አሜሪካ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች ወደ ትግራይ ሊገቡ ይገባል አለች

የፎቶው ባለመብት, State Department
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች ወደ ትግራይ ሊገቡ ይገባል አሉ።
አንቶኒ ብሊንከን ገለልተኛ የሆኑ የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች ወደ ትግራይ መግባት አገራቸው ከፍተኛ ትኩረት የምትሰጠው እንደሆነ ትናንት ታህሳስ 13፣ 2015 ዓ.ም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እነዚህ መርማሪዎች ወደ ክልሉ የሚገቡት በአሁኑ ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መኖር አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት አሜሪካ በትግራይ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነትንም ማረጋገጥ እየሰራችበት ያለ ጉዳይ ነው ብለዋል ብሊንከን።
አንቶኒ ብሊንከን ይህንን ምላሽ የሰጡት የባይደን አስተዳደር የሰብዓዊ መብቶችን የውጭ ፖሊሲው ማዕከል ለማድረግ ቃል መግባቱ ጋር ተያያይዞ በባለፉት ሁለት ዓመታት አሜሪካ በተለያዩ ሃገራት ላይ ያላትን ጫናና ተፅእኖ በመጠቀም በሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ ምን ያህል ውጤት አስገኝታለች የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኛ በቀረበላቸው ወቅት ነው።
አንቶኒ ብሊንከን በየመን ጦርነት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጥሰት መቀነስ እንደተቻለ ጠቁመው በኢትዮጵያም የተደረገው የሰላም ስምምነት ይህንን ሰብዓዊ ጥሰት ለማስቆም ያለመ ነው ብለዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቆም በአፍሪካ ጥላ ስር የተደረገውን ውይይት መደገፏንና በዚህም የሰላም ስምምነት እንዲደረስ መቻሉን ጠቁመዋል።
ይህ ስምምነት ግጭት በዘላቂነት እንዲቆም፣ ጠመንጃን ዝም በማሰኘት ረገድ እንዲሁም ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲገባ እንዲሁም ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት በክልሉ እየደረሰ የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቀንስ ወይንም ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ያለመ ነው ብለዋል።
ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት ዕድል (አጎዋ) ተጠቃሚነት እንድትመለስ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለሚያጣራው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሰብዓዊ ባለሙያዎች ቡድን ፍቃድ ስትሰጥ መሆኑ ተዘግቧል።
ሪፖርተር እንግሊዝኛው ጋዜጣ እንደዘገበው የባለሙያዎቹ ቡድን ወደ አገር ውስጥ ገብተው መመርመር እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ባለሥልጣን መናገራቸውን ነው።
ኮሚሽኑ ጦርነቱ ወደተካሄደባቸው የትግራይ ክልል አካባባቢዎች እንዲሄዱ አለመፈቀዱን መግለጹ ይታወሳል።
የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤን ለፖለቲካ ዓላማ ማራመጃነት እየተጠቀሙበት ነው እንዲሁም በሃገር ውስጥ ጉዳይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ነው በማለት የወቀሰችው ኢትዮጵያ በቅርቡም ኮሚሽኑ እንዲበተን መጠየቋን የሃገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ከቀናት በፊት የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ለኮሚሸኑ አዲስ ሊቀ መንበር መምረጡን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ታንዛኒያዊው መሃመድ ቻንዴ ኦትማንን አዲሱ ሊቀ መንበር አድርጎ የሾመ ሲሆን ለዚህም ቡድኑን ሲመሩ የነበሩት ኬንያዊቷ ካሪ ቤቲ ሙሪንጊ መልቀቃቸውን ተከትሎ እንደሆነም ተገልጿል።
ሁለት ዓመት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
19 ገጾች ያሉትን የመጀመሪያ ግኝት ሪፖርት ይፋም በተደረገበት ወቅት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሆን ተብለው የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች እንደ ጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ ስለመዋላቸው ምክንያታዊ የሆኑ ማስረጃዎች አሉ ብሏል።
ኮሚሽኑ እነዚህ የተፈጸሙ ጥሰቶች የጦር ወንጀሎች እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንደሆኑም ያምናል ብሏል።
የኮሚሽኑን ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደማይቀበለው አስታውቋል።












