት ነው ዕውቅናን እንዲሰጡ የምትጠብቁት?”