የሲዳማ ቡና በኪሎ ለምን እስከ አርባ ሁለት ሺህ ብር ተሸጠ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ያለፉት ሦስት ዓመታት ለሲዳማ ቡና ‘ቡናማ’ ዓመታት ናቸው።
ወርቃማ እንዳይባሉ ቡና ከወርቅም በላይ ነኝ ያለባቸው ዓመታት ናቸው።
ከዚህ ጀርባ ደግሞ ሦስት ስሞች ቀድመው ወደ አዕምሮ ይመጣሉ።
ንጉሤ ገመዳ፣ ታምሩ ታደሠ እና ለገሠ በጦሳ ናቸው።
ሦስቱም የሲዳማ ቡናን ይዘው ለውድድር ቀርበው አላፈሩም።
ይህ የቡና ውድድር ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ይባላል።
ውድድሩ ቡናን በጥራት ይለያል። ቀጥሎ በዓለም አቀፍ ጨረታ ለገበያ ያቀርባል።
ንጉሴ አንድ ኪሎ ቡናውን በ407 ዶላር ሸጠዋል።
የታምሩ ቡና ደግሞ 330 ዶላር ይገባዋል ተብሎ ዋጋ ተቆርጦለታል።
የለገሠ ቡና ግን ከሁለቱም የላቀ ነው። አንዱ ኪሎ ቡና 884.10 ዶላር ተሽጧል።
በዚህ ዋጋ የተሸጠ የኢትዮጵያ ቡና የለም።
አንድ ኪሎ ቡና 47 ሺህ 236 ብር ተሽጧል።
ስኬቱን ምስጋና “በቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ዙሪያ ለተሠራው ሪፎርም” የሚሉት አቶ ምንዳዬ ምትኩ የሲዳማ ክልል ቡና ፍራፍሬ እና ቅመማ ቅመም ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው።
ለአቶ ምንዳዬ ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ከውድድርም በላይ ነው።
‘አርሶ አደሮችንም ክልሉንም እየጠቀመ ያለ ውድድር ነው።’
መነቃቃት እና የሥራ ዕድልም ፈጥሯል።
“አርሶ አደሮቹና አቅራቢዎች በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር ተዘርግቷል። በዚህም የሲዳማ ክልል በጣም ተጠቃሚ ነው። ከሦስት ዓመት ወዲህ በቡና ላይ ለውጡ ትልቅ ነው” ይላሉ።
እውነትም ለውጥማ አለ። በመጀመሪያው ዓመት ያሸነፈው አርሶ አደር አሁን ሌላ ህይወት እየመራ ነው።
አርሶ አደር ከሚባለው ማዕረግ በተጨማሪ ላኪነትንም ደርቧል።
“ቀደም ሲል አነስተኛ ካፒታል ነበረው። (ከውድድሩ) በኋላ ግን የላኪነት ፈቃድ አውጥቶ ወደ ላኪነት አድጎ ሸላሚም ሆኗል።”

ይህ የአንድ ግለሰብ ብቻ ታሪክ ነው።
ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ቁጥራቸው እየጨመረ ነው።
“ይህ የክልሉ ሃብት ነው። ክልሉ ከእነዚህ ትልቅ ጥቅም ያገኛል፤ ገቢው ያድጋል። አርሶ አደሮቹ ህይወት ሲለወጥ ገበያውም ይነቃቃል። የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያለውን ትልቅ ችግር ይፈታል” የአቶ ምንዳዬ ሃሳብ ነው።
ይህንን የሰሙ ‘እኛስ?’ ያሉበት ነው።
በዚህ ዓመት ውድድርም በርካቶች ተሳትፈዋል።
በዚህ ዓመት ደግሞ አርሶ አደሮች ብቻ እንዲያቀርቡ ተደርጓል።
ባላቸው መሬት እና የመሬት ይዞታ አቅርበው እንዲወዳደሩ ነው የተደረገው።
በዘንድሮው ውድድር አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡት የሲዳማ ቡናዎች ናቸው።
“አንደኛ የወጣው ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኘበት እጅግ በጣም አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የነበረ ሰው ነው።”
ጥራታቸውም ቢሆን ምርጥ ነበር።
የአቶ ምንዳዬ “ዘንድሮ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና ነው ያቀረብነው። አርሶ አደሩም የጥራቱን ሁኔታ ያሻሻለበት እና ፊቱን ወደ ቡና ልማት ያዞረበት ነው” ብለዋል።
ዘንድሮ ለፍጻሜ የደረሱ 40 ተወዳዳሪዎች ነበሩ።
14ቱ ደግሞ ከሲዳማ ክልል ናቸው።
የሲዳማን ቡና ምን እንዲህ ተፈላጊ፣ ተመራጭ እና ውድ አደረገው?
ትልቁ ነገር አየሩ ነው።
“በጣም ውጤታማ እየሆኑ ያሉት ደጋማ አካባቢ ያሉ ቡናዎች ናቸው” ይላሉ አቶ ምንዳዬ።
ሌላው ደግሞ ‘ኦርጋኒክ’ (ተፈጥሯዊ) ቡና መሆኑ ነው። ምንም ዓይነት ኬሚካል አይዞርበትም።
“የጥላ ዛፍም አላቸው። የቡና ፓኬጅ መጠቀማቸውም ሌላው [ምክንያት] ነው። የአየሩ ሁኔታም የረዳን ይመስላኛል” ይላሉ አቶ ምንዳዬ ምክንያቱ ብዙ መሆኑን በመጥቀስ።
በተለይ የደጋ አካባቢ ቡናዎች ተመራጭ ሆነዋል።
አሁን ቡና ወደ ደጋማው ሲዳማ አካባቢ እየሰፋ ነው።
እነ አርቤጎና፣ ቡራ፣ ደንሳ፣ አሮሬሳ አካባቢዎች ቡና ማለትስ የእናንተ ተብለዋል።
“በሌሎችም አካባቢ ይስፋፋል የሚል እምነት አለን። እነ ቦና አካባቢም ይጠቀማሉ ብለን እናስባለን” ይላሉ አቶ ምንዳዬ።
አስገራሚው ነገር እነዚህ ቦታዎች ከቡና ጋር አይተዋወቁም ነበር።
ለምሳሌ የዘንድሮው አሸናፊ ለገሠ በጦሳ ነዋሪነቱ አርቤጎና ወረዳ ቡርሳ ቀበሌ ነው።
አርቤጎና አካባቢ በጣም ደጋማ አካባቢ ነው። አልቲቲዩዱም በጣም ከፍተኛ ነው።
“አሁን ግን [በእነዚህ ቦታዎች] ከፍተኛ መነቃቃት ነው ያለው።”
ቀደም ሲል እንሰት፣ ስንዴ እና ገብስ ያመርቱ ነበር።
ጊዜ ሲቀየር እነሱም ተቀየሩ። ጊዜው ሲቀየር የሚያመርቱትም ተቀይሯል።

“የኤክስቴንሽን ድጋፍ ይደረጋል። የቡና ፓኬጅ እንዲጠቀሙ ይደረጋል። ያረጁ ቡናዎች የመተከታት ሥራ ይከናወናል። ለባለሙያዎችም የስልጠና ድጋፍ እንሰጣለን። በተራው ባለሙያው እስከ ታች ወርዶ ይደግፋል። የተሻሻሉ ቡናዎች እንዲያመርቱ የበሽታ መከላከል ስራዎችን በተመለከተ ስልጠና፣ ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል” የአቶ ምንዳዬ ሃሳብ ነው።
ቢቢሲ፡ እርስዎ ቡና ይጠጣሉ?
አቶ ምንዳዬ፡ እኔ በጣም ቡና የምወድ ሰው ነኝ
ቢቢሲ፡ ሌላ ቦታም ሄደው ቡና ይጠጣሉ?
አቶ ምንዳዬ፡ [ሳቅ] ሌላ ቦታም ቡና እጠጣለሁ
ቢቢሲ፡ እና የሲዳማ ቡና ከሌሎች በምን ይለያል?
አቶ ምንዳዬ፡ ስለለመድኩት መሰለኝ የሲዳማ ቡና ይለያል። የቅመም ጣዕም አለው። በዚህ በኩል የራሱ ባህሪ አለው። የሲዳማ ቡና መጠጣት ከለመድክ ከፍተኛ ሱስ ነው የሚያሲዝህ። በቀን ቢያንስ 3 ስኒ ቡና ሳልጠጣ አልውልም። ሌላም ቦታ ስሄድ እጠጣለሁ። ብዙ ምርጥ ምርጥ ቡናዎች አሉን። የይረጋጨፌ ቡናም በጣም እወዳለሁ። በአጠቃላይ ቡና እጠጣለሁ።
የሲዳማ ቡና ጥሩ ስሙ የገነነ ነው።
ዕውቅናው እንዲጎለበት ከክልል እስከ ፌደራል ድረስ እየተሠራ መሆኑ ተነግሮናል።
በአንድ ወቅት የቡና ዋጋ ወረደ።
አርሶ አደሮች ቁጭ ብለው እንዲያስቡ ያደረገ የዋጋ መውረድ ነበር።
በምን ልተካው ሲሉ ወደ አዕምሯቸው ሽው ያለላቸው ጫት ነበር።
ጫት ቡናን እግር በእግር ተካ።
ግን አልዘለቀበትም።

አሁን ደግሞ ቀኝ ኋላ ነው ጉዞው። ቡና ግዛቴን አላስደፍርም አለ።
“ጫት እና ባህር ዛፍ እየነቀሉ ወደ ቡና እየቀየሩ ያሉ በርካታ አርሶ አደሮች አሉ” ይላሉ አቶ ምንዳዬ።
ከአንድ ኪሎ ቡና በአርባ ሺህዎች ከታፈሰ ጫት ለምኔ ነው ነገሩ።
“ከዋጋውጋር ተያይዞ የመጣ [ለውጥ] ነው።”
“ቀደም ሲል የልፋታቸውን አያገኙም ነበር። ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ሰንሰለቱ ብዙ እና አስቸጋሪ ዘርፍ ነበር። [አርሶ አደሩ] ካመረተው የጉልበቱን ዋጋ እያገኘ ባለመሆኑ ወደ ሌሎች ሰብሎች እየገባ ነበር። አሁን ከተሻሻለ በኋላ ነው ወደ ቡና የገባው።“
“[አሁንም] ዓለም ላይ ካለው ዋጋ አንጻርም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ ነው ማለት አይቻልም” የአቶ ምንዳ ሃሳብ ነው።
እንደካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ያሉት ለገበያው መሻሻል ትልቅ ጥቅም እየሰጡ ነው።
ለዚህ ለውጥ ደግሞ ከቡናና ሻይ ባለስልጣን ጀምሮ የተዘረጋውን አሠራር በምክንያትነት ያቀርባሉ።
ሁለት እና ከዚያ በላይ ሄክታር ያላቸው አርሶ አደሮች ቡናቸውን በተገቢው አዘጋጅተው ወደ ውጭ መላክ ይችላሉ።
“የምርት እና ምርታማነት ማሻሻል ላይ ይሠራል። ከግብይት ስርዓቱ ህገወጦችን የመከላከል ስራዎችም ይሠራል። ይህን የሚከላከል ግብረ ሃይልም አለ። ሌላው ደግሞ የግብዓት አቅርቦት ነው። በዚህ በኩልም ማሻሻል አለ።”
“የሲዳማ ቡና አልን እንጂ የኢትዮጵያ ቡና ማለት ነው። ቀደም ሲል መዳረሻ ያልነበሩ አካባቢዎችም የኢትዮጵያን ቡና ይፈልጋሉ። እንደ ክልል ስንጠቀም እንደሃገርም እንጠቀማለን። በክልል ደረጃም ቢሆን ከፕሬዝዳንቱ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ በዚህ ልክ ይሠራል።“
ቡና ተተክሎ ምርት ለመስጠት ሦስት ዓመት ይጠይቃል።
ቡና እየሰጠ 15 እስከ 18 ዓመት ይቆያል።
ከዓመታት በኋላል እርጅና ሲጫነው መታደስ ይፈልጋል። ካልሆነ ምርት ይቀንሳል።
ቡና ይህን ሁሉ አልፎ ነው ለገበያ የሚቀርበው።
የካፕ ኦፍ ኤክሰለን ‘አውራ ፓርቲ’ ሆነናል የሚሉት አቶ ምንዳዬ ሦስቱንም ዓመት “የፕሬዚዳንሺያል ሽልማት” ማግኘታቸውን አንስተው በቀጣይም ማንም አይነቀንቀንም ይላሉ።
“ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ መመልከት የለም። የክልሉም ፕሬዝዳንተ የሚመሩት ስለሆነ ከላይ እስከታች በትኩረት ስለሚሰራ ከዚህ በላይ መስራት እችላለን” ነው መልሳቸው እንዴት ተብለው ሲጠየቁ።













