የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋዮች 'በጥቂት ቀናት' ውስጥ ወደ መቀለ ሊያመሩ ነው

ኡሁሩ ኬንያታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የሚካሄደውን ድርድር የሚመሩት የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋዮች በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ መቀለ እንደሚያመሩ ተገለጸ።

የኅብረቱ አደራዳሪዎች ወደ ትግራይ የሚያቀኑት ከሳምንታት በፊት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረሰውን ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት አፈጻጸምን ለመታዘብ መሆኑን የቡድኑ አባል የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ሁለቱን ወገኖችን ሲያደራድሩ የነበሩት ፕሬዝዳንቱ እያበቃ ያለው የፈረንጆቹ ወር ከመጠናቀቁ በፊት ባሉት 8 ቀናት ውስጥ ወደ ትግራይ ሊያምሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ኡሁሩ በየትኛው ቀን ወደ መቀለ እንደሚጓዙ ሲጠየቁ፤ “ቁርጥ ያለ ቀን መናገር አልፈልግም፣ ነገር ግን በዚህ ወር መጨረሻ እንበል። ለዚያ ነው በጥቂት ቀናት ውስጥ ያልኩት” ሲሉ መልሰዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች ለሁለተኛ ጊዜ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ላይ ከረቡዕ ታኅሣሥ 12/2015 ዓ.ም. ጀምሮ እያደረጉት ያለው ውይይት ስኬታማ መሆኑን ኬንያታ ተናግረዋል።

የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች ባልተገኙበት በኡሁሩ ኬንያታ የተመራው የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች ሐሙስ ማምሻውን እየተካሄደ ስላለው ውይይት መግለጫ ሰጥተዋል።

ኬንያታ እየተካሄደ ባለው ውይይት “ከፍ ያለ ውጤት” መታየቱን እና በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ለማስፈን “በትክክለኛው አቅጣጫ እየተጓዝን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የሰላም ስምምነት አፈጻጸም

ረቡዕ እና ሐሙስ ታኅሣሥ 12 እና 13/2015 ዓ.ም. የሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ ጦር አዛዦች ለሁለተኛ ዙር በናይሮቢ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ከአንድ ወር በፊት በመንግሥት እና በህወሓት መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተገዢ በመሆን የስምምነቱን አፈጻጸም በጋራ ለመቆጣጠር እና ለማረጋገጥ በሚያስችሉ የመከታተያ ነጥቦች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።

ሁለቱ አካላት ከስምምነት መድረሳቸውን ይፋ ያደረገው የእርሰ በርስ ጦርነቱ በንግግር እንዲፈታ ድርድሩን በበላይነት ሲመራ የቆየው የአፍሪካ ኅብረት ነው።

ኅብረቱ ከሁለተኛው ዙር የናይሮቢ ውይይት በኋላ ባውጠው መግለጫ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ የሚፈቱበትን አፈጻጸም ተነጋግረዋል ብሏል።

የአፍሪካ ኅብረት በሁለቱ አካላት መካከል እያደረገ ያለው አዎንታዊ መተማመን የሚበረታታ ነው ያለ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች በኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት በጥራታቸው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።

የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት ከፍተኛ የጦር አመራሮች ያደረጉት ይህ ውይይት የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነትን በድርድር ለመቋጨት የተደረገው ሦስተኛ ዙር ንግግር ነው።

ፕሪቶሪያ እና ናይሮቢ

በህወሓት እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል ለሁለት ዓመት የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ወሳኝ የተባለው ግጭት የማቆም ስምምነት መፈፈሙ ይታወሳል።

በዚህ ስምምነት በሁለቱ ወገኖች መካከል ግጭት ለማቆም፣ ሰብአዊ እርዳታ ማቅረብ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች ማስጀመር እና የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ ማስፈታት ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።

ከዚያም በመቀጠል የዚህ የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ላይ የሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች የጦር አዛዦች ናይሮቢ ላይ ንግግር አድርገው ከስምምነት ደርሰው ነበር።

የአሁኑ ሦስተኛው ዙር ውይይት እንደ ከዚህ ቀደሞቹ በዝግ የተደረገ ሲሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ)፣ የአሜሪካ መንግሥት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነውበታል።

የስምምነቱ ሂደት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ግጭት በማቆም የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ፣ የውጪ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ፣ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያፈልጋቸው እንዲደርሳቸው እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን በትግራይ ማስጀመር ተስማምተው ነበር።

ስምምነቱ ከተደረሰ ሁለት ወራት ሊደፍን ጥቂት ጊዜ የቀረው ሲሆን፣ ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል በአንደንዶቹ አዎንታዊ እርምጃዎች ሲታዩ በሌሎቹ ደግሞ የተጠበቀው እንዳልተፈጸመ ለቱም ወገኖች ሲናጋሩ ቆይተዋል።

እንደ ቴሌኮም፣ የባንክ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በተመለከተ ለውጦች እየታዩ ነው። መቀለን ጨምሮ አንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች ከረጅም ጊዜ በኋላ ዳግም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅቦት ማግኘት ጀምረዋል። የስልክ ግንኙነት ቢሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ዳግም መሥራት ጀምሯል።

ወደ ትግራይ የሚገባውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅቦት በተመለከተ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መሻሻሎች ቢኖሩም ከእርዳታ ፈላጊው ቁጥር አንጻር ሲታይ ግን በቂ አለመሆኑን የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኦቻ ከቀናት በፊት መግለጹ ይታወሳል።

ለውጥ ካልታየባቸው ጉዳዮች መካከል የውጪ ኃይሎች ከትግራይ መውጣት የሚለው ይገኝበታል።

ህወሓት እና የፌደራል መንግሥቱ በደቡብ አፍሪካ በደረሱት የሰላም ስምምነት መሠረት የኤርትራ ኃይሎች ከኢትዮጵያ የሚወጡት ከህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ መፍታት ጋር ጎን ለጎን ነው።

የትግራይ ኃይሎች ከአውደ ወጊያ እየለቀቁ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ የኤርትራ ሠራዊት ግን ከትግራይ አለመውጣቱን በትግራይ ባለሥልጣናት በኩል ባለፉት ሳምንታት በተደጋጋሚ ሲሰማ ቆይቷል። በህወሓት በኩል ደግሞ ተዋጊዎቹ ትጥቅ መፍታት ስለመጀመራቸው የተባለ ነገር የለም።

አሁን ናይሮቢ ላይ የተደረገው ውይይት ቀደም ባሉት ውይይቶች ከስምምነት የተደረሰባቸው ተግባራዊነታቸውን ለመከታተል ያስችላል ተብሎ ይታመናል።