አድዋን በምናባዊ እውነታ የሚያስቃኘው ጉዞ ቴክኖሎጂስ

በጉዞ ቴክኖሎጂስ የፕሮጀክት ማናጀር የሆነችው ሜቲ ግርማ

አድዋ የኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም።

ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ወራሪን አሳፍረው የመለሱት ከወራሪዎች ጋር ተናንቀው በደም እና በላብ ነው።

ይህ ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው የተዋደቁለት ነጻነት፣ የድሉ ብስራት ዜማ በሌሎች በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ጥቁሮች ጆሮ ደርሶ ለትግላቸው ስንቅ፣ ለጉልበታቸው ብርታት ሆኗል።

አድዋ የአንድ ወቅት ታሪክ ብቻ አይደለም። ከዘመን ዘመን፣ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ የነጻነት አርማ ነው።

ይህንን የማያረጅ ታሪክ፣ የማይደበዝዝ ጌጥ የታሪክ ባለሙያዎች ሰንደውታል። የጥበብ ባለሙያዎች ተቀኝተውበታል።

ቴአትር ሆኖ ተመድርኳል፣ ፊልም ሆኖ ለዕይታ በቅቷል። ሙዚቃው እንደ ብሔራዊ መዝሙር ዘወትር እየተዘመረ አለ።

እጅጋየሁ ሽባባው. . .

“. . . የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣

ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት. . .”ስትል

ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን ደግሞ. . .

“. . . አድዋ የዘር አፅመ ርስትዋ

የደም ትቢያ መቀነትዋ

በሞት ከባርነት ስርየት

በደም ለነጻነት ስለት

አበው የተሰውብሽ ለት. . .”በማለት ተቀኝተዋል።

የዚህ ዘመን ወጣቶች አካል የሆኑት ጉዞ ቴክኖሎጂስ ደግሞ ሌላ ሃሳብ አላቸው።

ተመልካች የአንድን ክስተት አካል የሆነ ያህል በሚመስል ሁኔታ በምስል የሚያሳየው ዘመናዊ ጥበብ የሆነው ቨርችዋል ሪያሊቲ፣ ወይም የአማርኛ አቻው ምናባዊ እውነታ፣ ለጉዞ ቴክኖሎጂስ የተካነበት ነው ሊባል ይችላል።

ቴክኖሎጂው ባለንበት ስፍራ ሆነን በታሪክ ወደ ኋላ እና ወደፊት እንድንጓዝ ያስችላል።

ባልዋልንበት ቦታ ውለን፣ ባልወጣነው እና ባልወረድነው ተራራ እንድንመላለስ ማድረግ የምናቡ ውጤት ነው።

ጉዞ ቴክኖሎጂስ ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የኢትዮጵያውያንን የጋራ ታሪክ፣ አድዋን ለመዘከር ይጥራል።

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአጼ ምኒልክ በተመራው የኢትዮጵያ ሠራዊት እና ባሕር አቋርጦ ከአውሮፓ የመጣው የጣሊያን ሠራዊት ጋር የተካሄደው የአድዋ ጦርነት በታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱ ግዙፍ ታሪኮች መካከል አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታዎችን እና ቅርሶችን ዘመናዊ በሆነ መልኩ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲጎበኙ ለማስቻልም አቅደዋል።

ጉዞ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያውያን በታሪክ እና በዘፈን የሚያውቁትን አድዋን፣ በአካል የመገኘት ያህል እንዲቃኙት ለማስቻል የቨርችዋል ሪያሊቲ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሰርተዋል።

በዚህ ቨርትዋል ሪያሊቲ፣ የአድዋን ተራሮች፣ ጦርነቱን፣ በጦርነቱ ላይ የተሰዉ ጀግኖችን በቦታው የመገኘት ያህል ያሳያል።

በዚህ ውስጥ ደግሞ ታሪክ ነጋሪዎች መጥተው ተጨማሪ ማብራርያ ይሰጣሉ።

በ800 ገጾች የነበረን የታሪክ አምድ በ30 ደቂቃ መሰብሰብ መቻሉን በጉዞ ቴክኖሎጂስ ውስጥ የፕሮጀክት ማናጀር የሆነችው ሜቲ ግርማ ትገልጻለች።

አድዋ ሳይዘምቱ፣ በጦርነቱ ላይ አንድም ጠጠር ሳይጥሉ፣ በእጅዎ ጠላት ሠራዊት ሳይወድቅ አድዋን መታደም መቻል ነው የጉዞ ቴክኖሎጂ ሃሳብ።

‘አድዋ ዛሬ ናት፣ አድዋ ትናንት’ እንደ ማለት ነው።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, አድዋን ለመጪው ትውልድ ለማስተዋወቅ የሚተጉት ወጣቶች

የጉዞ ቴክኖሎጂስ መነሻ ምንድን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጉዞ ቴክኖሎጂስ የፕሮጀክት ማናጀር የሆነችው ሜቲ ግርማ ሶርያ በጦርነት እሳት ስትለበለብ ተመልክታለች።

ይህ የሶርያ ጦርነት ሰዉን እንደ ቋያ ሲያነድ፣ የታሪክ ቅርሶችን ዶግ አመድ ሲያደርግ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እንደ ተራ ወሬ ዘግበውት ሲያልፉ አይታለች።

“ቅርሶቹ ይሁነኝ ተብሎ በጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ወድመዋል። አንዳንዶቹ በጦርነቱ መካከል በተተኮሱ ከባድ መሳርያዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ታሪክ ይሰረዛል፤ እንደ አዲስ ይጻፋል” ትለላች ሜቲ።

ይህ ደግሞ አድዋን በቨርችዋል ሪያሊቲ ሰርቶ ለማስቀመጥ ምክንያት ሆናቸው።

ኢትዮጵያ ነጻነቷን ለማስጠበቅ በርካታ ጦርነቶችን አካሄዳለች የምትለው ሜቲ ግርማ፣ እነዚህ አበው እና እመው ጀግኖች ደማቸውን የገበሩባቸው፣ አጥንታቸውን የከሰከሱባቸው፣ ላባቸውን ያፈሰሱባቸው ጦርነቶች ለአሁኑ እና ለመጪው ትውልድ በአግባቡ አንዲተላለፍ ለማድረግ የድርሻቸውን ለመወጣት እየሰሩ መሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት አስረድታለች።

ጉዞ ቴክኖሎጂስ አፍሪካን በዲጂታል ዓለም ላይ ከፍ አድርጎ ማጉላት ያስባሉ።

የኢትዮጵያን ቅርሶች በቨርቹዋል ዓለም ህያው አድርጎ ማኖር ሌላኛው የዕቅዳቸው አካል ነው።

አፍሪካ የታሪክ ሀብታም ናት። እነዚህ የታሪክ ሐብቶች፣ በቁስም ሆነ በቅርሳ ቅርስነት የሚጠቀሱ ናቸው።

በዚህ የዲጂታል ዓለም አፍሪካን ቅርሶች የዓለም ዐይን ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ የጉዞ ቴክኖሎጂስ ባልደረቦች ምኞት ነው።

ምኞታቸውንም ሜቲ ስትገልጽ “የአፍሪካን ቅርሶች በዲጂታል መልክ ማስቀመጥ ቢቻል፤ መጪው ትውልድ በርካታ ነገር ሊማርበት ይችላል። በዚህ ወቅት እኛ ማየት ያልቻልነውን ማየት ይችላሉ” ትላለች።

ጉዞ ቴክኖሎጂስ ከኢትዮጵያ አልፎ ኮንጎ መቀመጫውን ካደረገ እና 'ኢንስቲትዩት ኦፍ ፍራንሲስ' ከተሰኘ ተቋም ጋር እየሰራ ይገኛል።

በዚህም ወደ ኮንጎ ተጉዘው ጎማን፣ ካውዚ ቤጋን፣ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖችን እና ጎሬዛዎችን ጎብኝተው ተመልሳል።

አሁን ዐይናቸው ያየውን፣ ጆሯቸው የሰማውን ወደ ምናቡ ዓለም በማምጣት በቨርችዋል ሪያሊቲ ማስቀመጥ ይቀራቸዋል።

ይህ የኮንጎን ቱሪዝም ለማሳደግ የሚውል ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ይህንን በሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር በማስፋት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቱሪዝምን፣ ጤናን እና ትምህርትን ማገዝ ያስባሉ።

በኢትዮጵያ ባህልና ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው

የራሱን ጀግና ያጣው ትውልድ

“ጀግኖች ያሉን አይመስለኝም” ትለላች ሜቲ በአፍላ ወጣትነት ያደገችባቸውን ዘመናት ስታስታውስ።

“ለምሳሌ ወንድሜ ስፓይደር ማንን ነው እንደምሳሌ የሚወስደው። አድዋ ላይ የተለበሱት ዓይነት አልባሳት መልበስ አይፈልግም። የስፓይደር ማንን አልባሳት ነው መልበስ የሚፈልገው።”

ይህ ደግሞ የሚያሳየው ስለታሪካችንን ያለንን ዝቅ ያለ እውቀት ነው ትላለች ሜቲ።

በጉያ ያንጠለጠሉትን ቱባ ታሪክ ጥሎ የሌላ ዓለም ጀግናን መቀላወጥ የዚህ ትውልድ እጣ ፈንታ ይመስላል።

የራሱ ጀግና ጠፍቶበት ጀግናውን ከሆሊውድ ፊልሞች ማህፀን ለማዋለድ የሚጥር ትውልድ ጉዳይ ያስጨንቃታል።

በሌላ ወገን ደግሞ የተለያዩ ታሪኮች የተጻፉት በበርካታ የታሪክ ምሁራን እና አዋቂዎች መሆኑ ሌላ ራስ ምታት ነው።

በዚህ ሩጫ በበዛብት የጥድፊያ ዓለም፣ ጊዜ ኖሮት ታሪኬን ልወቅ ብሎ ራሱን መጻሕፍት መካከል የሚቀብር ማግኘት መታደል ነው። ለዚህ ነው ቨርችዋል ሪያሊቲ መፍትሔ በደጅ የሆነ ቴክኖሎጂ የሆነው።

የረዥም ዓመት ታሪክን አጠር አድርጎ በሰላሳ እና ስልሳ ደቂቃ ውስጥ ጠብሰቅ አድርጎ መንገር፣ ማሳየት እና ማስዳሰስ መቻል የቴክኖሎጂው በጎ ጎን ነው።

ለዚህም ነው የኢትዮጵያውያን የሶፍትዌር ኢንጂነሮች ቡድን የአድዋ ጦርነትን የሚያሳይ ቨርችዋል ሪያሊቲ የሰሩት።

ኤፒክ ጌምስ ደግሞ ፕሮጀክታቸውን በገንዘብ በመደገፍ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።

ጉዞ ቴክኖሎጂስ አራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፀው በመስራት ላይ መሆናቸውን ሜቲ ትናገራለች።

ከእነዚህ መካከል አድዋ፣ ሶፍ ኡመር፣ ጢያ ይገኙበታል።

የአድዋ ጦርነትን በቨርችዋል ሪያሊቲ ሲሰሩት በርካታ የታሪክ ባለሙያዎች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በጋራ በመሆን ታሪኩን ሥጋ በማልበስ ረገድ ሚናቸውን ተወጥተዋል።

በዚህም ወጣቶች ታሪካቸውን እንዲሁም ጀግኖቻቸውን በቀላሉ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል ብለው ያምናሉ።

በተጨማሪም ታሪኮችን በመሰነድ ለወጣቶች እና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ከዓላማቸው መካከል አንዱ ነው።

የመጣበትን የሚያውቅ፣ የሚሄድበትን አይስትም የምትለው ሜቲ፣ አባት እናቶቻችን የከፈሉትን መስዋዕትነት ማወቅ እና ማክበርም ተገቢ መሆኑን ታሰምርበታለች።

ብዙ አፍሪካውያን ታሪካቸውን ባለማወቃቸው ታሪኮቻቸው በዲጂታል መልኩ ተሰንደው ካልተቀመጡ ሊጠፉ ይችላሉ ብላ ትሰጋለች።

በቨርችዋል ሪያሊቲ ሥራው ላይ የተሳተፉት የታሪክ ተመራማሪ፣ አፍሪካውያን ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለወጣቱ ትውልድ ታሪክና ባህላቸውን ማስተማር ይችላሉ ይላሉ።

በኢትዮጵያ ባህልና ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው “ወጣቱ ትውልድ መጻሕፍትን ማንበብ፣ እንዲሁም በብዛት የማይገኙ መዛግብትን ማየት ላይ አያተኩርም” እላሉ።

በተለይ ደግሞ እንደ አድዋ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ታሪኮች በቨርችዋል ሪያሊቲ መልክ ሲቀርቡ፣ ወጣቱ በቀላሉ ሊማር እነደሚችል ይናገራሉ።

ጉዞ ቴክኖሎጂስ ይህንን የአድዋ ምናባዊ እውነታ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በተለያዩ መናፈሻዎች፣ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ለማሳት እቅድ ዕዟል።

በዚህም ታሪካቸውን ለማወቅ ፍላጎት ላላቸው እና የታሪክ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ሳቢ ላልሆነላቸው ተማሪዎች መፍትሔ ማቀበል መሆኑን ሜቲ ትገልጻለች።