የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥትን መግለጫ ተቃወመች

የፎቶው ባለመብት, MAHIBERE KIDUSAN/FB
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት እሁድ ጥር 28/2015 ዓ.ም. ያወጣውን መግለጫ አጥብቃ ተቃወመች።
ከቤተክርስቲያኗ እውቅና ውጪ የተፈጸመውን የጳጳሳት ሹመት ተከትሎ በተከሰተው ችግር ዙሪያ ምንም ሳይል የቆየው መንግሥት ያወጣው መግለጫ ተቃውሞ ገጥሞታል።
ቤተ ክርስቲያኗ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መግለጫ “የቤተ ክርስቲያኗን ክብር፣ ታሪክ እና እውነታ ቸል በማለት በጉዳዩ ላይ የተሟላ መረጃ የሌላቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ የሚያደርግ ነው” ብላለች።
የፌደራሉ መንግሥት እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው “መለያየት” በውይይት እና በቤተ ክርስቲያኒቱ አሠራር መሠረት መፈታት አለበት ብሎ ነበር።
በቤተ ክርስቲያኗ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በኩል በተሰጠው ምላሽ “በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች መካከል የተፈጠረ መለያየት የለም” ካለ በኋላ በመንግሥት የተሰጠው መግለጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ያወገዘቻቸውን ግለሰቦች ሕጋዊ አካል አድርጎ እውቅና የሚሰጥ ነው ብሏል።
ባለፉት ቀናት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እውቅና ውጪ የተሰጠ ሹመትን ተከትሎ አለመግባባቶች መፈጠራቸው ይታወሳል።
ይህ አለመግባባት የተፈጠረው በኦሮሚያ ክልል ከፓትሪያርኩም ሆነ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጪ የ26 ጳጳሳት ሹመት መሰጠቱ ከተሰማ በኋላ ነበር።
ይህንን ሹመት የሰጡት አባቶች "ቤተክርስቲያኗ አካታች አይደለችም እና ምዕመናን በቋንቋቸው የእምነቱን ሥነ ሥርዓት እንዲፈጽሙ አላስቻለችም" በማለት እርምጃውን መውሰዳቸውን ይናገራሉ።
በፓትሪያርኩ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሐሙስ ጥር 18/2015 ዓ.ም. ባካሄደው ጉባኤ ድርጊቱ በቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖት፣ ቀኖና እና አስተዳደርን የሚጥስ ነው በማለት ሹመቱን የሰጡ እና የተቀበሉትን አውግዞ እንዲለዩ አድርጓል።
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን በእሁድ ዕለት መግለጫው መገናኛ ብዙኃን በጉዳዩ ላይ ዘገባ ሲሰሩ “ችግሩን ከሚያባብሱ ነገሮች መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል” በማለት አሳስቧል።
ቤተ ክርስቲያኗ ግን መንግሥት የሲኖዶሱን ድምጽ አፍኖ የሲኖዶሱ መግለጫዎች በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንዳይተላለፍ ካደረገ በኋላ፤ ህሊናዊ እና ሕጋዊ ተግባራቸውን እየፈጸሙ በሚገኙ የሚዲያ አካላት ላይ የማስፈራሪያ መግለጫ በመስጠት ድምጽ ለማፈን የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ብሏል።
ጨምሮም በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ በተፈጠረው አለመግባባት ጉዳይ መንግሥት ገለልተኛ ነኝ ማለቱን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ቤተ ክርስቲያኗ አትቀበለውም ብሏል።
መንግሥት በቃሉ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አልገባም ይበል እንጂ፤ በተግባር ግን “ለሕገ-ወጦቹ ስብስቦች” ድጋፍ ከመስጠት አልተቆጠበም ብሏል።
ከዚሁ ቀውስ ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት ውስጥ በተፈጠሩ ችግሮች በሰው ሕይወት እና አካል ላይ ጉዳት መድረሱ ተዘግቧል።
እስካሁንም ቢያንስ ሦስት የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን በፀጥታ ኃይሎች እርምጃ መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ የሚገኙም እንዳሉ ቤተክርስርስቲያኗ ገልጻለች።
በሕዝብ ግንኙነት በኩል የወጣው የቤተከርስቲያኗ መግለጫ፣ ለእምነቱ ተከታዮች ግድያ መንግሥትን ተጠያቂ ከማድረጉ በተጨማሪ “ለሕገ ወጥ ቡድኖቹ በመሳሪያ የታጀበ ድጋፍ በመስጠት እና ቤተ ክርስቲያንን በማስወረር” መንግሥትን ኮንኗል።
የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ከመንግሥት በኩል በይፋ የተሰጠው የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች መግለጫ፣ “የፀጥታ አካላት የሕዝብ እና የእምነት ተቋማት ሰላም እና ፀጥታ ማስከበር ግዴታቸው ነው” ብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኗ መንግሥት “በወገንተኝነት የምእመናንን ሕይወት እየነጠቀ ነው” ካለች በኋላ በመግለጫው በሻሸመኔ ከተማ በፀጥታ ኃይሎች የተፈጸመውን “ጭካኔ የተሞላበት የአደባባይ ግድያ እና የሕዝብ ፍጅት ያልጠቀሰ እና ሐዘኑን እንኳን መግለጽ ያልቻለበት እና ያላወገዘ መሆኑን ስንመለከት የመንግሥትን ግልጽ ሚና በቀላሉ ለመረዳት እንድንችል ያደርገናል” ብላለች።
በመጨረሻም ሥልጣንን ተገን በማድረግ የቤተ ክርስቲያኗን “ሕጋዊ ጥያቄ በግድያ፤ በእስር፤ በማዋከብ እና በማስፈራራት ሊፈታ” ስለማይችል መንግሥት የተጣለበትን መንግሥታዊ ኃላፊነት መወጣት የሚችለው ያለ አድሎ ሲሰራ ብቻ ነው ብሏል።
የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባዘዘው መሠረት ከዛሬ ጥር 29/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚኖረው የነነዌ የጸሎት መርሐ ግብር ላይ ምዕመናን ጥቁር የሐዘን ልብስ በመልበስ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እየተሰባሰቡ ነው።












