የፌደራል ፖሊስ ወደ መቀለ ከተማ መግባቱ ተገለጸ

ፌደራል ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Federal Police

የፌደራል ፖሊስ ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ በመግባት የፌደራል መንግሥቱን ተቋማት የመጠበቅ ሥራ ማከናውን መጀመሩ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዛሬ ታኅሣሥ 20/2015 ዓ.ም. እንዳስታወቀው የፖሊስ አባላቱን በትግራይ መዲና መቀለ ከተማ በመሰማራት የፌደራል መንግሥቱን ተቋማት የመጠበቅ ሥራቸውን ጀምረዋል ብሏል።

በመንግሥት እና በህወሓት መካከል ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም ከሁለት ወር ገደማ በፊት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሠረት የፌደራሉ ሠራዊትና የፖሊስ ኃይል በትግራይ ክልል ውስጥ እንደሚሰማሩ ተገልጾ ነበር።

በዚህም በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት የፌደራል መንግሥቱ ተቋማትን ለመጠበቅ ሥልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በክልሉ የሚገኙትን የፌደራል ተቋማትን ለመቆጣጠር ዛሬ ሐሙስ መቀለ ከተማ መግባቱ ተገልጿል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ እየሆነ ባለበት በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በትግራይ ክልል የሚገኙ በፌደራል መንግሥቱ የሚተዳደሩ አየር ማረፊያዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የቴሌኮም ተቋማትን፣ የባንክ እና ሌሎች የኅብረተሰቡ አገልግሎት ሰጪ ለሆኑ ተቋማት ጥበቃ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ፌደራል ፖሊስ እንዳለው ከዚህ ቀደምም በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ተሰማርቶ “ኅብረተሰቡን በማረጋጋት ወደ ቀየው እንዲመለስ በማድረግ እንዲሁም የፀጥታ እና ደኅንነት የማስከበር ሥራዎችን እየሰራ ቆይቷል” ብሏል።

የርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የፌደራል መንግሥቱ መቀለን ተቆጣጥሮ ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ክልሉን ባስተዳደረበት ጊዜ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና ፖሊስ በክልሉ ውስጥ ለስምንት ወራት ተሰማርተው መቆየታቸው ይታወሳል።

ከዚያም በኋላ የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ከወጣ በኋላ የህወሓት ኃይሎች ክልሉን ተቆጣጥረው የቆዩ ሲሆን፣ ባለፈው ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በተደረሰው የፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ወደ ትግራይ እንደሚገባ ተገልጿል።

በዚህ ስምምነት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲቀላጠፍ፣ የፌደራሉ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ፣ የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ ተስማምተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ፀጥታ አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ከሐሙስ ታኅሣሥ 20/2015 ዓ.ም. ጀምሮ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ወደ መቀለ እንደሚገባ እና የህወሓት ተዋጊዎች ከባድ መሳሪያዎችን ማስረከብ እንሚጀምሩ ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ በመግባት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንደሚጀምር ገልጸው ነበር።

የፌደራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊት አስካሁን ወደ መቀለ ስለመግባቱ የተባለ ነገር ባይኖርም፣ ከዋና ከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ግን ሪፖርቶች አመልክተዋል።

በሰላም ስምምነቱ መሠረት በዚህ ሳምንት ወሳኝ የሚባሉ እርምጃዎች በሁለቱም ወገኖች እየተወሰደ መሆኑ የታየ ሲሆን፤ የአየር በረራ ወደ መቀለ የተጀመረ ሲሆን በመዲናዋ እና በበርካታ የትግራይ አካባቢዎች ደግሞ የቴሌኮም አገልግሎቶች ተጀምረዋል።

በዛሬው ዕለት የሰላም ስምምነቱ ዋነኛ አሸማጋዮች የሆኑት የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ኡሁሩ ኬንያታ እንዲሁም የኢጋድ ሊቀመንበር ወርቅነህ ገበየሁ ከበርካታ አገራት ዲፕሎማቶች ጋር ወደ መቀለ ገብተው ከፌደራል እና ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።