በጋምቢያ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት መክሸፉ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጋምቢያ የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት ማክሸፉን የሃገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።
ከሙከራውም ጋር ተያይዞ አራት ወታደሮች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ሶስት ተባባሪ የተባሉትም በሽሽት ላይ መሆናቸውንም መግለጫው አመልክቷል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ጋምቢያን ለመምራት ያሸነፉትን ፕሬዚዳንት አዳማ ባሮው ከስልጣን ለማውረድ ከተደረገው የማክሰኞው መፈንቅለ መንግሥት ጀርባ ማን እንዳለ እስካሁን ግልጽ አልተደረገም።
ጋምቢያ በምዕራብ አፍሪካ ካሉ ሃገራት የተረጋጋች ስትሆን በባህር ዳርቻዎቿ እና በዱር አራዊቷም ምክንያት ለመዝናኛነት ከሚመረጡትም ስፍራም አንዷ ናት።
በአሁኑ ወቅት ዋና ከተማዋ ባንጁል ሰላማዊ እንደሆነችና ኑሮም እንደተለመደው መቀጠሉም ተገልጿል።
ምንም አይነት የተኩስ ድምጽ ያልተሰማም ሲሆን ጦሩም የሃገሪቱን ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን ለማስጠበቅ መሰማራታቸውን የሚያሳይ ምልክት የለም።
የመንግሥት መግለጫ በበኩሉ ኃገሪቱ ያላት ተጠባባቂ ጦር በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን ገልጿል።
“ሁኔታው ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራችን ስር ነው” ሲልም አክሏል መግለጫው
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጓል የሚል ወሬ በተሰማበትም ወቅት ጦሩ ወታደራዊ “ ልምምድ” እያደረገ እንደሆነ በመግለጽ አስተባብሏል።
ሃገሪቷን እየመሯት ያሉት ፕሬዚዳንት አዳማ ባሮው በአውሮፓውያኑ 2016 ለረዥም ጊዜ ሃገሪቷን የመሩትን ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህን በርካቶችን ባስደነገጠ ሁኔታ ማሸነፋቸው ይታወሳል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃሜህ ከአፍሪካ ትንንሽ ሀገራት አንዷ በሆነችው በጋምቢያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው ቢቆዩም በአሁኑ ወቅት በኢኳቶሪያል ጊኒ ለስደት ተዳርገዋል።
ባሮው ስልጣን መቆጣጠራቸውን ተከትሎም የሃገሪቱ ከፍተኛ መኮንኖች ከጦሩ ለቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ በጦሩ ላይ ያላቸውን እምነት ያጡ ሲሆን የግል ደህንነታቸውን የሚጠብቁት ከጎረቤት ሴኔጋል የመጡ ወታደሮች ናቸው። በተጨማሪም ዋናው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና የባህር ወደብ በናይጄሪያ እና በጋና ወታደሮች ይጠበቃሉ።












