የአድዋ ድል በዓል፡ አድዋን በሎሬት ፀጋዬና በእጅጋየሁ ሽባባው ሥራዎች ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Tsehay Publishers/ Getty Images
- ፀሐፊ, ደረጀ በላይነህ
- የሥራ ድርሻ, (ደራሲና ኀያሲ)
የዓድዋን ጦርነትና ድል በጥሞና ስንቃኝ፣ የእንባ ጤዛና የሳቅ ዜማ በትይዩ ያፏጩብናል። በአንድ አፋፍ ከረዥም ዓመታት በፊት በደም የተነከረ መስዋዕትነት፣ በሌላው በቋያ እሳት ተፈትኖ አልፎ፣ ዓለምን ያስደነቀና የነቀነቀ የድል ብስራት ወርቅ ሆኖ ሲወጣ በመንታነት ይከሰቱልናል።
ስመ ገናናዋ የዓድዋ መዝሙር እናት እጅጋየሁ ሽባባው እንዲህ የተቀኘችው በከንቱ አይደለም።
በኩራት፣በክብር፣በደስታ፣በፍቅር፣
በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን፤
ደግሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን።
ይህ ድብልቅልቅ ስሜት፣ ረቂቅ ትውስታ ሁለት ገጽታ ያለው የሁሌ ትዝታ፣ መዝሙርና ሙሾ ነው። በጦርነቱ ዕለት እንኳ ከዚያ አስደናቂ ድል በኋላ በዐጼ ምኒልክ፣ በራስ መኮንንና ሌሎችም ጀግኖች ፊትና ልብ ላይ የሚንቀዋለል ስሜት ነበር።
ከዚያ አስደናቂ ድል በኋላ የወደቁት እነ ፊታውራሪ ገበየሁ አባጎራውን የመሳሰሉ ጀግኖች ሞት ለጓዶቻቸው ሕመም ነበር።…ሰው ከፍሎ፣ ውድን ሰጥቶ ሌላ ውድ ነገር መቀበል ቀላል አልነበረም!!
ጀግኖቻችን የዓለም ዕብሪተኛ በስላቅ ምላሱን አውጥቶ እንዳያላግጥብን፣ የተሳለልንን ቢላ ነጥቀው፣ ቀንበሩን ከጫንቃችን የሰበሩት በራሳቸው ደም ነው፤ የድል ዜና ያሰሙን፣ ገድሉን የፈጸሙትና በታሪካችን ላይ ዘውድ የደፉት ከጠላት ጋር ተናንቀው ደምና ላብ ከፍለው ነው።
እናም ዛሬ ሲታሰቡን የማያረጁና በታሪካችን ገጾች የማይደበዝዙ ዝርግፍ ጌጦቻችን ሆነው ነው፤ ስለዚህ ሁሌም እንኮራባቸዋለን።
ታዲያ ይህንን አንገት ቀና የሚያደርግ የነጻነት ተጋድሎ፣ ጭንጫ መሬት ላይ የወደቀ ዘር ሆኖ አልቀረም። ይልቅስ በከያኒዎቻችን ልብ በቅለውና አድገው፣ እሸት ሆነው፣ አብበው ፈክተዋል፤ በዜማ አጊጠው፣ በጥበብ ተቀምመው፣ በልባችን በውብ ቀለም እንደ ጅረት ፈስሰዋል።
ከእነዚህ ድሉ ከወለዳቸው ከያንያን ውስጥ ስለ ዓድዋም ከፍ ባለ ጥበባዊ ቁመና፣ በሠፊ ምናብ ክንፍ ቅኝት የምናደንቃቸው ባለቅኔው ጸጋዬ ገብረመድኅንና እጅጋየሁ ሽባባው፣ ሌሎችም ወጣት ከያንያን አባቶቻችንን ከዘከሩበት ሥራ በጥቂቱ መዳሰስ የወቅቱ ጥያቄና የእኔም ጽሑፍ ዓቢይ ጉዳይ ነው።
በርግጥም ከታሪክ አንጻር የዓድዋን ድል ያህል ግዙፍና ለማንጸሪያነት የሚበቃ ሰማይ ጠቀስ ታሪክ፣ አሻራ ያለው ድንቅ የማይዳሰስ ሐውልት የለንም። ዓድዋ ዓለም አቀፍ ግርማ ያገኘ፣ የታሪክ ሰነዶችን ያጣበበ የዓለማችን ታላቅ ገድል ነው።
ሰለዚህም በየስፍራው በየአገሩ ብዙ ተጽፎለታል፤ ብዙ ተዘምሯል። እኛ ጋ ሲመጣም በያመቱ፣ አንዳንዴም በያጋጣሚው በጥበብ ሰዎች ብዕር ይዘመራል።
ከወጣቶቹ የሆሄ ሥነጽሑፍ ሽልማት የግጥም ዘርፍ የአንደኛው ዙር ተሸላሚ የሆነው ወጣት አበረ አያሌው "ፍርድ እና እርድ" በሚለው መጽሐፉ፣ ስለ ዓድዋ እንዲህ ያለው ለዓለም አቀፋዊነቱ ክብር ይመስለኛል።
አድዋ ሰፈር አይደለም-አድዋ መንደር አይደለም
ሀገር ነው ከነታሪኩ-አህጉር ነው፣ሰ……ፊ ዓለም።
እነምኒልክ ጦር ይዘው-ከመድፍ የተዋደቁ
ጎራዴ መዘው የሮጡ-በጠብ-መንጃ አፍ ያለቁ
ለጓጉለት ነፃነት -ደማቸውን ያፈሰሱ
ለሰፈር ብቻ አይደለም-ያህጉር ድል አታንኳሱ። ይላል።
ይህ ግዝፈቱን ማሳያ ነው። ዓድዋ በርግጥም ሩቅ፣ ለምናብም ልጥጥ ነው። ነግረው አይጨርሱትም፤ አፍሰው በጎተራ አያኖሩትም። እንደ ዋርካ ባለ ብዙ ቅርንጫፍ፣ በእልፍ ቃል የማይገለጥ፣ ከአእምሮ በላይ ነው።
የአንዲት ደሃ ሀገር የገበሬ ጦር ዘመናዊ ስልጠና የወሰደ የአውሮፓዊት ሀገር ጦር አሸነፈ ማለት እንደ ተረት የሚቆጠር ነው።…ግን በእውኑ ዓለም እውን ሆኖ ዓለምን አደናግሯል።
ስለዚህ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ችቦ፣ የአሸናፊነት ማሳያ ፊልም፣ የማይጠበቅ ተዓምር ብንለው ያስኬዳል!

የፎቶው ባለመብት, Chris Hellier
ስመ ጥሩ ከያኒ ቴዎድሮስ ካሳሁንም "ጥቁር ሰው" ብሎ በሰየመው አልበም ስለ ምኒልክ ያቀነቀነው፣ ስለ ቀለሙ ሳይሆን ድንበር የለሽነቱን ለማሳየት ይመስለኛል። ዓድዋ ድንበር የሌለው ድል፣ ጥቁር ሕዝቦችን ከተኙበት ለነጻነት ያባነነ የማንቂያ ደወል ነው።
በርግጥም ያለጥርጥር የዓድዋ ድል ጥቁር ሕዝቦች ለአምባገነን ነጮች "አንገዛም!" በሚል ቁጣ ማንነታቸውን በጦር ፍልሚያ የታደጉበትና ክብራቸውን ያስጠበቁበት ጦርነት የወለደው ተዓምራዊ ገድል ነው።
ወጣት፣ ጎልማሳ፣ ሙስሊም ክርስቲያን ነጻነትን ከሕይወት በላይ የተረጎመበት ዓለም አቀፍ ሰነድ ነው። ስለዚህ ይህንን ድል የኪነጥበቡ ቤት፣ የከያኒው ልብ "እንዴት ዘመረው? እንዴት ዘከረው?" ብሎ መቃኘት ጠቃሚ በመሆኑ ነው እንዲህ የምናየው። ስለዚህም በዚህ የጥበብ ዓለም ቅኝት ዓይኖቻችንን ኩለን የታሪካችንን ሰነድ፣ የሰንደቃችንን ግርማ አጥርተን ልናይ እመኛለሁ።
እናም ወደ መሙ ለመግባት በእጅጋየሁ ስንኞች እጀምራለሁ።
የሰው ልጅ ክቡር፣
ሰው መሆን ክቡር
ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን፤
"ሰው" የሚለው ቃል ሁለንታዊ (Universal) ነው። ዓለምን ሁሉ የሚሞላ ሰፊ ማዕቀፍ ነው፤ "ሰው ክቡር" ስትል ደግሞ የሰው ክብሩ ከነጻነቱ ይጀምራል። በነጻነት መኖር ሰዋዊና ሕሊናዊ ነው። ይህ ሀሳብ የሚወስደን ቶማስ ጀፈርሰን ዋነኛ መርሁ ያደረገው የሰው ልጅ ነጻ ሆኖ የተፈጠረ ፍጡር ነው የሚለውን ጉዳይ አጽንዖት ወደ መስጠት ነው፤ እኔም አባቶቼም፣ ሌሎች ያገሬ ልጆችም በዚህ ስለምናምን ባርነትን እስከ ዛሬ ባርነትን አሻፈረኝ ብለናል።
ዓድዋ የዚያ እምቢታ ማሳያና ውጤት ነው። በገሃድ እንደታየው፣ ለነጻነት ክብር ዓድዋ ላይ "ሰው"ን ሰው ለማድረግ ሰው ሞቷል፤ ለመንፈስ ልዕልና ሕይወቱን በጦር ሜዳ አፍስሷል፤ ደሙን ሜዳ ላይ ደፍቷል።
አዎ፤ በሞት ጥርስ ጫፍ ላይ የተንጠለጠለው የመጨረሻ ተስፋችንን፣ ለማለምለም በቋፍ ላይ የነበረውን ሉዐላዊነታችንን ለማስከበር በጊዜው ቤዛ የሆኑልን አባቶች ሺህዎች ናቸው። እናም ዓድዋ ላይ አንዱ የሌላውን መስቀል ተሸክሞ አልፏል፤ አንዱ ለሌላው ልዕልና ሞቷል። ወርቅ የሆነ ሰው በእሳት አልፎ፣ አፈር ሆኗል፤ ይህ ሁሉ ግን ሌሎችን ወርቅ አድርጎ ለማኖር ነው።
እጅጋየሁ ሽባባው፣
የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት
ትላለች!
ጸጋዬ ገብረመድኅን ደግሞ "እሳት ወይ አበባ" በሚል መጽሐፉ ላይ እንዲህ ይላል፤
ዓድዋ የዘር አፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ስርየት
በደም ለነጻነት ስለት
አበው የተሰውብሽ ለት
ይህም አንጓ ወደ ኋላና ወደፊት የሚያይ፣ የሚያጠንጥን፣ ከመስዋዕትነቱ ሜዳ እስከ ነጻነቱ አፅናፍ የሚተርክ ነው፤ በዚህ አንጓ መስዋዕትነቱ መቆየቱን የሚያሳየው የፈሰሰው ደም ደርቆ ትቢያ ሆኖ፣ ከአፈር ጋር አፈር መሆኑ ነው። የደረቀው ደም ግን ተበትኖ አልቀረም፤ መቀነት ሆኖ ኢትዮጵዊ አንድነታችንን አስጠብቆልናል፤ ሕልውናችንን በታሪክ ዳንዳ ከፍ አድርጎ ሰቅሎታል።
በደም ውስጥ ሕይወት አለ፤ ሕይወት ለነጻነት ተከፍሏል፤ ለባርነት ስርየት ፈስሷል። ምሱን የተቀበለው የዓድዋ ምድር ርስትነቱ ፀንቷል። ቦታው ዓድዋ፣ ኪዳኑ መስዋዕትነት ነው። ሰንደሉ ትውልድ ጤሶ እስከ ዛሬ በሀገርና በዓለም አድማሳት ይናኛል። …ዛሬም ለእኛ የሽቱ ያህል መዓዛ፣ ለማይወዱን ደግሞ የሞት ያህል ክርፋት ሆኖ ይኖራል። አባቶቻችን ጠባሳው ሕመም እንዳይሆን፣ በድል የክብር ቀለም ቀብተው፣ ከፍ አድርገው ሐውልቱን ከታሪክ ጋር ገምደውታል።
ስለዚህም ከያንያኑ ደም ተከፍሎበታል !... ሰው ተከፍሎበታል!... ይሉናል!
ያንን የደም ዋጋ፣ ያንን ታላቅ ተጋድሎ፣ ያንን እንደ ችቦ በታሪክ ውስጥ የሚነድድ ደም እጅጋየሁ ሽባባው እንዲህ ትገልጸዋለች።
በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፤
በክብር ይሄዳል፤ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ።

የፎቶው ባለመብት, David Redfern
ዓድዋ ነፍስን ለሌሎች ነፍስ የመስጠት ተዓምር ነው። ይህንን የሚያደርግ ደግሞ የጀግና ልብ ሩቅ ተመልካች ዓይን ነው። የከበረች ምድሩን አሳልፎ የማይሰጥ፤ የነጻነቱ ትዕምርት የሆነው የባንዲራው ቀለም በልቡ የታተመ፤ ስለዚህ ሕልሙ ሀገሩ ፤ ክብሩም ነጻነቱ የሆነ።
ስለ ወገኖቹ በቋያ እሳት አልፎ፤ ነበልባል ሆኖ ነድዶ ሲያበቃ ነበልባሉን በታሪክ አንገት ላይ የድል ጉንጉን አበባ አድርጎ ያጠለቀ፣ የትዝታውን አመድ በታሪክ ገጾች ላይ ወርቃማ ቀለም አጥቅሶ ያሰፈረ፣ ኩሩ ትውልድ መሆኑን ነግረውናል። ይህንን ደግሞ ሴቶች እናቶቻችን ሳይቀሩ በገቢር አሳይተውታል። በጦር ሜዳ ከተሰለፉት ሌላ ለቁስለኞች ውሃ በማቅረብ፣ ቁስላቸውን በመጠገን፣ አዝማሪዎቹ ጀግኖችን በማደፋፈር፣ ጀግንነታቸውን አሳይተዋል።
ሲጠቀለል የዓድዋ ጦርነት መነሻ ምንጩ "አትንኩን!" ነው። "አትንኩን" ቢሆንማ ቤቱ ተቀምጦ ባልተነካ!..."አትንኩን!" ያለው ግን ትግራይ ያለው ወገኑ ሲነካ ስላመመው ነው፤ ሰሜኑ፣ ደቡቡ፣ ምሥራቁ፣ ምዕራቡ ሲነካ "አትንኩን!" ብሎ በቁጣ ቤቱን ጥሎ ወጥቷል። ይህ ውለታ ያልጠፋት ከያኒ እንዲህ ታቀነቅናለች፡-
የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፣
ስንት ወገን ወደቀ በነጻነት ምድር
ትናገር ዓድዋ ትናገር ትመስክር!
ትናገር ዓድዋ ትናገር ሀገሬ
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ።
. . . በዘይቤ አሽቆጥቁጣ ዓድዋን ለእማኝነት ትጋብዛለች።
በዛሬው የነጻነት ሰንደቅ ስር በሚፍለቀለቅ የነጻነት ዜማ፣ በሀገር አደባባዮች ላይ ለመቆም ትናንት የተከፈለ ውድ ዋጋ አለ። ዛሬ እሸት እሸት ለሚሸትተው ተስፋ ትናንት የከሰለ የወገን አጽም ነበር። በዚያ ዐውደ ውጊያ የብዙ ጀግኖች አጥንት እንደ ችቦ ነዷል፤ ያ የብርሃን ወጋገን ግን ዛሬ በጸና ሥነልቡናዊ ማንነትና ክብር ሁላችንንም አቁሞናል።
እጅጋየሁ ሽባባው ለዚህ ምስክሯ የዓይን እማኟ ዓድዋ ናት እያለችን ነው።... ዓድዋ ተራራው -አድዋ - ሰማዩ ፣ ሰማዩን የሳመው የተራራው ከንፈር … ከውስጡ የሚመነጨው የትዝታ ገሞራ - ፊታውራሪ ገበየሁ - ገብቶ ሲነድድ - መዓዛው ለዛሬ ጣፋጭ- የነጻነት ዜማ … የባርነት ስርየት ነው። የመትረየስ እሳት ምላስ ያነደደው ተራራ፣ አፈሩን የዛቀው መድፍ ግራና ቀኙን የተጎሰመው ነጋሪት ድምጽ ያሸበረው ቁጥቋጦ የተሳከረውን ድብልቅልቅ ዋጋ፣ ስሌቱን የታሪክ ድርሳናት ብቻ ሳይሆኑ ዓድዋ ራሱ ይተርከው ብላለች።
ከያኒዋ "ትናገር … ትናገር! ያለችው በአጽንዖት ነው። ያኔ የነበረችው፣ ዛሬም በጉያዋ ስር ያንን ተዓምር ያቀፈችው እርሷ ናት!... የነደደ ፊቷ … የከሰለ ልቧ … ያንን ጠባሳ በእንባ እያጠቀሰ ሳይሆን በሳቅ እየፈካ ይናገረዋል!... እንባችንን አባቶቻችን አልቀሰው በሳቅ መንዝረው ሰጥተውናል! አፈር ሆነው ወርቅ አውርሰውናል!
ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን እንዲህ ይላል፤
ዓድዋ ሩቅዋ
የአለት ምሶሶ አድማስ ጥግም
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
የማይፈርስ ምሶሶ አድርገዋት ያለፉት፣ የማይደረስበት አድማስ አድርገው ታሪኳን የጻፉት ኩሩ ትውልድ ነበሩ። እንደ ጧፍ የነደዱ የማይገሰስ ክብር፣ የማይናድ ገድል ጽፈው ያለፉ!...እነዚህ ጀግኖች ግን በየአቅጣጫው የተመሙት ሞተው እናን በክብር ለማኖር ነው።
እናም እጅጋየሁ ሽባባው ዓድዋን እንዲህ ታሞካሻታለች፤
ዓድዋ ዛሬ ናት ዓድዋ ትናንት
መቼ ተረሱና የወዳደቁት
ምስጋና ለእነሱ የዓድዋ ጀግኖች
ለዛሬ ነጻነት ላበቁኝ ጀግኖች
የጥቁር ድል አምባ ዓድዋ
አፍሪካ እምዬ ኢትዮጵያ
ተናገሪ የድል ታሪክ አውሪ
ስለ ዓድዋ በዜማ አቀንቅና አላበቃችም፤ ስለ ዋነኞቹ ጀግኖች አውስታለች፤"ምስጋና!" ብላ የክብር ዘውድ ደፍታላቸዋለች፤ አበባ ጉንጉን አጥልቃላቸዋለች፤ ሻማ ለኩሳለች።
የስንኟ ጅማሬ ከሰው ልጅ ጥቅም ተነስቶ ወደ ጥቁር ሕዝቦች ከዚያም ወደ አፍሪካ አፍንጫ ደርሷል፤ የድሉን አበባ እያሸተተች፣ ጀግኖች በነሰነሱት የነጻነት ጉዝጓዝ በክብር አዚማለች። ኢትዮጵያ የአፍሪካ - የጥቁር ሕዝቦች ከፍታ ችቦ ለኳሽ!...
ጋሽ ጸጋዬም
ዋ!... ዓድዋ
ያንቺን ጽዋ ያንቺን አይጣል
ማስቻል ያለው አባ መቻል
በዳኘው ልብ በአባ መላው
በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ናፍስ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ፤ በለው በለው
ጸጋዬ ወደ ሽለላና ቀረርቶ ይሻገራል፤ ጀግኖቹን በፈረሳቸው ስም እየደጋገመ በሽለላና ቀረርቶ ቃና - "በለው በለው!" ይላል፤ ያንን የትንቅንቅ ቀን፣ ያንን የመስዋዕትነት ምድጃ፣ ያንን ጀግኖች የጨሱበትን ደመራ ያወዛውዛል - ዓድዋ!...
ዓድዋ የጀግኖች ቃል ኪዳን ውርስ! ወርቅ አፈር ሆኖ፣ወ ርቅ የተወለደበት ማሕጸን!!
*ደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ ከዚህ ቀደም ዘጠኝ የግጥም፣የወግ እና የልብ ወለድ ሥራዎች አሳትሟል። በተለያዩ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ላይ ሂሳዊ ዳሰሳ በማቅረብም ይታወቃል። በቅርቡም "ኂሳዊ ዳሰሳ" የተሰኘ የተለያዩ ሥነ ጽሁፋዊ ሂሶችን የያዘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል።















