የአዲሱ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ ሹመት አነጋጋሪ የሆነው ለምን ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, NBE
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ እንዲሆኑ ማሞ ምሕረቱ ባለፈው ሳምንት ተሹመዋል።
ማሞ ምሕረቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተሾሙት የቀድሞውን የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴን (ዶ/ር) ተክተው ይሠራሉ።
አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ባለፈው ዓመት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ኩባንያ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።
የዓለም ባንክ ሠራተኛ የነበሩት ማሞ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ እና በዓለም ንግድ ድርጅት የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ ሆነውም አገልግለዋል።
በፈንጆቹ 2019 ፋይናንሻል ታይምስ በተሰኘው ጋዜጣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ውስጥ ካሉ ወጣት ልሂቃን (ቴክኖክራት) መካከል አንዱ ተብለው የተመረጡት ማሞ ምሕረቱ፣ የማዕከላዊው ባንክ ገዢ ሆነው ተሹመዋል።
የሕግ ምሩቁ ማሞ በዓለም ባንክ ከፍተኛ የግል ዘርፍ ስፔሻሊስት ሆነው እንዳገለገሉ የዓለም ባንክ ድረ-ገጽ ይጠቁማል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በፈረንጆቹ ከ2018 ጀምሮ ባንኩን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፉት 30 ዓመታት አዲሱን ተሿሚ ጨምሮ አምስት ገዢዎችን አስተናግዷል።
የአዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ወደ ሥፍራው መምጣት በዘርፉ በተሰማሩ ባለሙያዎች ዘንድ መከፋፈል የፈጠረ ይመስላል።
በአንድ ወገን አዲሱ የባንኩ ገዢ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያላቸው ቅርበት ሥራቸው ላይ ጫና ይፈጥራል የሚሉ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ፣ በሌላ በኩል ተቋሙ ገለልተኛ እስካልሆነ ድረስ የአዲስ ሰው መሾም ለውጥ አያመጣም ብለው የሚከራከሩ አሉ።
ብሔራዊ ባንኩ ነፃና ገለልተኛ ነውን?
“የብሔራዊ ባንክ ገዢ ብቻውን ትልቅ የምጣኔ ሃብት ውሳኔ ሊያሳልፍ አይችልም” የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይ፤ ነገር ግን የመነሻ ሐሳቦችን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በማቅረብ እንዲወሰን የማድረግ አቅም እንዳለው ያስረዳሉ።
ዋሲሁን እንደሚሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋም ሊሆን ስለሚገባው፤ ገዢውም በተመሳሳይ ገለልተኛ መሆን አለባቸው ተብሎ ይታሰባል ይላሉ።
“ለምሳሌ ‘ገንዘብ ማተም የለብንም፤ ጥቅሙ እና ጉዳቱ ይሄ ነው’ ብለው የማሳመን ሥራ የሚሠሩ ናቸው። ስለዚህ የብሔራዊ ባንክ ገዢዎችን እንደተፈለገው የሚሾሩ መሆን የለባቸውም።”
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አክለውም ይህ ‘በሎጂክ’ (አመክንዮ) ሲታይ ትክክል ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ይህ እውን እንዳልሆነ ይናገራሉ።
እንደ ኬንያ እና ጋና የመሳሰሉ የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ የበርካታ አገራት ብሔራዊ ባንኮች ከመንግሥት ተጽዕኖ ነጻ የሆኑ ገለልተኛ ተቋማት መሆናቸው ይነገራል።
ለምሳሌ የኬንያው ብሔራዊ ባንክ እኤአ ከ1996 ጀምሮ በፓርላማው ውሳኔ መሠረት ከየትኛውም አካል ነጻ ሆኖ እንደሚሠራ እና አመራሮቹንም በክህሎት አወዳድሮ እንደሚቀጥር ይገልጻል።
“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአንፃሩ በመንግሥት ተፅዕኖ ሥር ያለ ተቋም ነው” ይላሉ፤ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድ።
አንድ አገር ውስጥ መታተም ያለበት ገንዘብ ከጠቅላላ አገራዊ ምርት ዕድገት አንፃር ከሁለትና ሦስት በመቶ በላይ እንዲሆን አይመከርም የሚሉት ዋሲሁን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከዚህ በላይ ሲታተም እንደነበር አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ ይላሉ።
እንደ ዋሲሁን ገለጻ ይህ የሚያሳየው ብሔራዊ ባንኩ ከፖለቲካ መሪዎች ተጽእኖ ያልፀዳ መሆኑን ነው።
አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅርብ መሆናቸው እና ለገዢው ፓርቲ ያላቸው ቅርበት፤ “አይሆንም” የማለት አቅም አላቸው ወይ? የሚል ጥያቄ ይጭራል ይላሉ ዋሲሁን።
“ባደጉ አገራት ፖለቲከኞች ወደ ብሔራዊ ባንክ ገዢ በመደወል ‘ገንዘብ ይታተም ወይም አይታተም’ ሊሉ አይችሉም። ‘ፊስካል ፖሊሲ’ ወደሚመሩት በመሄድ በጀት ይጨመርልኝ ሊሉ ይችላሉ። መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴርን የበጀት ጭማሪ ሊጠይቅ ይችላል።”
አብዱልመናን ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋም አይደለም የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው።
በፈረንጆቹ 2008 የወጣው አዋጅ ብሔራዊ ባንኩ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን አድርጎታል፤ ስለዚህ የአገሪቱ መሪ ባንኩ እና ገዢው ላይ ጫና የማሳደር ሥልጣን አላቸው ባይ ናቸው አብዱልመናን።
በተጨማሪም ብሔራዊ ባንኩ ዓላማዎቹን የሚያስፈፅም የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ቢኖረውም በተግባር ግን ገዢው እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሳተፉበት የማክሮ-ኢኮኖሚ ኮሚቴ እንዳለ የሚጠቅሱት አብዱልመናን ባንኩ፤ “ምንም ነጻነት የሌለው መንግሥት እንደፈቀደ ተፅዕኖ የሚሳድርበት ተቋም ነው” ይላሉ።
ለዚህም ነው በኢትዮጵያ የተደረገው የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሹም ሽር “የሚያመጣው ለውጥ የለም” የሚሉት አብዱልመናን መሐመድ።
ባይሆን አዲሱ የባንኩ ገዢ ዓለም ባንክ ውስጥ ይሠሩ ስለነበር ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ያቀላጥፉት ይሆናል የሚል ተስፋ አላቸው።
“ዲቫሉዌሽን (የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም) ጠ/ሚኒስትሩ እና የባንኩ ገዢ ያሉበት ኮሚቴ የሚወስነው ውሳኔ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ብሔራዊ ባንክ ሲዳሰስ
ከብሔራዊ ባንክ መቋቋም በፊት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባንክ በአፄ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት የተቋቋመው አቢሲኒያ ባንክ ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፈረንጆቹ ጥር 1964 ሥራ እንደጀመረ የባንኩ ድረ-ገፅ መረጃ ያመላክታል።
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፈረንጆቹ 2008 በተሻሻለ አዋጅ የተቋቋመ ሲሆን “ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት እና የተረጋጋ የገንዘብ ሥርዓት እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት” የተቋቋመ እንደሆነ ነጋሪት ጋዜጣ ይገልጻል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድ አንደኛው የብሄራዊ ባንክ ሚና የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር (Monetary stability) እንደሆነ ያሰምራሉ።
ስያሜያቸው ይለያይ እንጂ በመላው ዓለም ማዕከላዊ ባንኮች አሉ የሚሉት ሌላኛው የዘርፉ ባለሙያ ዋሲሁን በላይ ናቸው።
እንደሚሉት የአንድ አገር ምጣኔ ሃብት ‘ፊስካል’ እና ‘ሞኒተሪ’ ፖሊሲ በሚቆጣጠሩ ድርጅቶች ይመራል።
‘ፊስካል’ ፖሊሲ ማለት የመንግሥትን በጀት የሚያስተዳድሩ፣ እንዲሁም ግብር የሚሰበስቡ እንደ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ገቢዎች ያሉ ተቋማት ናቸው።
‘ሞኒተሪ’ አሊያም የገንዘብ ፖሊሲውን የሚመራው ደግሞ ብሔራዊ ወይም ማዕከላዊ ባንክ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ ሥልጣን ኃላፊነቶች አሉት። ዋና ዋና የሚባሉት እነሆ፡
- ሳንቲም እና የብር ኖት ማሳተም፤ የአገሪቱን የገንዘብ አቅርቦት መቆጣጠር
- የወለድ መጠን ሌሎች የገንዘብ ክፍያዎችን መቆጣጠር
- የውጭ ምንዛሪን መመሥረት እና አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ክምችት ማስተዳደር
- ለባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እና ሌሎች የገንዘብ ተቋማት ፈቃድ መስጠት እና መቆጣጠር
- ባንኮች እና የገንዘብ ተቋማት የሚጠቀሙባቸውን የወርቅ እና የውጭ ምንዛሪ ክምችት ገደብ ማስቀመጥ
- የአገሪቱን መንግሥት ወክሎ እንደ ባንከር፣ ፊስካል ወኪል እና የገንዘብ አማካሪ ሆኖ ማገልገል
- በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ኢትዮጵያን መወከል ናቸው።
የአዲሱ ገዢ ሹመት ለምን አነጋጋሪ ሆነ?
ሹመቱን አጥብቀው ከተቃወሙ ምሑራን መካከል ግንባር ቀደሙ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዮናስ ብሩ (ዶ/ር) ናቸው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምጣኔ ሃብት አማካሪዎች ምክር ቤት ሊቀ-መንበር በመሆን ያገለገሉት ዮናስ፣ ሹመቱን ለምን እንደሚቃወሙ ባተቱቡት ጽሑፋቸው ሦስት አበይት ነጥቦችን ያነሳሉ።
አንደኛው አዲሱ የባንኩ ገዢ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ሰው መሆናቸው እና የገዢው ፓርቲ አባል እና የሕዝብ እንደራሴ መሆናቸውን ነው።
“የብሔራዊ ባንክ ገዢ ነፃ እና ገለልተኛ ሰው መሆን አለበት” ይላሉ።
“ምንም እንኳ ማሞ ‘የበቁ ባለሙያ’ ቢሆኑም የትምህርት እና የሙያ ልምዳቸውን የሚመጥን ሌላ ሥልጣን ቢሰጣቸው የተሻለ ይሠራሉ ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ሁለተኛ ያሉትን ምክንያት ያሰፍራሉ።
በሦስተኛነት የሚያስቀምጡት ምክንያት፤ አዲሱ የባንኩ ገዢ በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን እየመሩ ድርጅቱ በእግሩ ሳይቆም “በትምህርት እና በልምድ ብቁ ወዳልሆኑበት” ቦታ ሊመጡ አይገባም የሚል ነው።
በጠቅላላው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት አደጋ በተጋረጠበት በዚህ ወቅት ሊሆን የሚገባ ሹመት እንዳልሆነ በጽሑፋቸው አስረድተው ኢትዮጵያ ከጋና፣ ከናይጄሪያ እና ከኬንያ ልምድ መውሰድ አለባት ይላሉ።
የኬንያ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ የዶክትሬት ድግሪያቸውን ከዬል ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፣ በአገሪቱ ገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል።
አልፎም በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እስከ ምክትል ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።
የጋና ብሔራዊ ባንክ ገዢ ኬን ኦፎሪ-አታ በበኩላቸው ከ30 ዓመታት በላይ ዎል ስትሪትን ጨምሮ በአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት አገልግለዋል።
በኢኮኖሚክስ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ድግሪ፣ ከዬል ስኩል ኦፍ ማኔጅመንት ደግሞ ማስተርስ ድግሪ ይዘዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሚና
ዋሲሁን በላይ የብሔራዊ ባንክ ገዢ “ሞኒተሪ ፖሊሲውን መምራት ይችላል፤ ዕውቀት እና ብቃት አለው ተብሎ ስለሚታመን” ገዢው የሚያመጣቸው ምክረ-ሐሳቦች ጫና የመፍጠር ዕድል አላቸው።
አልፎም የብሔራዊ ባንክ ገዥ አገር ወክሎ በዓለም አቀፍ መድረክ የመደራደር ሥልጣን የተሰጠው ግለሰብ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግሥት ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ግብዓት ሊሆን እንደሚችል ያሰምራሉ።
የአንድ አገር የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሹመት ከአገሪቱ አልፎ የሌሎችም ትኩረትን እንደሚስብ የሚናገሩት ዋሲሁን በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም “የብሔራዊ ባንክ ገዢ ተለወጠ የሚል ዜና እንጂ፣ የትራንስፖርት ወይም የግብርና ሚኒስትር ሹመት ትኩረት አያገኝም፥”
ለዚህም ምክንያቱ የማዕከላዊ ባንክ ገዢ መሾም የአገራት ምጣኔ ሃብት ላይ ዘዋሪ ብቻ ሳይሆን ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያለው በመሆኑ ነው ይላሉ።
ዋሲሁን እንደሚሉት ብሔራዊ ባንኩም ሆነ ገዢው ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ እና ገለልተኛ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ የገዢው የማስተዳደር አቅምም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት።
አብዱልመናን “ባንኩ ገለልተኛ ነው ማለት ተጠሪነቱ ለፓርላማ እና ለሕዝብ ይሆናል፤ ፖለቲካዊ ሹመት መሆኑ ቀርቶ በባለሙያ ይመራል ማለት ነው” ብለው ገለልተኛ የባንክ ሥርዓት የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል አይነተኛ ሚና እንዳለው ይጠቁማሉ።
አክለው ባንኩ ገለልተኛ ቢሆን ኖሮ የመንግሥት የገንዘብ ተቋማት እንደፈለጉ ከባንኩ መበደር አይችሉም ነበር ይላሉ።
“ይህ ማለት እንደተፈለገ ብር ማተም አይቻልም ማለት ነው። ገደብ ይበጅበታል። መንግሥት እንደፈለገ ብር አትም ብሎ አይጫንህም። ይህ ደግሞ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የተሻለ ሁኔታ ይፈጥራል።”












