ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ሠራዊታቸው ‘ፀብ ጫሪ እና ተንኳሽ ኃይልን አስታግሷል’ አሉ

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈርቂ

የፎቶው ባለመብት, shabait

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈርቂ

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈርቂ የአገራቸው ሠራዊት በስም ያልጠቀሱትን ‘ፀብ ጫሪ’ እና ‘ተንኳሽ’ ያሉትን ኃይል አስታግሷል ሲሉ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ለኤርትራውያን እሁድ ዕለት የጀመረውን የ2023 አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ላይ ነው።

“በሕዝቡ የሚሞቅ እቅፍ ውስጥ ያለው የኤርትራ መከላከያ ኃይል ወረራ ለመፈጸም ይፍጨረጨር የነበረን ኃይል በፀረ-ማጥቃት አስታግሷል። በዚህም ኩራቴ ገደብ የለሽ ነው” በማለት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ስለጦር ኃይላቸው ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን 2022 በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ያሉ ኤርትራውያን “ንቁ ሆነው በጽኑ አቋም የሚያኮራ ትግል አድርገዋል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ “ወረራ ለመፈጸም ሲፍጨረጨር” ነበር ያሉትን ኃይል ማንነት በስም አልጠቀሱም።

ይሁን እንጂ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መከላከላያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት በትግራይ ውስጥ ተሰማርቶ የህወሓት ኃይሎችን ሲወጋ ቆይቷል።

ኤርትራ ምንም እንኳ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ስለመሆኗ በግልጽ ያለችው ነገር ባይኖርም፣ የህወሓት በቀጠናው መኖር የደኅንነት ስጋት ይፈጥርብኛል ትላለች።

የሰሜኑ ጦርነት ጅማሮ ላይ የህወሓት ኃይሎች ሮኬቶችን ወደ አሥመራ ማስወንጨፉ ቡድኑ ለአገሪቱ የደኅንነት ስጋት ስለመሆኑ እንደማሳያም ሲጠቀስ ቆይቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፕሬዝዳንቱ በአዲስ ዓመት መልዕክታቸው አገራቸው ኤርትራ እአአ 2022 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ፈተና ገጥሟት እንደነበረ ገልጸው፤ ከወረርሽኙ እና ከተፈጥሯዊ አደጋዎች በላይ የምዕራባውያን ጫና ኤርትራ ላይ በርትቶ እንደነበረ ገልጸዋል።

ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት የኤርትራ ሠራዊትና ባለሥልጣንት በተደጋጋሚ ሲወቀሱ ቆይተዋል።

በተጨማሪም የአሜሪካ መንግሥት በኤርትራ ወታደራዊ አመራሮች እና በመንግሥት በሚተዳደሩ ተቋማት ላይ ዕቀባ በማድረግ ስለጦርነቱ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ላይ የአገሪቱን ሠራዊት ተጠያቂ ሲያደርግ ቆይቷል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለአዲስ ዓመት ባደረጉት ንግግር ምዕራባውያን በአገራቸው ላይ ይፈጽሙታል ያሉት “ሴራ” በአውሮፓያኑ 2023 ሊቀጥል እንደሚችል ተናግረዋል።

ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተሳትፎ ያደረገው የኤርትራ ሠራዊት በካባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የመሠረተ ልማቶች ላይ ውድመት በማድረስ ሲከሰስ ቆይቷል።

የኤርትራ ሠራዊት እስካሁን በኢትዮጵያው ጦርነት ስለመሳተፉ ምንም ያለው ነገር ባይኖርም፣ ምዕራባውያን የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ በአሥመራ እና በአዲስ አበባ ላይ ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል።

ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነትን ያስቆመው የሰላም ስምምነት ሰነድ ላይ የኤርትራ ሠራዊት በስም ባይጠቀስም፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል መከላከያ ጦር ውጪ ያሉ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ ተስማምተዋል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ የሚጠበቅበትን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ባሳወቀበት ባለፈው ሳምንት ውስጥ የኤርትራ ወታደሮች ከአንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች እየወጡ መሆናቸውን ነዋሪዎች ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።

የኤርትራን ነጻነት የመራውና በብቸኝነት አገሪቱን የሚያስተዳድረው ሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክርሲ እና ለፍትህ (ህግዴፍ) ፓርቲ የቀድሞው የኤርትራ ሕዝብ ነጻነት ግንባር እና ህወሓት ከኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግሥት ጋር በተደረገው ጦርነት በትብብር መዋጋታቸው ይታወቃል።

ሁለቱም ኃይሎች ወደ ሥልጣን ከወጡ በኋላ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት በአስር ሺዎች የሞቱበት የሁለት ዓመት ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበር።