በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስለተከሰተው ሁኔታ እስካሁን የምናውቀው

መስቀል የያዘ ዲያቆን

የፎቶው ባለመብት, Mahibere Kidusan/fb

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከእውቅናዬ ውጪ ተሰጥቷል ያለችውን የጳጳሳት ሹመት ተከትሎ ጥር 18/2015 ዓ.ም ውሳኔ አሳልፋለች።

በፓሪያሪኩ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ጵጵስና ሹመት የሰጡ እና የተቀበሉ አባቶች ከቤተክርስቲያኒቷ ተወግዘው እንዲለዩ ወስኗል።

በዚህም አባ ሳዊሮስ፣ አባ አዎስጣጤዎስ እና አባ ዜናማርቆስ ከድቁና ጀምሮ ያለው ክህነተ ሥልጣናቸውን አንስቶ ያወገዘ ሲሆን፣ ሕገ ወጥ ሹመቱን የተቀበሉ 25 መነኮሳት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአንድነት ጉባኤ ተለይተው እንዲወገዙ ወስኗል።

ይህንን ውሳኔም ተከትሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያኗን ቀኖና እና ሕግ ጥሰዋል ተብለው በመወገዝ እና እንዲለዩ የተወሰነባቸው አባቶች ውሳኔውን እንደማይቀበሉ አሳውቀዋል።

ያልተጠበቀው ክስተት

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ውስጥ ወሊሶ አቅራቢያ ሶዶ ዳጬ ወረዳ ሐሮ በዓለ ወልድ ቤተክርስቲያን ውስጥ እሁድ ጥር 14/2015 ዓ.ም. 26 የጳጳሳት ሹመት ከፓትሪያርኩም ሆነ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጪ መሰጠቱ ተሰማ።

ይህንን ሹመት ያካሄዱት አባቶች የሚመሩት በአባ ሳዊሮስ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኗ አካታች አይደለችም እና ምዕመናን በቋንቋቸው የእምነቱን ሥነ ሥርዓት እንዲፈጽሙ አላስቻለችም በማለት እርምጃውን መውሰዳቸውን ይናገራሉ።

ይህንንም ተከትሎ በፓትሪያርኩ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሐሙስ ጥር 18/2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ድርጊቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት፣ የቀኖና እና የአስተዳደራዊ ጥሰቶች የሚፈጽም መሆኑን በመግለጽ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም የጵጵስና ሹመት የሰጡ እና የተቀበሉ አባቶች ይቅርታ ጠይቀው እስኪመለሱ ድረስ የክህነት ሲመታቸው ተገፎ ከቤተክርስቲያኗ ተወግዘው እንዲለዩ ወስኗል።

ሦስቱ የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው የተላለፈባቸውን ውግዘት እና ከቤተክርስቲያኗ የመለየት ውሳኔ በመቃወም እንደማይቀበሉት በመግለጽ በያዙት ዕቅድ መሠረት እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል።

ሹመቱ እና ያስከተለው ውጤት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሲኖዶስ ላይ ያላቸውን ጥያቄ አቅርበው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ያካሄዱት አባቶች አቡነ ሳዊሮስ፣ አቡነ ዜና ማርቆስ እና አቡነ ኤዎስጣጤዎስ ናቸው።

ለዚህ እርምጃቸው እንደ ምክንያት የጠቀሱት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር አልቻልንም፣ ሲኖዶሱ ከአንድ አካባቢ ብቻ የተዋቀረ ነው የሚል ነው።

ይህም በርካታ ምእመናን ከቤተክርስቲያኗ እንዲርቁ እያደረገ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ለዚህም እንደ መጀመሪያ እርምጃ የቤተክርስቲያኗን ሥርዓት የጣሰ ነው በተባለው ሁኔታ በአብዛኛው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለሚገኙ እና ለተወሰኑ የደቡብ ክልል አካባቢዎች 26 ኤጲስ ቆጰሳት ሹመዋል።

ነገር ግን አንደኛው አባት እራሳቸውን በማግለል ይቀርታ በመጠየቅ መመለሳቸው ተዘግቧል።

ይህንንም ተከትሎ የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በአባ ሳዊሮስ መሪነት የተፈጸመው ድርጊት “የቤተ ክርስቲያኗን ቀኖና የጣሰ፣ ሃይማኖትን የሚከፋፍል፣ የአገር አንድነትን የሚሸረሽር እና የሚያፈርስ፣ ምእመናንን ከምእመናን፣ ካህናትን ከካህናት፣ ሊቃውንትን ከሊቃውንት…የሚያጋጭ ነው” በማለት አውግዞታል።

በተጨማሪም ሹመቱን የሰጡትን ሦስት ጳጳሳት እና 25 አባቶችን ሥልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ “በሕይወትም ሆነ በሞት” ከቤተክርስቲያኗ አገልግሎት በማውገዝ እንዲገለሉ ወስኗል።

የተወገዙት አባቶችም በቅዱስ ሲኖዶሱ የተላለፈባቸውን ውሳኔ በመቃውም እነሱም በበኩላቸው ውግዘትን በማውጣት፣ በያዙት ዕቅድ መሠረት ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል።

ይህ ሁኔታ እስካሁን ድረስ የእምነቱ ተከታዮች ባሻገር፣ የሌሎችም ሰዎች ዋነኛ የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።

በክስተቱ እና በተላለፈው ውሳኔ ዙሪያ ከተለያዩ ወገኖች የተቃውሞ እና የድጋፍ ሃሳቦች እየተሰነዘሩ ነው።

ክስተቱ ያስከተለው ስጋት

ምንም እንኳ ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት ባይችልም በአቡነ ሳዊሮስ ከተሾሙ ጳጳሳት መካከል የተወሰኑት ወደ ምድባቸው መንቀሳቀስ መጀመራቸው ይነገራል።

የቤተክርስቲያኗ መሪዎች እና ሌሎችም ይህ ሁኔታ ወዳልታሰበ አቅጣጫ እንዳያመራ እና ግጭት እንዳይፈጠር ስጋት ተፈጥሮባቸዋል።

ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ መንግሥት እሁድ ጥር 21/2015 ዓ.ም. ለመንግሥት እና ለሕዝቡ ሕግ እንዲከበር እና የሁሉም ደኅንነት እንዲጠበቅ በቤተክርስቲያኗ የመገናኛ ብዙኃን በኩል ጥሪ አቅርበዋል።

አቡነ ማትያስ በዋናነት ባስተላለፉት መልዕክት አደራ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግ እና ሥርዓት እንዲከበር እና “ፀጥታ እንዳይደፈርስ እና የንጹሐን ክርስቲያን ደም እንዳይፈስ ከወዲሁ ብርቱ ጥንቃቄ የተመላበት ጥበቃ እንዲደረግ በእግዚአብሔር ስም በአጽንዖት እንጠይቃለን” ብለዋል።

በቤተክርስቲያኗ በኩል ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ለጥበቃ ተሰማርቶ የነበረው የፖሊስ ኃይል ተነስቶብናል የሚል ክስ ቀርቦ የነበረ ሲሆን፣ ቢቢሲ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ጠይቆ የተነሳ የፖሊስ ጥበቃ እንደሌለ እና አስፈላጊ በሚሆንበት እንዲሁም ጥያቄ ሲቀርብ ፖሊስ እንደሚሰማራ ተገልጿል።

ቅዳሜ ዕለትም የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ በጅማ አገረ ስብከት ከ20 ዓመታት በላይ ያገለገሉት አቡነ እስጢፋኖስ በፖሊስ ከጅማ ከተማ እንዲወጡ ተደርጓል ሲል የሲኖዶሱ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

እንደ ዘገባው ከሆነ ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ ከጅማ እንዲወጡ የተገደዱት፣ “በፖሊስ ታስረው ከዋሉ በኋላ” ነው።

በተጨማሪም “መፈንቅለ ሲኖዶስ” አድርገዋል ከተባሉት አባቶች ጋር ሕገወጥ ሹመት ከተሰጣቸው በኋላ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ሲኖዶሱ የተመለሱት መጋቤ ሐዲስ አባ ጸጋዘዓብ አዱኛ ደሞ፣ ከመንበረ ፓትርያርኩ ግቢ ተይዘው ወዳልታወቀ ሥፍራ ከተወሰዱ በኋላ መለቀቃቸው ተሰምቷል።

ማን ምን አለ?

የ26ቱ ጳጳሳት ሹመት እነደተሰማ በቀዳሚነት ሀሳባቸውን በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ያሰፈሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ናቸው።

“የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በዘር ለመክፈል የተኬደው ርቀት አደገኛም አሳዛኝም ነው” ያሉት የተከበሩ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጨምረውም “ሕገ ወጥ የጳጳሳት ሹመት ገጠር ውስጥ ተደብቆ በመፈጸም ታሪክ ይቅር የማይለው ኃጢአት ተሠርቷል” ብለዋል።

ዲያቆን ዳንኤል ለተፈጸመው የቀኖና ጥሰት “የመጀመሪያው መፍትሔ ሦስቱን ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ጠርቶ ማነጋገር ቢሆን ጥሩ ነው” በማለት ዝርዝር ጉዳዮችን መመርመር በቀጣይ የሚወሰዱ መፍትሔዎች ከዚህ ውይይት ከሚገኝ ውጤት መነሳት አለበት ሲሉ ምክር ሰንዝረው ነበር።

ክስተቱን ለማስቆም የሚችሉ አካላት “ለማስቆም ባለመፈለጋቸው በሰማይም በምድርም ተጠያቂ ናቸው” ሲሉ በውል ያልጠቀሷቸውን አካላትም ወቅሰዋል።

እንዲሁም የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) “ከምድራዊም ሆነ መንፈሳዊ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ትውፊት እና ቀኖና ጋር የሚጋጭ የትኛውም ድርጊት መጨረሻው የሰመረ ሊሆን አይችልም” በማለት አባቶች በትዕግሥት እና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ችግሩን ይፈቱታል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ከዚህ ውጪ ግን መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር ጥያቄ እየቀረበለት ቢሆንም፣ ከየትኛውም የመንግሥት አካልም ሆነ ባለሥልጣን ይህንን በርካቶችን ስላሳሰበ ጉዳይ የመንግሥትን አቋም የሚያንጸባርቅ በይፋ የተሰጠ አስተያየትም ሆነ መግለጫ አልተሰማም።