በእስያ አገራት ዋነኛው ዕጽ አዘዋዋሪ ትውልደ ቻይናዊ ለአውስትራሊያ ተላልፎ ተሰጠ

ትሲ ቺ ሎፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ በእስያ አገራት በጥብቅ ከሚፈለጉት ተጠርጣሪዎች መካከል ቀዳሚ የነበረው ግለሰብ ኔዘርላንድስ ውስጥ ከተያዘ በኋላ ለአውስትራሊያ ተላልፎ ተሰጠ።

ግለሰቡ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የዕጽ ንግድ ከእስያ አገራት እስከ ኒው ዚላንድ ድርስ ያከናውን ነበር።

ትሲ ቺ ሎፕ በአውስትራሊያ በቀረቡበት ክስ የዕድሜ ልክ እስራት ሊጠብቀው ይችላል ተብሏል።

ትሲ ቺ ሎፕ የተባለው የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ዝናው እና ሃብቱ ናኝቶ ከሜክሲኳዊው ኤል ቻፖ ጋር በርካቶች ያነጻጽሩታል።

በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ በእስር ላይ የሚገኘው ጆኣኪን ኤል ቻፖ ጉዝማን በዓለማችን ኃያሉ የዕጽ አዘዋዋሪ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።

በእስያ ውስጥ 70 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን የሚያካሂድ ኩባንያ የነበረው ሰው ባለፈው ዓመት ነበር በኢንተርፖል አማካይነት በአምስተርዳሙ ሺሎፕ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።

ትውልደ ቻናዊው ግለሰብ ወደ ካናዳ ለመብረር ሲል ነበር በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው።

አውስትራሊያ ግለሰቡ ተላልፎ እንዲሰጣት እና የፍርድ ሂደቱም በአውስትራሊያ እንዲካሄድ ለሁለት ዓመታት ካደረገችው ሕጋዊ ጥረት በኋላ ተላልፎ ተሰጥቷል።

የአውስትራሊያ ፖሊስ ግለሰቡ እጁ በካቴና ታስሮ እና በታጠቁ የፀጥታ ሰዎች እየተመራ ሜልበርን አየር ማረፊያ ከአውሮፕላን ሲወርድ የሚያሳይ ምስል አጋርቷል።

የ59 ዓመቱ ግለሰብ 'ሳም ጎር ሲንዲኬት' የተሰኘ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ የሚንቀሳቀስ ኩባንያ መሪ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ የአውስትራሊያ ፖሊስ አገሬ ለሚገቡት አደንዛዥ ዕጾች 70 በመቶ ይህ ጉባንያ ተጠያቂ ነው ይላል።

ይህ ቡድን በተለይ ሜታአምፊታሚን በብዛት እንዲሁም ሄሮይን በሻይ ቅጠል ከረጢት አድርጎ ወደ አውስትራሊያ ሲልክ ነበር።

ይህ ግለሰብ ሜታአምፌታሚን ተብሎ ከሚጠራው አደንዛዥ ዕፅ ሽያጭ ብቻ 17 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እአአ 2018 ማግኘት እንደቻለ ይገመታል።

ፖሊስ የግለሰቡ መኖሪያ ነው ባለው ሜልበርን ከተማ በሚገኝ ቤት ላይ ባደረገው ብርበራ 4 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር በጥሬ ያገኘ ሲሆን፣ 99 በዲዛይነር የተሰሩ ቦርሳዎች እና ላምቦርጊኒ የተሰኘ ቅንጡ መኪና አግኝቶ ነበር።

ግለሰቡ የሚቀርቡበትን ክሶች ያጣጥላል። እርሱ እንደሚለው ከሆነ እስሩ በአውስትራሊያ ባለሥልጣናት የተቀነባበረ ሲሆን፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ከታይዋን ወደ ካናዳ ተገዶ ሲሄድ ኔዘርላንድስ ላይ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ቀድመው አሲረዋል ብሏል።

ይህ ዕጽ አዘዋዋሪ ለመያዝ የተደረገው ዘመቻ በአውስትራሊያ ፖሊስ እየተምራ 20 የፀጥታ ተቋማትን አሳትፎ ነበር።

ግለሰቡ በቅርብ ዓመታት በማካዎ፣ ሆንግ ኮንግ እና ታይዋን እየኖረ እንደነበረ መረጃዎችን ይጠቁማሉ።

ትሲ በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ከዕጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ ወንጀል በአሜሪካ ለዘጠኝ ዓመታት ታስሮ ነበር።