ከጦርነቱ መቆም በኋላ “በደላሎች እየተቀጣን ነው” የሚሉት የመቀለ ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተለምዶ ቀበሌ 16 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የመቀለ ከተማ ደላሎች መናኸሪያ ሆኗል።
በአንድ ወቅት መቀለ ውስጥ ጭር ያለ የመኖሪያ አካባቢ የነበረው ይህ ቦታ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በበርካታ መጠጥ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች ተሞልቷል።
እዚህ አካባቢ በጣም አስፈላጊ መረጃ የፈለገ ሰው፣ እስከ ገዛ ገረላሰ ምግብ ቤት የሚወስደውን መስመር ተከትሎ መሄድ ይበቃዋል።
እዚህ አካበቢ ተቀምጠው የዕለት እንጀራቸውን የሚጋግሩ ደላሎች፣ የመቀለን ሸማች ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ።
የዕለታዊ ግብይቶች፣ የሸቀጦች ዋጋ እዚህ ይተመናል። የሰላም ድርድሩ የሚሄድበትን መንገድ አይተው ዋጋ የሚጨምሩ እና የሚቀንሱ ደላሎች የሚርመሰመሱበት አካባቢ ሆኗል ይላሉ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ።
“ሁኔታውን በማጥናት በከተማው ውስጥ የሸቀጦች እና አቅርቦቶች ዋጋ እንዲጨምር ወይም እንዲቀንስ ያደርጋሉ። በአጠቃላይ በዚህ የቀውስ ወቅት የትግራይ ኢኮኖሚ የሚወሰነው እዚያ ነው” ሲሉ አስተያየት ሰጪው ትዝብታቸውን ያጋራሉ።
በትግራይ ክልል የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት መከፈቱን ተከትሎ፣ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ከክልሉ እየተሰሙ ካሉ ቅሬታዎች መካከል አንዱ በንግድ ሥርዓቱ እና በፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ላይ ያለው ችግር ነው።
ቀደም ሲል በዋጋ ጭማሪ የተማረሩ የከተማዋ ነዋሪዎች “ከጥይት ቀጥሎ ሰውን እየገደለ ያለው ስግብግብ ነጋዴ ነው” ሲሉ ቆይተዋል።
“ነጭ ጤፍ በኪሱ ይዘው ይመጣሉ”
“መቀለ ድሮ እንደምትታወቀው አይደለችም” የሚለው የመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሸዊት ውዳሴ፣ በአሁኑ ወቅት “የጫማ እና የልብስ ጥያቄ ያለው ሰው የለም፤ አብዛኛው የምግብ ጥያቄ ነው ያለው” ሲል ያስረዳል።
አክሎም “ሁሉም ሰው ተጎሳቁሎ፣ ያለ ዕድሜው አርጅቶ ይታያል። የሕይወት ፈተናው ተጽእኖ ሰው ፊት ላይ ይነበባል፤ አሁን የመንግሥት ሠራተኛ የሚመስል ሳይቀር ነው እየለመነ ያለው” ይላል።
ለዚህም አንዱ ምክንያት የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ መናር እና የገንዘብ እጥረት መሆኑን ያስረዳል። በከተማው የምግብ ዋጋ እስከ 300 በመቶ የጨመረበት ጊዜ እንደነበር የሚናገረው መምህር ሸዊት፣ የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ “ተጠቅመው እየበለጸጉ ነው” የሚላቸውን “ነጋዴዎች” ይወቅሳል።
የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ ለማወቅ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የከተማው ነጋዴዎች እና ነዋሪዎች፣ የፌደራል መንግሥት እና የህወሓት አመራሮች ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በተለያዩ መንገዶች ብዛት ያለው አቅርቦት መታየቱን እና ገበያውም መጠነኛ መረጋጋት ማሳየት መጀመሩን ተናግረዋል።
ለዚህም ማሳያው፣ ለብዙዎቹ ከአቅም በላይ የነበረው የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ ከብር 17,000 ወደ 7,000፣ ዘይት ደግሞ ከብር 2,500 ወደ ብር 1,200 እና ከዚያ በታች እንደወረደ ገልጸዋል።
አሁንም ግን በሁሉም አቅርቦቶች ላይ ፍትሃዊ ያልሆኑ ዋጋዎች እንዳሉ የሚናገረው መምህር ሸዊት “ሕዝቡ ከሌለው ገንዘቡ ላይ እየተቀማ ነው። ሁኔታው የፈጠረው ነው ብለህ ዝም ማለቱ በጣም ከባድ ነው፤ የመንግሥት ድጋፍ ያላቸው ነው የሚመስሉት። ምክንያቱም እነሱ ካልገቡበት ይህ ሊፈጠር አይችልም” ይላል።
ሌላ የከተማው ነዋሪ የሆነች ነጻነት ክፍላይ “ለመኖር በጣም አስቸጋሪ የሆነበት ሁኔታ ውስጥ ነን ያለነው። አሁንም ሳንበላ የምናድርባቸው ቀናት አሉ። ገንዘብም ስለሌለን ገበያው እኛን አይመለከትም ማለት ይቻላል። ከዚህ በላይ የሚገልጸው ነገር የለም” በማለት አስተያየቷን ታካፍላለች።
በትግራይ ክልል ትክክለኛ የገበያ ሥርዓት አለመኖሩን ተከትሎ፣ ክልሉን የማስተዳደር ሕጋዊ ሥልጣን አለኝ በሚለው የትግራይ መንግሥት ውስጥ ያሉ ግለሰቦች እጃቸው አለበት በማለት ብዙዎቹ የክልሉን አስተዳደር ይወነጅላሉ።
“ይህን ሁሉ ያመጣው የንግድ ሥርዓቱ ነው፤ ለምሳሌ ነዳጅ መጥቶ እያለ ነዳጅ ይዘው የቆዩ ነጋዴዎች ሸጠው እስኪጨርሱ ድረስ እየጠበቋቸው ነው። ነጋዴው ማን ነው፥ ደላላው ማን ነው ተቀላቅሎ አደገኛ ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉ አቶ እያሱ አባይ ቅሬታቸውን ለቢቢሲ አካፍለዋል።
እያሱ አባይ ስሙ ተቀይሯል ነጋዴ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳለ፣ ነገር ግን የተለያዩ እቃዎች በብዛት እየገቡ መሆኑን ይጠቅሳል።
የመቀለ ከተማ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ በሪሁ ሃፍቱ እንደገለፁት፣ የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ከመደበኛው የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ያፈነገጠ ነው።
ነገር ግን ምክር ቤቱ ገበያውን ተቆጣጥረውታል እየተባሉ ያሉትን “ነጋዴዎች” ሊያውቃቸውና ጤናማ የገበያ ሥርዓት ሊፈጥር አልቻለም?
“በየትኛው አድራሻ እንወቃቸው? አሁን ነጋዴ ሆኖ ያለው የንግድ ፍቃድም ሆነ አድራሻ የሌለው ነው። አብዛኞቹ ነጭ ጤፍ ለማሳያ ኪሳቸው ውስጥ ይዘው ነው የሚዞሩት። ከዚያ እዚህ ቦታ ሄደህ ግዛ ይላሉ። ስለዚህ በቀጥታ ለመከታተል ትንሽ አስቸጋሪ ነው” ይላል አቶ በሪሁ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“የማይታይ መንግሥትማ ተመስርቷል”
በትግራይ ላለፉት 18 ወራት ከበባ እና የማኅበራዊ አገልግሎቶች መቋረጥ በነበረበት ወቅት በርካታ፣ መሠረታዊ አቅርቦቶች በኮንትሮባንድ ይገቡ እንደነበር ይገለጻል። ይህ ደግሞ ወደ ክልሉ የሚገባውን ገንዘብ ያካትታል።
ኮንትሮባንድ በሚካሄድበት ወቅት የትርፍ ተካፋዮች ስለሚኖሩ የዋጋ ጭማሪ ሊታይ ቢችልም እንኳ፣ ነጋዴው ብዙ ብር አውጥቶ በእጁ መያዙና እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በጥሬ ገንዘብ መሆኑ የሸቀጦችን ዋጋ እንዲጨምር እና የኑሮ ውድነትን እንዳባባሰው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡት የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ኃይሉ ከበደ፣ “የችግሩ መንስኤ ገዢው መዋቅር በጦርነት ወቅት ኢኮኖሚ እንዴት ይመራል የሚል አሰራር ስለሌለው ነው” ብለው ነበር።
“አሁን በዋነኛነት ገንዘብ የለም፣ የመንግሥት ሠራተኛ ደሞዝ የለውም። የግብይት ሥርዓቱ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከሥርዓቱ ጋር ግንኙነት ባላቸው ጥቂት ነጋዴዎች እና በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች እጅ ነው ያለው።
“ነጋዴው ሁሌም እንዲህ ዓይነት ሥርዓት አልበኝነት አለ ብሎ ንፋስ የሚያመጣቸውን ዕድሎች ነው የሚጠቀመው። በጦርነት ውስጥ ፀጥታን ማስከበር የሚችለው መንግሥት ነው” ብለዋል።
ጦርነቱ የገበያውን ፍላጎት ማሟላት የሚችል አስመጪ እና ጅምላ አከፋፋይ በቦታው እንዳይኖር በማድረጉ መደበኛ የንግድ ሥርዓት ተከትሎ የሚመጣ ሸቀጥ አልነበረም የሚለው የመቀለ ከተማ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በሪሁ ሃፍቱ በኮንትሮባንድ ንግድ እንዲሰማሩ መመርያ ተሰጥቶ እንደነበር ይጠቁማል።
“በከበባ ውስጥ ስለነበርን ለሕዝብ የሚጠቅም ሸቀጣ ሸቀጥ ይዞ መምጣት የሚችል አካል ካለ ማምጣት እንዲችል ከመንግሥት ጋር መግባባት ተፈጥሮ ነበር፤ በኮንትሮባንድ ማምጣት ይችላል የሚል መመሪያ ተፈቅዶ ነበር። በዚህ መልኩ ሸቀጦችን የሚያስገባው ግን የሚሸጥበትን ቦታ እና መጋዘኑን አላሳወቀም። ደላሎች እና ሌሎችም የተቆጣጠሩት ነበር፤ ይህ ደግሞ ለመቆጣጠርም ከባድ ነው” ይላል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ የገንዘብ እና የሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች እጥረት መኖሩ፣ የገበያው ፍላጎቱም ከፍተኛ መሆኑ በእንደዚህ ዓይነት ንግድ ላይ የሚሰማሩ ግለሰቦች እና ነጋዴዎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
እነዚህ መንግሥት የማይሰራው ነገር ሲኖር ወይም በአስተዳደራዊ እጥረት ምክንያት አቅርቦቶችን ማቅረብ ሳይችል ሲቀር የሚፈጠሩ ችግሮች እንደሆኑ ከዚህ በፊት ያነጋገርናቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወንጀል እና የፀጥታ ባለሙያ ተናግረዋል።
“ለምሳሌ ወደ የትኛውም አካባቢ አቅርቦት ሊገባ ካልቻለ ኮንትሮባንዲስቶች ይገባሉ፤ መንግሥትን ተክተው በመስራት ትርፋቸውን ይወስዳሉ። እንዲህ ያለ ችግር ሲፈጠር ተጠቃሚ አካላት ይፈጠራሉ፤ ሰው አማራጭ እንዲያጣ ያደርጉና ሳትወድ ወደእነሱ ንግድ ትገባለህ። ሁሉም ነገር በተዘጋበት ሁኔታ ደግሞ ለወንጀለኛ ሰጥተህ ሥራ መስራት የታለመ ይሆናል” ይላሉ ባለሙያው።
አንድ ነጋዴ ሌላውን ነጋዴ የዋጋ ጭማሪ እንዲያደርግ ሲያስገድደው የምታይበት፣ ገንዘብ የያዘ ተነጋግሮ ዋጋ የሚወሰንበት የገበያ ሁኔታ ተፈጥሮ እንዳለ መምህር ሸዊትም ይገልጻል።
“ነዳጅ የሚሸጡ ነጋዴዎች ሁሉም ስለሚተዋወቁ ጠዋት ጠዋት ተሰብስበው ዋጋ ይወስናሉ፤ ጤፍ እንደዚያው። አጋጣሚውን ተጠቅሞ የተጋነነ የገበያ ዋጋ እየጫነ ላለ ነጋዴ ሽፋን የሚሰጥ፣ እንዳላየ ሆኖ የሚያልፍ ምናልባትም በጥቅም የተሳሰረ አካል ያለ ይመስላል። ምክንያቱም የሚመለከተው ቢሮ ሥራውን ሰርቶ ሊከላከለው የሚችል ጉዳት ሆኖ ሳለ ሌላ የማይታይ መንግሥት ነው የተመሰረተው” ይላል።
የመንግሥት መዋቅር እና የሕግ ተቋማት መፍረስ ለእነዚህ ሕገወጥ ተግባራት መስፋፋት ምክንያት ሆኗል፣ ያለው አቶ በሪሁ ይህ ደግሞ በከተማዋ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ክትትል እና እገዛ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ይናገራል።
ምክር ቤቱ ነጋዴዎቹን የንግድ ፍቃድ እንዲያሳድሱ መጠየቅ እንዳልቻለ እና በዚህም ምክንያት ነጋዴው ከአባልነቱ እንደወጣ ይህም አሳሳቢ እንደሆነ ይጠቁማል። አሁን ለሕዝብ ምሬት መንስኤ የሆነው የዋጋ ጭማሪም የዚሁ ክፍተት ውጤት ነው ብሎ ያምናል።
“በሞተር ሳይክል እስከ አፋር መግቢያ ድረስ በመሄድ የገበያውን ሁኔታ በማጥናት ዋጋ የሚጨምሩ ደላሎች አሉ። እነዚህ መከታተል የሚችለው መንግሥት ነው፤ ቢያንስ ሠራዊት አለው። በዚህ መንገድ የሕዝቡን ምሬት መፍታት ይቻል ነበር። ነገር ግን የዚህ ሁሉ ውድቀት በሕዝቡ ላይ ችግር አስከትሏል” ይላል።
ገበያው እስኪረጋጋ ድረስ የሸማቾች ማኅበራት ሸቀጦችን የሚያስመጡበት ሁኔታ መፍጠር ጊዜያዊ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል የሚገልጸው ምክትል ፕሬዚዳንቱ “በዋናነት ሥርዓት ነው ሁሉንም የሚያድነው፤ ሥርዓት የሚፈጠርበት መንገድ መኖር አለበት” ይላል።












