የኤርትራ ሠራዊት ከአድዋ እና ከአክሱም እየወጣ መሆኑን ነዋሪዎች ገለፁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኤርትራ ሠራዊት ይገኝበት ከነበረው የአድዋ እና የአክሱም አካባቢዎች በብዛት እየወጣ መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለፁ።
ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በበርካታ መኪኖች የተጫኑ የኤርትራ ሠራዊት አባላት ከእንዳባገሪማ አካባቢ በመምጣት አድዋን አቋርጠው ሲያልፉ ማየታቸውን አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
“ከዛሬ ጠዋት [ጥር 12/2015 ዓ.ም.] ጀምሮ ወታደሮቹ በጣም ብዙ በሆኑ ትላልቅ ስካንያ አውቶቡሶች፣ በሲኖትራኮች፣ በአይሱዙዎች ተጭነው ሲወጡ አርፍደዋል።”
ነዋሪው ከአካባቢው ሲወጣ የተመለከቱት የሠራዊት ብዛት እጅግ ብዙ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ሌላ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ የዐይን እማኝ ደግሞ “መኪኖቹ ጥሩንባ እየነፉ ሠራዊቱም እየጨፈረ” እንደነበር መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ጨምረውም ሲወጡ ተመለከትኩ ያሏቸው የኤርትራ ወታደሮች ናቸው ሰንደቅ ዓላማ ይዘው እየጨፈሩ እና መፈክሮችን እያሰሙ ከአድዋ ወደ አክሱም አቅጣጫ መጓዛቸውን ገልጸዋል።
ለሁለት ዓመት የቆየውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለማብቃት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መሪዎች መካከል በተደረሰው ስምምነት የፌደራሉ የመከላከያ ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ እንደሚደረግ ተጠቅሷል።
ቢቢሲ ያናገራቸው የአድዋ ከተማ ነዋሪዎች አክለውም በከተማ ዳርቻዎች ላይ የፌደራል መንግሥት ሠራዊት አባላት እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከሁለት ቀን በፊትም በተመሳሳይ የኤርትራ ሠራዊት አባላትን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ራማ አቅጣጫ መሄዳቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዐይን ምስክር፣ የአሁኖቹ መኪኖች ግን ከሠራዊቱ ባሻገር ሌሎች እቃዎችን ጭነው መመልከታቸውን ገልፀዋል።
“ከሁለት ቀን በፊት ወደ አዲ በራኽ ከ20 እስከ 30 የሚሆኑ መኪኖች አልፈዋል። የዛሬውን ለየት የሚያደርገው አንዱ ነገር ብዛት ያለው ሠራዊት መሆኑ እና ሁሉንም ነገር የጫኑ መሆናቸው ነው። ፀረ አውሮፕላን የጫኑ አይሱዙዎች ሳይቀሩ አልፈዋል።”
ከኤርትራ በኩል ያሉ የተለያዩ የቢቢሲ ምንጮችም የአገሪቱ ሠራዊት እና የጦር መሳሪያዎች በብዛት እየወጡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ በተደረሰው ስምምነት የኤርትራ እና የአጎራባች ክልሎች ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ፣ የህወሓት ተዋጊዎች ደግሞ ትጥቅ እንዲፈቱ ለማድረግ የሚያስችል ዘላቂ የተኩስ አቁም ከተፈረመ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል።
በዚህም መሠረት ከሳምንት በፊት የህወሓት ታጣቂዎች ከባድ መሳርያዎችን ለፌደራል መንግሥት ማስረከብ መጀመራቸው የተነገረ ሲሆን፣ የአማራ ልዩ ኃይል አባላትም ከሽረ አካባቢ መውጣት መጀመራቸው ተገልጿል።
ነገር ግን በጦርነቱ ውስጥ ጉልህ ሚና ስለነባራቸው የኤርትራ ሠራዊት አባላት እስካሁን ሲሰማ የነበረው መረጃ አርስ በእርሱ የሚቃረን ነበር።
ቢበሲ ያነጋገራቸው የአክሱም ነዋሪ ደግሞ በበኩላቸው ዛሬ አርብ ጥር 12/2015 ዓ.ም. ማለዳ ከ2፡30 ሰዓት ጀምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች እና የጦር መሳርያዎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከተማዋን አቋርጠው ወደ ሽረ እየሄዱ መሆኑን ገልፀዋል።
የአክሱም ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ በሪሁ ካህሳይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ታንኮች እና መድፎች እንዲሁም ሠራዊት ያዙ መኪኖች በከተማዋ ሲያልፉ ማርፈዳቸውን ገልፀዋል።
“እያለፉ የነበሩትን መኪኖች ለመቁጠር ሞክሬ ነበር። 70 የሚሆኑ መኪኖች፣ 12 ታንኮች፣ 4 ዙ 23 ቆጥሬያለሁ። አሁንም እያለፉ ነው። የተለያዩ ዓይነትመኪኖች ናቸው። ሰውም እቃም ጭነው ከአድዋ ወደ ሽረ እየሄዱ ነው።”
በመኪናዎቹ ላይ ‘ኤርትራ አሸነፈች’ የሚል መፈክር ተለጥፎ እንዳዩ የሚገልፁት አቶ በሪሁ፣ የአክሱም ነዋሪ ወደ አስፓልት ወጥቶ የሠራዊቱን መሄድ እየታዘበ እንደሆነ ገልፀዋል።
“ጠቅልለው እየወጡ ይመስለኛል። ሕዝቡም ተደስቶ ጎዳናውን ሞልቶት ይታያል” ብለዋል አቶ በሪሁ።
ሌላ ቢቢሲ ያነጋገረው የአክሱም ነዋሪ ብዙ ወታደሮችን የጫኑ መኪናዎች ከተማውን አቋርጠው እያለፉ መሆናቸውን በመግለጽ ታንክ እና መድፍ የጫኑ መኪናዎች ማየቱንም ተናግሯል።
“ተሳቢ መኪናዎች ላይ የተጫኑ ብዙ ወታደሮችን አይቻለሁ። በመካከል ደግሞ መሳርያ የጫኑ መኪኖች ነበሩ። እስካሁን ድረስ መቶ የሚሆኑ መኪኖች አይቻለሁ። ይህን ያህል መኪና እና ሠራዊት ሲንቀሳቀስ አይተን አናውቅም። አሁንም ገና እያለፉ ነው” ሲሉ ነዋሪው አርብ ረፋድ ላይ ለቢቢሲ ገልጿል።
የኤርትራ ሠራዊት በከፍተኛ ቁጥር ከአድዋ እና ከአክሱም ከተሞች እየወጣ መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ያረጋገጡ ሲሆን፣ ይህንን በተመለከተ ግን ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ መንግሥታት እንዲሁም ከህወሓት መሪዎች በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ጀምሮ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት አማፂያን መካከል ሲካሄድ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነትን ተከትሎ ኤርትራ ከፌደራል መንግሥቱ ጎን ሠራዊቷን አሰልፋ ቆይታለች።
የኤርታራ ሠራዊት በትግራይ ጦርነት በነበረው ተሳትፎ በተለያዩ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የንብረት ውድመቶች ይከሰሳል።
የተባበሩት መንግሥታትም እና ሌሎች የመብት ተሟጋቾች ሁሉም በጦርነቱ የተሳተፉ ወገኖች ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈፀማቸውን ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ለረዥም ጊዜ በትግራይ ጦርነት መሳተፏን በይፋ ያልገለፀችው ኤርትራ ሠራዊቶቿ በደፈናው “ጠላት” ያለቻቸው ኃይሎች ማስታገሱን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት አስመልክተው ባወጡት መግለጫ ላይ ገልፀው ነበር።












