በየቀኑ በስልካችን የምንጭነው ፎቶና ቪድዮ የት ነው የሚቀመጠው?

ክላውድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቀን ስንት ጊዜ ስልክዎን ይመለከታሉ?

ዘንድሮ የተሠራ ጥናት አንድ ሰው በአማካይ 58 ጊዜ ስልኩን ይመለከታል ይላል። ከ58ቱ ጊዜ 30ው በሥራ ቦታ ነው የሚከናወነው።

ጥናቱ በ47 አገራት ነው የተሠራው። ሰዎች በየቀኑ በአማካይ ሦስት ሰዓት ከሩብ ስልካቸው ላይ እንደሚያጠፉ ይጠቁማል።

ስልካችን ላይ ከምናጠፋው ሰዓት አብላጫውን የሚይዙት ማኅበራዊ ሚዲያ መከታተል እንዲሁም ፎቶ እና ቪድዮ ማንሳት ናቸው።

ሌላ ጥናት እንደሚለው፣ በየሰከንዱ 45 ሺህ ፎቶዎች፣ በየሰዓቱ 196 ሚሊዮን ፎቶዎች፣ በየቀኑ ደግሞ 4.7 ቢሊዮን ፎቶዎች ይነሳሉ።

ይሄ ሁሉ ፎቶ የሚከማቸው በማይታየው፣ በማይዳሰሰው ክላውድ (cloud) ነው።

ክላውድ ፎቶ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ስልካችን ላይ የምንመዘግበውን መረጃ ያከማችልናል።

በ1960ዎቹ እንደተፈጠረ የሚነገርለት ክላውድ፣ በዋናነት አገልግሎት የሚሰጡት አፕል (አይ ክላውድ)፣ አማዞን (አማዞን ዌብ) ድሮፕቦክስ እና ጉግል ናቸው።

ክላውድ የመረጃ ክምችትን በምን መንገድ ለወጠ? የሚሠራውስ እንዴት ነው? ስንል የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ ወይም ኤአይ) ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው ብሩን ጠይቀናል። በኳንቲፊ የቴክኖሎጂ ተቋም የዓለም አቀፍ ጥናት እና ምርምር ዘርፍ መሪ ናቸው።

ክላውድ ምንድን ነው? ምንስ ይጠቅማል?

ዶ/ር ዳኛቸው እንደሚሉት፣ ክላውድ ከመፈጠሩ በፊት መሥሪያ ቤቶች በራሳቸው ማዕከላዊ የመረጃ ቋት (central server) ነበር መረጃ የሚያከማቹት። ይህ ማለት ሥራ የሚከናወነው፣ መረጃም የሚቀመጠው በመሥሪያ ቤት ኮምፒውተር ላይ ነው።

ግለሰቦችም መረጃ የሚያከማቹት በስልካቸው ወይም በላፕቶፓቸው ከፍ ሲልም ሀርድ ዲስክ ላይ ነበር።

እነዚህ ኤሌክትሮኒክሶች ይሞላሉ። ለመረጃ ምዝበራም ይጋለጣሉ።

እንደ አማዞን ያሉ ግዙፍ ተቋሞች ለሥራቸው የኮምፒውተር ስሌት (computation) ይፈልጋሉ።

ሰዎች በበይነ መረብ የሚያዙትን ምርት ለመከታተል፣ በቀጣይ ምን መግዛት እንዳለባቸው ለመጠቆምም ኮምፒውቴሽን ያስፈልጋቸዋል።

“. . .ብዙ ዳታ ሴንተር (የመረጃ ማዕከል) ዲስትሪብዩት አድርገው ማዘጋጀት ጀመሩ። ይሄንን የሚጠቀሙት ለበይነ መረብ ግብይት ነው። ከዚያ አዲስ የንግድ ሐሳብ አምጥተው [ሰርቨሩን] ለደንበኞቻቸው ማከራየት ጀመሩ” ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

ክላውድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የክላውድ ሐሳብ ከዚህ በፊትም ቢኖርም አማዞን የበለጠ ታዋቂ አድርጎታል።

ግለሰቦችና ተቋማትም በcloud computing አማካይነት መጠነ ሰፊ መረጃ፣ ዘለግ ላለ ጊዜ ያስቀምጣሉ።

በክላውድ መረጃ የሚከማቸው ኢንተርኔት በመጠቀም ሲሆን፣ መረጃው ከየትኛውም ቦታ፣ በየትኛውም ዓይነት ኤሌክትሮኒክስ፣ በማንኛው ጊዜ ይገኛል።

ክላውድ፣ መረጃ እንዳይጠፋ ወይም መረጃው የተመዘገበበት ኤሌክትሮኒክስ ቢጠፋ እንኳን መረጃውን በሌላ ኤሌክትሮኒክስ ለማግኘት ይጠቅማል።

ለምሳሌ ስልክ ስንቀይር በቀድሞ ስልካችን የነበሩት ምሥሎች፣ ጽሑፎች፣ ቪድዮዎች፣ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ልውውጦች፣ ስልክ ቁጥሮች እና ሌሎችም ጠቃሚ መረጃዎች ወደ አዲሱ ስልካችን ይሸጋገራሉ።

እንዲህ አይነቱን አገለግሎት በነጻ ከሚሰጡ መካከል ጉግል ድራይቭ፣ ድሮፕቦክስ እና ቦክስ ይገኙበታል። የሚያከማቹት መረጃ መጠን ከፍተኛ ነው። የመረጃ ምዝበራን ለመከላከል፣ መረጃ ደኅንነቱ ተጠብቆ ዘለግ ላለ ጊዜ እንዲቀመጥም ይረዳል።

“ክላውድ የሚባለው መረጃው ፊዚካሊ (በተጨባጭ) የት እንዳለ ስለማይታወቅ ነው። መረጃው የተቀመጠው ቴክሳስ ነው ወይስ ናይሮቢ ዳታ ሴንተር የሚለው አይታወቅም። መረጃው ብዙ ቦታ ይቀመጣል” ሲሉ ነው ዶ/ር ዳኛቸው የሚገልጹት።

ክላውድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቪድዮ፣ ድምጽ፣ ሰነድ እና ሌላም መረጃ ክላውድ ላይ እንዲከማች እንደ ማይክሮሶፍት እና ጉግል ያሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ይመክራሉ።

ዶ/ር ዳኛቸው እንደሚሉት ከመረጃ ክምችት ባሻገር ለኮምፒውቲንግ ሲባልም ክላውድ ጥቅም ላይ ይውላል።

“. . .ኤአይ የኮምፒውቲንግ ፓወር ማግኘት ነው። ሞዴሎችን ለማስተዋወቅና ለማሠልጠን የሚያስፈልገው የኮምፒውቲንግ ሪሶርስ ብዙ ነው። ለዚህም [መረጃውን ለማብላላት] የሚያስፈልገው ሪሶርስ ክላውድ ላይ ስላለ፣ ተከራይቶ መጠቀም ይቻላል። ክላውድ ላይ ዳታውም ኮምፒውቲንግ ሪሶርሱም አለ። ክላውድ እንዲሁ የተበተነ ነገር አይደለም። ሴንተሮች (ማዕከሎች) አሉት። ኮምፒውት የሚደረገው፣ እነዚያ ማዕከላት ላይ በኢንተርኔት አማካይነት ነው።”

ተቋሞች የራሳቸው የክምችት ማዕከል ማቋቋም እና ማስተዳደር የሚጠይቃቸውን ወጪ ለመቆጠብ ሲሉ ክላውድ ይከራያሉ።

መረጃ የሚቀመጠው አንድ ቋት ወይም ማዕከል ውስጥ ብቻ አይደለም። ኢንተርኔት እስካለ ድረስ፣ በማንኛውም ሰዓት፣ ከአንድ በላይ በሆኑ ኤሌክትሮኒክሶች ጭምር ማግኘት ይቻላል።

የተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እና የበይነ መረብ አገልግሎት ሰጪዎችም በተሻለ ፍጥነት እንዲሠሩ ክላውድ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ዶ/ር ዳኛቸው እንደሚሉትም፣ እነ ዩቲዩብ እና ፌስቡክ የመጡት ክላውድ በመኖሩ ነው።

መረጃ ከተለያየ ቦታ እንዲገኝ ማስቻሉ የቴክኖሎጂ ፍጥነት እየጨመረ እንዲሄድ ማገዙን ባለሙያው ያክላሉ።