በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዙት አባቶች ውሳኔውን ተቃወሙ

የተወደዙት ጳጳሳት

የፎቶው ባለመብት, socila media

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያኗን ቀኖና እና ሕግ ጥሰዋል ተብለው በመወገዝ እንዲለዩ የተወሰነባቸው አባቶች ውሳኔውን እንደማይቀበሉ አሳወቁ።

ከሳምንት በፊት ከአዲስ አበባ ውጪ በምትገኝ ቤተክርስቲያን ውስጥ 25 የኢጴሲ ቆጶስ ሹመትን የተቀበሉ እና ሹመቱን በሰጡ ጳጳሳት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሐሙስ ዕለት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ አውግዞ ከቤተክርስቲያኗ እንዲለዩ መወሰኑ ይታወቃል።

በቤተክርስቲያኗ ላይ “መፈንቅለ ሲኖዶስ” ሞክረዋል የተባሉት አባቶች አርብ ዕለት ጥር 19/2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ አስራ ሁለት የሚደርሱ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን ስብሰባውን በማሳሳት በምዕመኑ ላይ “ግራ መጋባትን ፈጥረዋል” ሲል ከሷል።

በዚህም መሠረት የተላለፈባቸውን ውግዘት እና ከቤተክርስቲያኗ የለመለየት ውሳኔ በመቃወም እንደማይቀበሉት በመግለጽ በያዙት ዕቅድ መሠረት እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል።

በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ለተፈጠረው ለዚህ ቀውስ ምክንያት የሆነው ክስተት በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ውስጥ ወሊሶ አቅራቢያ ሶዶ ዳጬወረዳ ሐሮ በዓለ ወልድ ቤተክርስቲያን ውስጥ እሁድ ጥር 14/2015 ዓ.ም. 26 የጳጳሳት ሹመት ከፓትሪያርኩም ሆነ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጪ መሰጠቱ ነበር።

ከሕግ ውጪ ተደረገ በተባለው ሂደት ከተሰየሙት ጳጳሳት መካከል አንደኛው ይቅርታ በመጠየቅ መመለሳቸውን የቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ይህ በዋናነት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንዲሁም በአንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ያገለግላሉ ያሏቸውን ኤጲስ ቆጶሳትን በመሾም የውዝግቡ መነሻ የሆኑት አባቶች፣ ቤተክርስቲያኗ አካታች አይደለችም ምዕመናን በቋንቋቸው የእምነቱን ሥነ ሥርዓት እንዲፈጽሙ አላስቻለችም በማለት እርምጃውን መውሰዳቸውን ይናገራሉ።

ይህንንም ተከትሎ በፓትሪያርኩ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሐሙስ ጥር 18/2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ድርጊቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት፣ የቀኖና እና የአስተዳደራዊ ጥሰቶች የሚፈጽም መሆኑን በመግለጽ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።

በዚህም የጵጵስና ሹመት የሰጡ እና የተቀበሉ አባቶች የቅርታ ጠይቀው እስኪመለሱ ድረስ የክህነት ሲመታቸው ተገፎ ከቤተክርስቲያኗ ተወግዘው እንዲለዩ ተወስኖባቸዋል።

እስካሁን በግለሰብ ደረጃ ጥቂት የመንግሥት ባለሥልጣናት በክስተቱ ላይ አስተያየት የሰጡ ቢሆንም፣ ከመንግሥት በኩል ግን ምንም አይነት አስተያየት አልተሰጠም።