የስልክ አገልግሎት በመቀለ ከጀመረ 24 ሰዓት ሳይሞላ ከ220 ሺህ በላይ ጥሪዎች ተስተናገዱ

በትግራይ ክልል ሞባይል ስልክ እየጠቀመች ያለች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በትግራይ ክልል ሞባይል ስልክ እየጠቀመች ያለች ሴት

ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው የስልክ አገልግሎት ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ የክልሉ አካባቢ መሥራት ከጀመረ በኋላ ከተቀረው የአገሪቱ ክፍል እና ከመላው ዓለም በርካታ ሰዎች ወደ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጥሪ እያደረጉ ነው።

የስልክ አገለግሎት ዘግየት ብሎ በጀመረባት የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ስልክ መሥራት የጀመረው ረቡዕ ታኅሣሥ 19/2015 ዓ.ም. ምሽት ነበር።

በዚህም ለረጅም ጊዜ ከቤተሰብ ጋር ሳይገናኝ በርቀት የቆየው ሕዝብ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የስልክ ጥሪ ወደ መቀለ አድርጓል።

ወደ መቀለ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ የመጀመሪያው የሙከራ ጥሪ በስኬት ከተደረገ በኋላ አመሻሽ ላይ አገልግሎቱ መጀመሩን ተከትሎ እስከ ሐሙስ አስር ሰዓት ድረስ ከ220 ሺህ በላይ የስልክ ጥሪ ወደ ከተማዋ መደረጉን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ መሳይ ውብሸት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የቆየው የስልክ አገልግሎት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መጀመርን ተከትሎ የተጀመረ ሲሆን፣ የአገሪቱ ዋነኛው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢው ኢትዮ ቴሌኮም እንዳስታወቀው በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የፋይበር መስመሮችና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ሲጠግን ቆይቷል።

ይህንንም ተከትሎ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት እስካሁን ድረስ ከ27 በላይ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከተሞችና አካባቢዎች የስልክ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርገዋል።

ይህ የስልክ አገልግሎት መጀመር ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ተለያይተው የቆዩ በርካታ ቤተሰቦች እና ወዳጆች እንዲገናኙ ያስቻለ ሲሆን፣ ስልክ መስራት በጀመረባቸው ስፍራዎች አንዳንዶች ችግር እያጋጠማቸው እንደሆነ እየተናገሩ ነው።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና የኮምዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ መሳይ ውብሸት እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች በተመለከተ ለቢቢሲ እንዳስረዱት፣ አገለግሎቱ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ተቋርጦ በመቆየቱ በርካቶቹ ሲም ካርዶች ላይሰሩ ከሚችሉበት ደረጃ ላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናገረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢትዮቴሌኮም አሰራር መሠረት ሲም ካርዶች አገልግሎት ላይ ሳይውሉ ለረጅም ጊዜ ካርድ ሳይሞሉ እና ጥሪ ሳያደርጉ በሚቆዩበት ጊዜ ሥርዓቱ ቁጥሮቹን ጥሪ ብቻ ወደ መቀበል ሲቆይ ደግሞ ከአገልግሎት ወደ ማገድ ደረጃ ውስጥ እንደሚያስገባቸው ገልጸዋል።

ነገር ግን በክልሉ ውስጥ በጦርነት ምክንያት አገልግሎት ተቋርጦ በመቆየቱ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች የገጠማቸውን ችግር ለመቅረፍ የማስተካከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን አቶ መሳይ ተናግረው፣ ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ውስጥ የኢትዮ ቴሌኮም መደብሮች በቀጣይ ቀናት ሥራ ስለሚጀምሩ የበለጠ ችግሩ እንደሚቀረፍ ተናግረዋል።

ለሁለት ዓመት ያህል በተካሄደው ጦርነት የትግራይ ክልል ከሁሉም አይነት የግንኙነት መስመሮች ተቆራርጣ የቆየች ስትሆን፣ ለዚህ የሚያገለግሉ መሠረተ ልማቶች ላይ ውድመት እንደደረሰ ተነግሯል።

ኢትዮ ቴሌኮም እንዳስታወቀው በክልሉ ውስጥ አገልግሎቱን ለመጀመር 980 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ባለው የፋይበር መስመር ላይ ጥገና ማድረግ ነበረበት። በዚህም ወደ 30 የሚጠጉ የትግራይ ከተሞች የስልክ እና ሌሎች የቴሌኮም አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ገልጿል።

እጅግ አስፈላጊ የሆኑት የመሠረታዊ አገልግሎቶች ማለትም የኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮም እና የባንክ አገልግሎቶች እርስ በእርስ የተሳሰሩ በመሆናቸው የቴሌኮም አገለግሎት የማስጀመሩ ሥራ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን ተከትሎ እየተከናወነ ነው።

የቴሌኮም አገልግሎት መጀመር ተከትሎ ደግሞ የባንክ አገልግሎት እየተጀመረ ሲሆን እስካሁንም 61 የተለያዩ ባንኮች ቅርንጫፎች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። ይህም በቀጣይ ቀናት በበርካታ የትግራይ አካባቢዎች እየሰፋ እንደሚሄድ መንግሥት አስታውቋል።

እነዚህ መሠረታዊ አገለግሎቶች መልሰው ሥራ መጀመር የቻሉት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ወሳኝ የተባለው በዘላቂነት ግጭት የማቆም ስምምነት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተፈርሞ ጦርነቱ ከቆመ በኋላ ነው።

በዚህ ስምምነትም የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲቀላጠፍ፣ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ፣ የፌደራሉ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ እና የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ የሁለቱ ወገኖች ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መሪዎች በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ለስምምነቱ ተግባራዊነት አስፋለጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ያሳወቁ ሲሆን፣ ሰኞ ታኅሣሥ 17/2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች አፈጉባኤ የተመራው የልዑካን ቡድኑን ጉዞ በተመለከተ ማብራሪያ ከተሰጣቸው በኋላ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ ክልል የመሠረታዊ አግልግሎቶች የማስጀመሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማዘዛቸው ተገልጿል።