ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በትግራይ የአመራር ለውጥ እንዲደረግ ጥያቄ አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, dw
የህወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በትግራይ ያለውን አመራር መልሶ ማዋቀር እንዲደረግ ጥያቄ አቀረቡ።
ክልሉን ሲያስተዳድር የቆየው የህወሓት ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረ ጽዮን ይህንን የተናገሩት በመካሄድ ላይ ባለውና “የክልሉ ምክር ቤት ስድስተኛ የሥራ ዘመን አምስተኛ መደበኛ ጉባኤ” በተባለው ላይ መሆኑን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
በክልሉ ዋና ከተማ እየተካሄደ ባለው ስብሰባ ላይ “አሁን የጀመርነው ሂደት ከከባድ ጦርነት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ የምንሸጋገርበት ነው። ይህ የሽግግር ጊዜ ደግሞ በጥንቃቄ መያዝ እና መመራት አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።
“ስለዚህ ሰላማችን ተጠብቆ እና ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችል መልሶ ማዋቀር ያስፈልጋል። በመሆኑም የህወሓት አባላትን እና የሌሎች የትግራይ ተወላጆችን አቅም ለመጠቀም የሚያስችል ማሻሻያ እንድናደርግ እንዲፈቅድ የተከበረው ምክር ቤት ኃላፊነት እንዲሰጥ እጠይቃለሁ” ብለዋል።
ደብረ ጽዮን ለምክር ቤቱ ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት የህወሓት ከፍተኛ የአመራር አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በአመራሩ መዋቅር ላይ ለውጥ የለም በማለት ከገለጹ በኋላ ነው።
ከቀናት በፊት አንስቶ በህወሓት ከፍተኛ የአመራር ቦታዎች ላይ ያሉ ቀደምት አባላት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች ሲወጡ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ዋነኛ የሚባሉት የቡድኑ መሪዎች ሥልጣን መልቀቃቸው በስፋት ሲነገር ነበር።
ነገር ግን የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ እሁድ ዕለት “ለትግራይ ሕዝብ ደኅንነት እና ህልውና አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች መሠረት ያረደገ ለውጥ ለማድረግ መግባባት አለ፤ አዲስ የተመሰረተ ካቢኔም ሆነ የተደረገ አዲስ አወቃቀር ግን የለም” ሲሉ በትዊተር ላይ ምላሽ ሰጥተው ነበር።
ለሁለት ዓመታት የቆየውን የእርስ በርስ ጦርነትን ለማብቃት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መሪዎች መካከል ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሠረት አወዛጋቢውን ክልላዊ ምርጫ ተከትሎ የተመሰረተው የትግራይ መስተዳደር ህልውና የሚያበቃ ይሆናል።
በዚህም በከባድ ጦርነት ውስጥ ባለፈችው የትግራይ ክልል ውስጥ ምርጫ ተካሂዶ የክልሉን አመራር የሚረከብ አካል አስኪቋቋም ድረስ በፌደራል መንግሥቱ አማካይነት ጊዜያዊ አስተዳደር እንሚመሰረት ይጠበቃል።
ትናንት ሰኞ ጥር 15/2015 ዓ.ም. መካሄድ በጀመረው የምክር ቤት ጉባኤ ላይ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም እና ሌሎች ጉዳዮች በማንሳት ደብረፅዮን ገ/ሚከኤል (ዶ/ር) ሪፖርት አቅርበዋል።
ሊቀመንበሩ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት፣ መብራት፣ ስልክ እና በመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማስጀመር በኩል መሻሻሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ የቀሩትም በአፋጣኝ በበቂ ሁኔታ ሥራ እንዲጀምሩ ጠይቀዋል።
የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ በአገሪቱ ሊካሄድ የነበረው ምርጫ እንዲረዘም ሲደረግ፣ ውሳኔውን በመቃውም የትግራይ ክልል የእራሱን የምርጫ አስፈጻሚ አካል አቋቁሞ ያካሄደው ምርጫ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የነበረውን ግንኙነት አበላሽቶች እንደነበር ይታወሳል።
ከዚህ ምርጫ ላለፉት 30 ዓመታት ክልሉን በብቸኝነት ሲመራ የነበረው ህወሓት አሸናፊ ነኝ ቢልም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው ሕገ ወጥ ነው በማለት ውጤቱን ውድቅ አድርጎ ከክልሉ መስተዳደር ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋርጦ ነበር።
ከዚያም ከጥቂት ወራት በኋላ ጦርነት ተቀስቅሶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን በሽብር ቡድንነት ሰይሞ መሪዎቹ ላይ ክስ መመስረቱ ይታወቃል።
ደም አፋሳሹ ጦርነት ለሁለት ዓመታት ከተካሄደ በኋላ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በተደረሰው ስምምነት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ተወስኗል።
የስብሰባው አጀንዳ ምንድን ነው?
በትግራይ ያለውን ሁኔታ እዚያው መቀለ ሆነው በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ጌታቸው አረጋዊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ስብሰባውን እያካሄዱ ያሉት በጦርነቱ ሂደት ከፍተኛ ኃላፊነት የነበራቸው፣ በቀጥታ ጦርነቱ የመሩ፣ ከአሁን በፊት አመራር ላይ የነበሩ ናቸው ይላሉ።
“በመንግሥትም በፓርቲም ውስጥ የነበሩ አንድ ላይ ተሰብስበው በአጠቃላይ ትግራይ አሁን ያለችበት ሁኔታ እና እየገባችበት ያለውን የለውጥ እና የሽግግር መድረክ ምን ይምሰል” የሚል አጀንዳ ላይ እየተወያዩ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ጉባኤ መሠረታዊ ለውጥ ይመጣል ብለው በርካታ ሰዎች እንደሚጠብቁ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው “አጠቃላይ ሁኔታውን እንዴት እንምራው? ማን ይምራው? ምንድን ነው? ወዴት አቅጣጫው ነው የምንሄደው? እንዴት ነው የምንሄደው? የሚለው መነሻ ተደርጎ አጠቃላይ የለውጥ ዝግጁነት እንዲኖር” የአመራሩ ፍላጎት መኖሩን ይጠቅሳሉ።
አቶ ጌታቸው እንደሚሉት በትግራይ እስካሁን ከነበረው ሁኔታ እና የፖለቲካ አወቃቀር አንጻር ጉልህ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ያምናሉ።
በዚህም የመንግሥት እና የፓርቲ ግንኙነት ምን ይሁን? ፓርቲ እና መንግሥት መለያየት ስላለባቸው ሁኔታ፣ አጠቃላይ ለውጥ እንዲካሄድ እና ከፓርቲ ውጪ የሆኑ ደግሞ ይህንን የለውጥ ሂደት እንዲመሩት፣ ይህንን ሂደት የሚመራ ሃሳብ እና አደረጃጀት ማምጣት አለብን የሚል አጀንዳ በጉባኤው ትኩረት ያገኙ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በትግራይ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ጌታቸው እንደሚሉት “እስካሁን ባለው ሁኔታ ዋናውን ለውጥ ህወሓት ሳይሆን ህወሓት ያልሆኑ ሰዎች የሚመሩት ቢሆን የሚል ሀሳብ አለ። ገና ወደ ድምዳሜ የተደረሰ ነገር ግን አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ስለዚህም የተለያዩ አካላት እየተሳተፉበት ባለው የምክር ቤቱ ስብሰባም ከዚህ መሠረታዊ የለውጥ ሂደት ጋር በተያያዘ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንጂ “እገሌ የቢሮ ኃላፊ ወይም ካቢኔ የሚለውን ለማጽደቅ አይደለም” ብለዋል።












