ሃጫሉ ሁንዴሳ፡ ለብዙሃኑ ድምጻዊ ለሌሎች ደግሞ 'ዐይን' የነበረው ሃጫሉ

ሃጫሉ

የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ዓመቱ ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት ሲቀሩ የተከሰተ ቢሆንም ከቤተሰቦቹ ጀምሮ በሌሎች በርካታ ግለሰቦች ህይወት ላይ ካስከተለው ከባድ ሐዘን በተጨማሪ በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ ጉልህ የሚባል ነው።

ከዚህ አንጻር የሃጫሉ መገደልና እሱን ተከትሎ የተከሰተው አለመረጋጋት የብዙዎችን ሕይወት አናግቶ በሽግግር ላይ የሚገኘውን የአገሪቱ ፖለቲካንም ወደ ቀውስ መርቶታል። በዚህም በርካታ ሰዎች ለእስር ተዳርገው ዓመቱ ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል።

ቢቢሲም ይህንን ጉልህ የዓመቱ አስደንጋጭ ክስተትን ሲዘክር ስለወጣቱ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ብዙም ያልተነገሩ ጥቂት ነገሮችን ለመቃኘት ሞክሯል።

መስመር

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም. ምሽት 3፡30 ገዳማ በጥይት ተመትቶ ተገደለ።

የሃጫሉ ግድያ በርካቶችን ያስደነገጠ፣ ያሳዘነ እና ያስቆጣ ነበረ።

የድምጻዊውን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው አለመረጋጋት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ንብረት ወድሟል። በሺዎች የሚቆጠሩም ለእስርና መፈናቀል ተዳርገዋል።

የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በ2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ከተፈጠሩ አነጋጋሪ ጉዳዮች መካከል አንዱ በመሆን አልፏል።

በዚህ ዘገባ ውስጥም ስለ ድምጻዊ ሃጫሉ የሙዚቃ እና ህይወት ያልተሰሙ እውነታዎችን እንደሚከተለው ለመቃኘት ወደድን።

ከልጅነቴ ጀምሮ አፌ እረፍት የለውም ነበር . . .

1976 ዓ.ም. የተወለደው አርቲስት ሃጫሉ፤ ትውልድ እና እድገቱ ምዕራብ ሸዋ አምቦ ከተማ ነው።

ዘጠኝ ወንድም እና እህት ያለው ሃጫሉ፤ ከአብሮ አደግ ጓደኞቹ ጋር ከብት በመጠበቅ ነው ያደገው።

በሙዚቃ ፍቅር ገና በልጅነቱ እንደወደቀ የሚናገረው ሃጫሉ፤ "እዘፍናለሁ፣ ከልጅነቴ ጀምሮ አፌ እረፍት የለውም ነበር" ብሎ በአንድ ወቅት ተናግሯል። በትምህርት ቤት የሙዚቃ ክበብ አባል በመሆን ይዘፍን ነበር።

ወላጅ አባቱ አቶ ሁንዴሳ ግን በዚህ ደስተኛ አልነበሩም። "አባቴ ዶክተር ወይም ፕሮፌሰር እንድሆን ነበር የሚፈልገው። 'ዘፋኝ ትዳር አይመሰርትም' ይላል" ሲል ሃጫሉ በአንድ ወቅት ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

እስር በልጅነት

ሃጫሉ ገና የ17 ዓመት ታዳጊ ሳለ ያጋጠመው ነገር ህይወቱን የቀየረ አጋጣሚ ሆኗል።

በ1995 ዓ.ም. ላይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የነበረው ሃጫሉ ክስ ሳይመሰረትበት፣ ጥፋተኛ ሳይባል አምስት ዓመታት በአምቦ 'ከርቸሌ' በእስር አሳልፏል።

እርሱ እና ጓደኞቹ ከአምስት ዓመታት እስር በኋላ "ነጻ" ተብለው መሰናበታቸውን ሃጫሉ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግሯል።

እስር ቤት ሳለ ግን የሙዚቃ ክህሎቱን እንዲያሳድግ መልካም አጋጣሚ ሆኖ እንዳለፈ በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል። "ከዚያ ቀደም መዝፈን እንጂ ግጥም እና ዜማ ለመጻፍ ሞክሬ አላውቅም ነበር" ያለው ሃጫሉ፤ ግጥም እና ዜማ መጻፍ የጀመረው የአምቦ ከርቸሌ ታሳሪ ሳለ ነበር።

የአዲስ ዓመት ልዩ ጥንቅር

የሃጫሉ የሙዚቃ ሕይወት

ሃጫሉ "ሰኚ ሞቲ" እና "ዋኤ ኬኛ" የተሰኙ ሁለት የሙዚቃ አልበሞችን ለአድማጭ ጆሮ አብቅቷል። ከአልበሞቹ በተጨማሪ ግን የለቀቃቸው ነጠላ ዜማዎች እጅግ ተወዳጅ ሥራዎቹ ሆነዋል።

ከአምስት ዓመታት በፊት 'ማለን ጅራ?' [ምኑን አለሁት?] በሚል ለሕዝብ ያበቃው ነጠላ ዜማ የኦሮምኛ ቋንቋን በማይችሉት ዘንድ ሁሉ ተወዳጅ ሆኖለታል።

ሃጫሉ ይህን ሙዚቃ የሰራው በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው የመሬት ወረራ እጅጉን ስላሳሰበው መሆኑን ለቢቢሲ እንዲሁም ለሌሎች መገናኛ ብዙሃን ተናግሮ ነበር።

'ማለን ጅራ' የሚለው ነጠላ ዜማ ለህዝብ ጆሮ ከበቃ ከሁለት ዓመታት በኋላ፤ 'ጅራ ጅራ . . .' [አለን አለን . . . ] የተሰኘውን ሌላ ተወዳጅ ሥራውን ለአድናቂዎቹ አቅርቧል።

በቀደመ የነጠላ ዜማ ሥራው 'ምኑን አለሁት' ያለው ሃጫሉ 'ጅራ ጅራ . . .' በሚለው የነጠላ ዜማው ደግሞ በአገሩ ያለውን ተስፋ ያንጸባረቀበት ነበር።

ሃጫሉ ከመገደሉ በፊት በኦኤምኤን ቴሌቪዥን ላይ ባደረገው ቃለ መጠይቅ ላይ ለሕዝብ ጆሮ ያልደረሱ የተለያዩ ሥራዎች እንዳሉት ተናግሮ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ከ7 ያላነሱ የሙዚቃ ሥራዎች በተለያዩ ስቱዲዮች ውስጥ እንደሚገኙ፤ እንዲሁም የቤተሰብ አባላትና ጓደኞቹ ከሚመለከታቸው ጋር ተወያየተው በአልበም መልክ ለአድናቂዎቹ ለማቅረብ ሃሳብ እንዳላቸውም ቢቢሲ መረዳት ችሏል።

ሃጫሉ

ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን እና ሃጫሉ

ሃጫሉ ከገጣሚ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ጋር የቅርብ የሥጋ ዝምድና እንዳላቸው ከዚህ ቀደም ተናግሯል።

"ኦሮሞነትን እና ኢትዮጵያዊነትን አጣጥሞ መሄድ እንደሚቻል ከሎሬት ጸጋዬ ተምሬያለሁ" በማለት ሃጫሉ በተደጋጋሚ ሲናገርም ተደምጧል።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን የባህል ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ለይኩን ሃጫሉ እና ሎሬት ጸጋዬ "ለሞት ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው" ይላሉ።

በሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን አስተሳሰብ ላይ መሠረት ያደረጉ የሃጫሉ ሥራዎች መኖራቸውንም የማዕከሉ ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ይናገራሉ።

ለማሳያም የሎሬት ጸጋዬን 'የት አባቱ ሞትም ይሙት' የሚለውን ግጥም ያስታውሳሉ።

እባካችሁ ዘመዶቼ

ስሞት ሞትም አብሮኝ ይሙት

በሳቅ በደስታ ግደሉት

በሃሴት በእልልታ ወግሩት

ካጥንቴ በታች ቅበሩት

እባካችሁ ዘመዶቼ ለሞት የልብ ልብ አትስጡት ይላል የሎሬቱ ግጥም።

ሃጫሉም በሙዚቃ ሥራዎቹ 'ከእኔ በኋላ ትውልድ አለ'፣ 'የሞት ፍርሃት አምቦ ከርቸሌ ተቀብሯል' የሚሉ ይዘት ያላቸው የሙዚቃ ሥራዎች እንዳሉት ያመለክታሉ።

ሃጫሉ በፖለቲካ አቋሙ እና በሙዚቃ ሥራዎቹ ምክንያት፣ ከተለያዩ አካላት ማስፈራሪያዎች እና የግድያ ዛቻዎች ይደርሱበት እንደነበረ በተደጋጋሚ ተናግሯል።

በዚህም ከአገር እንዲወጣ በተለይ ወላጅ እናቱ በተደጋጋሚ ሲጠይቁት፤ "ምነው የእኔን ሞት ምን የተለየ ያደርገዋል? ቆሜ እቀራለሁ እንዴ?" እያለ ይመልስላቸው እንደነበረ ወላጅ እናቱ ይናገራሉ።

"ውለታሽ በዛብኝ"

ሃጫሉ ትዳር የመሰረተው እና ሦስት ልጆችን የወለደው የልጅነት ፍቅረኛውን አግብቶ ነበር። ሃጫሉ ለውድ ባለቤቱ ፋንቱ ደምሴ፤ "ውለታሽ በዛብኝ" ሲልም ተቀኝቶላታል።

ሃጫሉ እና ፋንቱ ፍቅር የጀመሩት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሃጫሉ ለእስር ተዳረገ።

ፋንቱ ለእስር የተዳረገ እጮኛዋን ከቤተሰብ ተደብቃ፣ ስንቅ በመቋጠር በየዕለቱ ትጎበኘው እንደነበረ የሃጫሉ ጓደኞች ይናገራሉ።

ሃጫሉም በሙዚቃው "ችግር እና መከራን አብረሽኝ ላየሽው . . . ውለታሽን ለመመለስ አቅም የለኝም። ህይወቴ አልፎ ከመድረ ገጽ ብጠፋም መቼም አልረሳሽም" ሲል ለፋንቱ ተቀኝቷል።

ሃጫሉ በሚያደርጋቸው ቃለ መጠይቆቹ ሁሉ ስለ ሚስቱ ተናግሮ አይጠግብም፤ "በእርሷ ሁሉም ይሳካልኛል። በጣም ነው የምወዳት" ሲል ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

ሃጫሉ የቤተሰብ ዐይን ነበር

ሃጫሉ ለብዙሃኑ ድምጻዊ ነበር። ለአንዳንዶች የነጻነት ታጋይ ለቤተሰቡ ግን "ዐይን" ነበር።

አቶ ሁንዴሳ ቦንሳ ልጃቸውን ሲያስታውሱ "ልጄ ጀግና ነው። ለእውነት ይሞታል" ይላሉ።

"ሃጫሉ ከልጅነቱ ጀምሮ ጀግና እና ደፋር ነበረ። ውሸት አይወድም። እውነት ነው የሚወደው፤ የሚሞተውም ለእውነት ነው" የሚሉት የሃጫሉ ወላጅ አባት አቶ ሁንዴሳ ቦንሳ፤ ሃጫሉ ለሞት የተዳረገው ለወገኑ በመቆርቆሩ እና "ያገባኛል" በማለቱ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሃጫሉ እናት ወ/ሮ ጉደቱ ደግሞ "ልጄ ገና ከልጅነቱ አስተዋይ ነበር" ይላሉ።

"ልጄ በእኔ ነበር የሚምለው" የሚሉት ወ/ሮ ጉደቱ ለሃጫሉ ልዩ ፍቅር እንዳላቸው ይናገራሉ። የሃጫሉ ታላቅ ወንድም የሆነው ሃብታሙ ሁንዴሳ በበኩሉ፤ ሃጫሉ ለሰው ፍቅር ያለው እና በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ እንደበረ በማስታወስ፤ "ሃጫሉ ለቤተሰቡ ዐይን ነበር" በማለት ይናገራል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, "ልጄ የሞተው ለእውነት ነው"

የሃጫሉ የመገደል ዜና

ሰኔ 22 ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ገላን ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በጥይት ተመትቶ መገደሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ከእኩለ ለሊት በኋላ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ሰኔ 25/2012 ዓ.ም. የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የቀብር ሥነ ሥርዓት በአምቦ ከተማ በሚገኘው የገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተፈጽሟል።

የሃጫሉ ግድያ በቤተሰቦቹና በአድናቂዎቹ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል። አስካሁንም ይኽው ስሜት ከአገሪቱ አየር ላይ ቀለል ሳይል ዓመቱ ሊጠናቀቅ ነው።

የሃጫሉ መገደልን ተከትሎ በአገሪቱ የተከሰተው አለመረጋጋት የበርካቶችን ህይወት ከመቅጠፉ በተጨማሪ የአካል ጉዳትንና የንብረት ውድመትን አስከትሏል። ግድያው በአገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት ላይም በዓመቱ ከተከሰቱት ሁሉ ትልቅ ተጽእኖ የነበረው ክስተት ሆኖ አልፏል።