ባይደን በጦርነቱ ዩክሬን መቼም ብቻዋን እንደማትሆን ለዜለንስኪ አረጋገጡላቸው

ፕሬዚዳንት ዜለንስኪና ባይደን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከሩሲያ ጋር በሚደረገው ጦርነት አሜሪካ ከዩክሬን ጎን እንደምትቆም ለዜለንስኪ አረጋገጡላቸው።

ፕሬዚዳንቱ “የፈጀውንም ያህል ጊዜ ቢፈጅ” አሜሪካ ከጎናችሁ ናት ብለዋቸዋል።

ሩስያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የመጀመሪያ የባህር ማዶ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ አገራቸው ዩክሬን “ብቻዋን እንደማትሆንም” ነው ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት የተነገራቸው።

በዋሽንግተን ለሚገኙት ዜለንስኪ ከአሜሪካ የ2 ቢሊዮን እርዳታ የተለገሰላቸው ሲሆን ተጨማሪ 45 ቢሊዮን ዶላርም ቃል ገብተውላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ዜለንስኪም ከአሜሪካ ለተሰጣቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

ረቡዕ ዕለት በተካሄደው የጋራ መግለጫም ላይ ፕሬዚዳንት ባይደን ለዩክሬን ያለውን ዓለም አቀፍ ጥምረት የመቀጠሉ ጉዳይ “አሳሳቢ አይደለም” ብለዋል።

አንዳንድ አጋሮቹ ጦርነቱ ያስከተለው የዋጋ ግሽበት እንዲሁም የዓለም የምግብ ስርጭትና ኃይል አቅርቦት መስተጓጓል ለዩክሬን የሚደረገው ትብብርን ያከስመዋል የሚል ስጋት ቢኖራቸውም ፕሬዚዳንት ባይደን በዚህ አይስማሙም።

ባይደን የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ይህንን “ደም አፋሳሽ ጦርነት የማስቆም አላማ የላቸውም” ሲሉም ወቅሰዋቸዋል።

የዩክሬን ዋነኛ አጋር አሜሪካ ከዚህ ቀደም 50 ቢሊዮን እርዳታ የለገሰች ሲሆን ለሰብዓዊ እና ደህንነትን የሚሸፍን ነው። አሜሪካ ከማንኛውም ሃገር በላቀ ዩክሬንን በከፍተኛ ሁኔታ እየደገፈቻት ትገኛለች።

የወታደራዊ መለዮቻውን ለብሰው በአሜሪካ የታዩት ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ የአሜሪካ ምክር ቤት ለዩክሬን ተጨማሪውን 45 ቢሊዮን እርዳታ እንደሚያጸድቅም ተስፋቸውን ገልጸዋል። ይህም “ እሴቶቻችንን፣ ነጻነታችንን” እንድንጠብቅ ይረዳናል ሲሉም ተሰምተዋል።

ሪፐብሊካኖች በጥር ወር የአሜሪካውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበላይነት የሚቆጣጠሩት ሲሆን ለዩክሬን ዝም ብለው ድጋፋቸውን እንደማይቀጥሉ አስጠንቅቀዋል።

ነገር ግን ከፖላንድ ሬዝዞው ከተማ በአሜሪካ አየር ኃይል የተጓዙት ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ “በምክር ቤቱ ምንም አይነት ለውጥ ቢኖርም” ለአገራቸው የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥል እምነታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።