የቡና አገር በሆነችው ኢትዮጵያ ያልተለመደው የጥርኝ ቡና

በሁለት ስኒ የቀረበ ቡና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጥርኝ የምታመረተው ቡና በተለመደው መንገድ ገበሬው ቡና ለቅሞ፣ አድርቆ፣ አጥቦ፣ አፍልቶ ከሚጠጣው የተለየ ነው።

እንዲሁ የቡና ሱሰኛ የሆነ እና አነስተኛ ገቢ ያለው፣ መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ የሚጠጣው፣ አልያም ቤቱ አጭሶ አጫጭሶ የሚያፈላው ቡናም አይደለም።

ደረጃው ከፍ ያለ፣ ዋጋው ውድ፣ ጥም መቁረጫ ብቻ ሳይሆን ደረጃ መለያ የሆነ የቡና ዓይነት ነው፤ የጥርኝ ቡና።

ይህ ቡና በትላልቅ የዓለማችን ሆቴሎች ውስጥ በከፍተኛ ገንዘብ ይሸጣል። የእንስሳት መብት ተቆርቋሪዎች ግን ሽንጣቸውን ገትረው በሕግ አምላክ ሲሉ ይከራከራሉ።

በእንግሊዘኛ kopi Luwak ወይንም ደግሞ Civet coffee ይባላል።

ምክንያቱም ጥርኝ የምታመርተው ቡና ስለሆነ ነው።

ጥርኝ በአብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ በማምረት የምትታወቀው ዝባድ ነው።

ዝባድ ደግሞ ሽቶ ለማምረት የሚያገለግል ነው።

ከረዥም ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ ዝባድን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ስሟን ብትተክልም፣ የጥርኝን ቡና በማምረት እና በመላክ ግን እንዳልተሳካላት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የጥርኝ ቡና እንዴት ነው ቡና የምታመርተው?

የዱር እንስሳት ተመራማሪ እና በጅማ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ሐብታሙ በጥርኝ ላይ በርካታ ምርመሮችን ሰርተዋል።

እኚህ የዱር እንስሳት ተመራማሪ (ዋይልድ ላይፍ ኢኮሎጂስት) ስለ ጥርኝ ቡና ሲያስረዱ “በአጭሩ ኮፒ ሉዋክ ማለት ቀይ ቡና (የበሰለ ቡና) ጥርኝ ተመግባ ግርባቡ ላይ ያለውን ፕሮቲን እና ካርቦ ሃይድሬት ወስዳ ከገለባው ጋር የምታወጣው ቡና ነው” ይላሉ።

እኚህ ተመራማሪ እንደሚሉት ጥርኟ የምትፈልገው “ቡናው ውስጥ ያለውን ንጥረ ነገር ነው።”

ቀይ ቡናን ጥርኝ ብቻ ሳይሆን ልጆች ስለሚጣፍጣቸው እንደሚበሉት ዶ/ር ታደሰ ይናገራሉ።

“ተመራምረን እንደ ደረስንበት የቡና ግርባብ ላይ ፕሮቲን ካርቦሃይድሬት እና ስብ አለ። ስለዚህ ኮፒሉዋክ ማለት ከጥርኝ ሆድ ውስጥ የወጣ ቡና ማለት ነው።"

አቶ ፍፁም በከሬ የቡና ባለሙያ ናቸው።

በየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሆነው UNIDO ውስጥ በቡና ፕሮጀክት ላይ የብሔራዊ ቴክኒክ አማካሪ ሆነው ያገለግላሉ።

እርሳቸውም የዶ/ር ታደሰን ሃሳብ በማጠናከር “ቡናው ከሆዷ ውስጥ ሲወጣ ልክ አንደታጠበ ቡና ነው" ብለዋል።

ጥርኝ ቀይ ቡና እየተመገበች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለመሆኑ ጥርኝ ምን ዓይነት እንስሳ ናት?

ይህች ዝባድ በማምረት የምትታወቅ እንስሳ የምትመደበው አጥቢ ከሆኑት ወገን ነው።

“በዓመት ውስጥ አንዷ ሶስት አራት ጊዜ ትወልዳለች። አንዳንዴ ደግሞ አራት ወልዳ ሁለት ታሳድጋለች” ይላሉ የዱር እንስሳት ተመራማሪው።

ጥርኝ በባህሪዋ ስጋም አትክልቶችንም ትመገባለች።

“ከጥንቸል ያነሱ አእዋፋትን ትመገባለች። እንቁላላቸውንም ትበላለች። የሞተ ነገር መሬት ላይ የምተወው የላትም። ጥንቸል፣ አይጥ ታድናለች። ከእጽዋት ደግሞ ከቡና በተጨማሪ የዋርካ እንዲሁም የዋንዛ ፍሬዎችን ትመገባለች።”

ጠባይዋስ እንዴት ነው ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ታደሰ “ሰው ትጣላለች፤ ብትለምድም እሺ አትልም። እየተጠነቀቁ ነው። ቤት ውስጥ ወልዳ ካሳደገች ለማዳ ትሆናለች። ከውጪ የምትያዘው ግን ከሰው ጋር ትጣላለች” ይላሉ።

ጥርኞች በማህበራዊ ኑሯቸው ግላዊ እንዲሁም ክልለተኛ ናቸው።

እነዚህ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ የሚኖሩ አጥቢ አንስሳት በአፍሪካ፣ እስያ እንዲሁም ላቲን አሜሪካ ውስጥ በስፋት ይገኛሉ።

በእርግጥ ኢንዶኔዢያ ያለችዋ ጥርኝ በአካል አነስ ብትልም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጥርኝ ዝርያ ግን ግዙፍ መሆኑን ዶ/ር ታደሰ ያስረዳሉ።

ጥርን ቀይ ቡና ከተመገበች በኋላ የተፀዳዳችው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጥርኝ ቡና እንዴት ይለቀማል?

የጥርኝ ቡና በሁለት መንገዶች ሊለቀም ይችላል።

አቶ ፍፁም በከሬ ይህንንም ሲያብራሩ “አንደኛው ይህችን ጥርኝ ይዘናት ቤት ውስጥ ቡና እንድትመገብ ተደርጎ የምታወጣው ነው። ሌላኛው ደግሞ ቡና በሚበቅልበት አካባቢ የሚመረተው ነው።"

እንደ አቶ ፍፁም ከሆነ ይህች እንስሳ ቡናውን ከበላች በኋላ ሄዳ የምትፀዳዳው አንድ አካባቢ ወይንም ጉዳጓድ ውስጥ ነው።

". . .ዛሬ ለምሳሌ በልታ የሆነ ቦታ ከተፀዳዳች ተመላልሳ ተመሳሳይ ቦታ ነው የምትፀዳዳው። በዚህ ምርት ላይ ትንሽ አስቸጋሪ የሚያደርገው ነገር፣ ጫካ ከሆነ የምትፀዳዳበት ቦታን ማግኘት ሊያስቸግር ይችላል”

ዶ/ር ታደሰ በበኩላቸው “የአንድ የቤተሰብ አባላት በአንድ ቦታ ነው የሚፀዳዱት። ይህም እንደ ድንበር ያገለግላቸዋል። ኑሯቸው ለየብቻ ስለሆነ ይህ ቦታ ለእነርሱ እንደ መገናኛ ቦታ ነው። የትም የበሉትን መጥተው የሚፀዳዱት አንድ ቦታ በላይ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

ጥርኝ የበላችውን ቀይ ቡና ከተፀዳዳች በኋላ ገበሬው ምርቱን ሲሰበስብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጥርኝ ቡና ከሌላው ቡና በምን ይለያል?

የጅማ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ታደሰ “ፕሮቲኒ ከውስጡ ወጥቶ ያለቀ ቡና ጣዕሙ የተለየ ነው። እንደ ጉድ ይጣፍጣል” ሲሉ ይገልጻሉ።

አክለውም “ቡናው ሆዷ ውስጥ ሲቆይ የተለያዩ ኢንዛይሞች ውስጥ ተዋህዶ ፕሮቲኑ ተሰባብሮ ይወጣል” ይላሉ።

ፕሮቲን ግርባቡ ውስጥ እና የቡናው ፍሬ ውስጥ ይገኛል። ከቡናው ውስጥ ፕሮቲን የሚያወጣ ፋብሪካ “በዚህ ዓለም የለም” ሲሉ ይህችን እንስሳ ዶ/ር ታደሰ ያደንቃሉ።

“ሆዷ ውስጥ ያለውና የምታመነጨው ቅመም ፕሮቲኑን ከሆዷ ውስጥ ያወጣል። ፕሮቲኑ የወጣለት ቡና ደግሞ እንደ ጉድ ይጣፍጣል። የቡና ደረጃ በምን ይለካል? ከተባለ ቡና ውስጥ ባለው የፕሮቲን መጠን ነው። ፕሮቲን የሌለው ቡና ጣዕሙ የትም የለም።”

አቶ ፍፁም በከሬም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ።

“የተለየ ጣዕም አለው፤ ሆዷ ውስጥ መብላላቱን (ፈርመንቴሽኑን) ጨርሶ ነው የሚወጣው፤ ይህ ደግሞ የቡናውን ጣዕም (ካፕ ኳሊቲ) ይጨምራል። ዱር ውስጥ የተለያየ ነገር ስለምትመገብ ከእነዚህ ጋር ነው መብላላቱ የሚካሄደው። ይህ ደግሞ ኢንደስትሪው ውስጥ ገብቶ ከሚወጣው ቡና የተለየ ያደርገዋል።”

የቡና ዛፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ ውስጥ የጥርኝ ቡና ምን ያህል ይታወቃል?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች እንደሚገልፁት፣ ጥርኝ ባለችበት እና ትላልቅ ደኖች በሚገኙበት አካባቢ ይህ ምርት በስፋት ይገኛል።

ኢንዶኔዢያ፣ ኮሎምቢያ እና ኮስታሪካን ይንን የቡና ዓይነት በብዛት በማምረት ይታወቃሉ።

በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያም ግዙፍ ደኖች እና ጥርኝ በሚገኙበት ስፍራ ይህ ምርት ይታወቃል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ አለ። ነገር ግን የምርት መጠኑ በጣም ትንሽ ነው። እርሷን መከታተል በጣም ይፈልጋል” ይላሉ አቶ ፍፁም።

ዶ/ር ታደሰ በበኩላቸው አርሶ አደሮች ይህንን የቡና ዓይነት እንዲያመርቱ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

“ከዚህ ቀደም አምርተን ነበር። ነገር ግን ገበያ የለም። ገበያ ፍጠሩልን ብለን 'ኢሴክስ' ጥያቄ አቅርበን ነበር። በዚህ ምክንያት ተስፋ ቆርጠናል። ወደፊት እንደሚሳካ ግን ተስፋ አለኝ።"

ኢትዮጵያ ውስጥ በኢሊ አባቦራ፣ ከፋ፣ ሻኪሶ እና ጅማ ይህንን ቡና የሚያመርቱ ገበሬዎች መኖራቸውን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ነገር ግን እንደ አገር ይህንን የሚደግፍ ፖሊሲ የለም ሲሉ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

አቶ ለሚ ይታገሱ፣ አርከና ኮፊ በሚባል ድርጅት ውስጥ የገበያ ማፈላላግ ባለሙያ በመሆን ያገለግላሉ።

እኚህ ባለሙያ የጥርኝ ቡና ለማምረት ፈልገው ቢጠይቁም መከልከላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለሥልጣናት ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር በጣም ጥቂት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ለሚ፣ “ቪዲዮ አውጥቼ አሳየኋቸው። ሽቶ ማምረት ፈልገህ ነው አሉኝ። ይህንን እኛ አናውቅም ሲሉ መለሱልኝ” ይላሉ።

በስኒ የቀረበ ቡና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጥርኝ ቡና ምን ያህል ያወጣል?

አጠቃላይ የጥርኝ ቡና በጣም ውድ ከሚባሉት መካከል ነው። ነገር ግን ትክክለኛ ዋጋውን ለማወቅ ያስቸግራል።

አቶ ፍፁም ቡናው የጥርኝ ነው ተብሎ ከተመሰከረለት፣ የስፔሻሊቲ ቡና ከሚባለው እጥፍ ነው የሚሸጠው ሲሉ ያስረዳሉ።

የተለያዩ ምንጮች አንድ ስኒ የጥርኝ ቡና ከ30 እስከ 100 የአሜሪካ ዶላር ያወጣል ሲሉ ይገልጻሉ።

ግማሽ ኪሎ የጥርኝ ቡና ከ100 እስከ 600 የአሜሪካ ዶላር ይቸበቸባል የሚሉም አሉ።

ዶ/ር ታደሰ በበኩላቸው “ዋጋው በጣም ከፍተኛ ነው። አንድ ስኒ በ50 ዶላር ነው የሚጠጣው። አሁን ደግሞ ጭራሽ እየተወደደ መጥቷል ሲሉ ይገልጻሉ።

“ጥርኝ የሚያረባ ሰው ጊዜውን ጠብቆ የበሰለ ቡና እንድትመገብ ካደረጋት ሁለት ስራዎች ናቸው የሚሰሩት። አንድ ዝባድ ያመርታል። ሌላው ደግሞ እንደ ጉድ የሚጣፍጠውን ቡና ያመርታል። ጥርኝም ትጠቀማለች። ገበሬውም ገቢው ከፍ ይላል። አገሪቱም ሌላውን አንድ መቶ ኩንታል ከምትልክ ይህንን ቡና ሶስት እና አራት ኪሎ ብትልክ ይሻላታል” ሲሉ ጠቀሜታውን ይገልጻሉ።

ለጥርኝ መብት ቆመናል የሚሉ የመብት ተሟጋቾች ግን ይህች እንስሳ ለምርቷ ሲባል ታድና በአንድ አካባቢ እንዳትንቀሳቀስ በመደረግ ጥሬ ቡና እንድትበላ እየተደረገ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ዶ/ር ታደሰ ግን ይህንን ይቃወማሉ።

“. . . ጫካ ውስጥ ድሮም ቡና ትመገባለች። ገበሬው ገቢው ከፍ ካለ ጥርኝን ይንከባከባል" ሲሉ ይመልሳሉ።