ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለኢትዮጵያ ያጯቸው አምባሳደር ማን ናቸው?

ኧርቪን ጆዜ ማሲንጋ

የፎቶው ባለመብት, STATE DEPARTMENT

የምስሉ መግለጫ, ኧርቪን ጆዜ ማሲንጋ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጉዳይ አስፈጻሚ ደረጃ የሚገኘውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲን የሚመሩ ከፍተኛ ዲፕሎማትን በዕጩነት ማቅረባቸውን ጽሕፈት ቤታቸው ገልጿል።

ፕሬዝዳንት ባይደን አገራቸውን በመወከል በተለያዩ አገራት የሚያገለግሉ በርካታ ዲፕሎማቶችን በእጩነት ባቀረቡበት ዝርዝር ውስጥ በኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሆኑላቸው ኧርቪን ጆዜ ማሲንጋን ማቅረባቸውን ዋይት ሐውስ አስታውቋል።

የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ባወጠው መግለጫ ላይ አገራቸውን በተለያዩ አገራት፣ ዓለም አቀፍ እና ቀጠናዊ ተቋማት ውስጥ በመወከል፣ የባይደን የአስተዳደር ቁልፍ አመራሮች ሆነው እንዲያገለግሉ ያጯቸውን ግለሰቦች ይፋ አድርገዋል።

በዚህም መሠረት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ እና በተለያዩ አገራት በዲፕሎማትነት ያገለገሉት ኧርቪን ጆዜ ማሲንጋን የአህጉራዊው ድርጅት መቀመጫ በሆነችው በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያው ሪፐብሊክ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው እንዲሠሩ በዕጩነት አቅርበዋቸዋል።

ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ አሜሪካ በአዲስ አበባ የነበሯታን አምባሳደሯን በማንሳት ለኤምባሲዋ ጊዜያዊ ጉዳይ አስፈጻሚ መሰየሟን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።

በወቅቱም የነበሩትን አምባሳደር ጊታ ፓሲን በጊዜያዊነት በመተካት በኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግሥት ጊዜያዊ ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው እስካሁን እያገለገሉ ያሉት ዲፕሎማት ትሬሲ አን ጃኮንሰን ናቸው።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል የነበረው ግንኙነት ሻክሮ የቆየ ሲሆን፣ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ከነበራት ግንኙነት አንጻር የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዷ ይታወሳል።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላም በተለይ የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተል የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክኛ ሰይማ በኃላፊነቱ ላይ ሦስት ጉምቱ ዲፕሎማቶች ሲሠሩ ቆይተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኧርቪን ጆዜ ማሲንጋ ሰፊ ልምድ ያላቸው ሙያተኛ ዲፕሎማት ሲሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ በአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ውስጥ ተቀዳሚ ምክትል ረዳት ኃላፊ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ።

ማሲንጋ ቀደም ሲል በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ በተለያዩ የአፍሪካ እና የእስያ አገራት በተለያዩ የዲፕሎማቲክ ደረጃ እና ኃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በተለይ የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው ሱዳን ምክትል አምባሳደር እንዲሁም በቻይና የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።

ፈረንሳይኛ፣ ስፓኒሽ እና ማንዳሪን ቋንቋዎችን የሚያውቁት ኧርቪን ጆዜ ማሲንጋ የመጀመሪያ ዲግሪ በውጭ ግንኙነት እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ በሕዝብ አስተዳደር እንዳላቸው ከዋይት ሐውስ የወጣው መረጃ ያመለክታል።

ለአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት የምትሰጠው አሜሪካ ለሁለት ዓመት የዘለቀውን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማብቃት በተደረገው ጥረት ውስጥ በልዩ መልዕክተኛዋ ማይክ ሐመር አማካይነት ቁልፍ ሚና እንደተጫወተች ይነገራል።

ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን ለወራት የዘለቀ ጥረት ያደረገችው አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ጦርነቱን ያስቆመው የሰላም ስምምነት በመፈረሙ ደስታዋን የገለጸች ሲሆን አፈጻጸሙንም በቅርበት እየተከታተለች መሆኗን በተደጋጋሚ ገልጻለች።

ይህ ፕሬዝዳንት ባይደን አሁን ያቀረቧቸው ዕጩ አምባሳደር ምናልባትም አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ የታየው የሰላም ተስፋ ከአገሪቱ ጋር ያላት ግንኙነት ለማሻሻል ያላትን ፍላጎት ለማሳየት የወሰደችው አንድ እርምጃ ሊሆን ይችላል።

በአፍሪካ እና በአካካቢው ጉልህ ስፍራ ያላት አገር እና ለአስርታት የአሜሪካ የቅርብ አጋር ሆና የቆየችውን ኢትዮጵያን በጉዳይ አስፈጻሚ ደረጃ ለአንድ ዓመት ያህል ግንኙነቷ እንዲቆይ ለማድረጓ አሜሪካ እስካሁን ምክንያቷን በይፋ ሳትገልጽ ቆይታለች።

በአሜሪካ መንግሥት አሠራር መሠረት ፕሬዝዳንቱ ለተለያዩ ኃላፊነቶች የሚመደቡ ዲፕሎማቶችን በዕጩነት ያቅርቡ እንጂ ምርጫው እና ጥቆማው በአብዛኛው የሚቀርብላቸው “የውጭ አገልግሎት ቦርድ” በተባለው አካል ነው።

በዚህ ሂደት ተመርጠው በፕሬዝዳንቱ ይሁንታ ያገኙ ዲፕሎማቶች በአገሪቱ ምክር ቤት (ሴኔት) ምክርና ስምምነት መሠረት እንዲጸድቅ ይደረጋል።

በዚህ ሂደትም የፕሬዝዳንቱ ዕጩዎች ውድቅ የመደረግ አጋጣሚ እምብዛም የተለመደ አይደለም፤ ስለዚህም ኧርቪን ጆዜ ማሲንጋ ቀጣዩ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ነው።

አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነቱ ዘርፍ እንደተለመደው የተለያዩ የግንኙነት ውጣ ውረዶች በሚኖሯቸው ጊዜ የዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸውን ደረጃ ከፍና ዝቅ ሲያደርጉ ቆይተዋል።