በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጥቁር በመልበሳቸው ምክንያት ‘አገልግሎት ተነፈግን’ አሉ

የፎቶው ባለመብት, EOTC Broadcasting Service Agency
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ ሰኞ ጥር 29/2015 ዓ.ም. ከተጀመረው የነነዌ ጾም ጋር ምዕመናን ጥቁር በመልበስ ምህላ እንዲያደርጉ ባዘዘችው መሠረት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርካታ ሰዎች ይህንን እየፈጸሙ ነው።
ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የታወጀው ከሁለት ሳምንት በፊት ከቤተክርስቲያኗ ሕግ እና ሥርዓት ውጪ ነው በተባለ ሁኔታ ሦስት ጳጳሳት 26 ኢጲስ ቆጶሳትን መሾማቸውን ተከትሎ ያጋጠሙ ክስተቶችን መሠረት በማድረግ ነው።
ነገር ግን ይህንን የሲኖዶሱን ትዕዛዝ ተግባራዊ ያደረጉ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ወከባ እና እንግልት እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች በፀጥታ ኃይሎች መታሰር እንዳጋጠመ የቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አንዳንድ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ሠራተኞቻቸው ጥቁር ልብስ እንዳይልብሱ በቃል እና በጽሁፍ እያስታወቁ መሆናቸውን እንዲሁም ጥቁር የለበሱ ተገልጋዮችን አናስተናግድም ያሉም እንዳሉ ቢቢሲ ያናገራቸው ሰዎች ገልጸዋል።
ለቢቢሲ ቃላቸው የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጥቁር ልብስ በመልበሳቸው ምክንያት አገልግሎት ፍለጋ ወደ ሄዱባቸው የመንግሥት ተቋማት መግባት ጭምር መከልከላቸውን ተናግረዋል።
ነዋሪዎች በልብሳቸው ቀለም ምክንያት አገልግሎት እንዳያገኙ ከልክለውናል ካሏቸው ተቋማት መካከል የክፍለ ከተሞች ጽህፈት ቤቶች፣ የገቢዎች ቢሮ እና የወረዳ ፖሊስ ጣቢያዎች ይገኙበታል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጥቁር ልብስ የለበሱ ሰዎች እስራት፣ አንግልት እና መዋከብ እየተፈጸመባቸው ነው ብሏል።
ይህ ጥቁር የመልበስ ውሳኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የመንግሥት ድጋፍ አላቸው ያላቸውን አባቶች አውግዞ ከለየ በኋላ፣ አጋጥሟል ያለውን ፈተና ምዕመናኑ ጥቁር በመልበስ አስከ ረቡዕ የካቲት 01/2015 ዓ.ም. ድረስ በጾም እና ጸሎት ከቤተ ክርስቲያን ጎን እንዲቆሙ ነው ጥሪ ያስተላለፈው።
ይሁን እንጂ የቤተ ክርስቲያን ጥሪ በመቀበል ጥቁር ከለበሱት መካከል ለቢቢሲ የተናገሩ የእምነቱ ተከታዮች፤ አገልግሎት ፍለጋ በሄዱባቸው መንግሥታዊ ተቋማት እንዳይገቡ መከልከላቸውን ገልጸዋል።
ወቅታዊውን የቤተክርስቲያኗን ጉዳይ ይዘው በፍርድ ቤት እየተከራከሩ ያሉት የሕግ ባለሙያው አንዷለም በዕውቀቱ ገዳ እንደሚሉት፣ ሰዎችን በለበሱት የልብስ ቀለም ማዋከብ የሰብዓዊ መብት ጥስት ነው።
“ጥቁር በመልበሳችን አገልግሎት ተነፈግን”
የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ነዋሪ የሆኑት አቶ ይልማ ሰኞ ጥር 29/2015 ዓ.ም. በጃንሜዳ ማኅበረሰብ ፖሊስ ጣቢያ በነበራቸው ቀጠሮ መሠረት ወደ ፖሊስ ጣቢያው ቢሄዱም “ጥቁር በመልበሴ አገልግሎት ማግኘት አልቻልኩም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በር ላይ የነበረች የፖሊስ አባል ያለምንም መሸፋፈን ነበር በለበስኩት የልብስ ቀለም ምክንያት ወደ ፖሊስ ጣቢያው መግባት እንደማልችል እቅጩን የነገረችኝ።”
አቶ ይልማ እንደሚሉት ጥቁር በመልበሳቸው ወደ ፖሊስ ጣቢያው እንዳይገቡ የተከለከሉት እርሳቸው ብቻ አይደሉም፤ ሌሎችም ሰዎች ሲጉላሉ ተመልክተዋል።
“ይህ ነገር የተከሰተው በእኔ ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ለጉዳይ የመጡ ሰዎች ሲመለሱ ተመልክቻለሁ” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፣ የእርሳቸው ጉዳይ አስቸኳይ ስላልሆነ በሌላ ቀን ለመምጣት በመወሰን መመለሳቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ መንግሥታዊ አገልግሎት ፍለጋ ከሄዱበት የቦሌ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ጥቁር በመልበሳቸው ብቻ ከበር እንዲመለሱ ተደርገዋል።
እኚህ ነዋሪ ወደ መንግሥታዊ ተቋሟ መግባት ያልቻሉት ጥቁር ልብስ በመልበሳቸው መሆኑን ሲነገራቸው ማመን እንዳልቻሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ ከአዲስ አበባ በምሥራቅ አቅጣጫ በኦሮሚያ ክልል ወደምትገኘው ለገ ጣፎ ለገ ዳዲ ከተማ መግቢያ ላይ የክልሉ ፖሊስ ጥቁር የለበሱ ተሳፋሪዎችን እየለየ ከመኪና ያስወርድ እንደነበረ ገልጸዋል።
ኢሰመጉ በበኩሉ ሰዎች በለበሱት የልብስ ቀለም እንግልት፣ እስራት እና ማዋከብን እየፈጸሙ ያሉት ተቋማት እና ደርጅቶች ናቸው ያለ ሲሆን፣ ሁኔታው ተባብሶ የሰው እና ንብረት ጉዳት ከማስከተሉ በፊት የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
“የሕግ ጥሰት ነው”
በለበሱት የልብስ ቀለም አይነት ብቻ ሰዎች መዋከብ የለባቸውም የሚሉት የሕግ ባለሙያው አንዷለም በዕውቀቱ፤ “ሰዎች ጥቁር መልበሳቸው የሃይማኖት ግዴታቸው እንዲሁም ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው ነው” ሲሉ ይናገራሉ።
“የሃይማኖቱ ተከታዮች ጥቁር እንዲለብሱ በቅዱስ ሲኖዶስ ትዕዛዝ እስከተሰጣቸው ድረስ ይህን ትዕዛዝ አማኞች መከተል አለባቸው” የሚሉት የሕግ ባለሙያው፤ አማኞች ይህን የማድረግ መብታቸው ደግሞ በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 27 ላይ ተደንግጓል ይላሉ።
በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 27 የሃይማኖት፣ የእምነት እና የአመለካከት ነጻነት ተደንግጓል። አንቀጽ 27 ንጹስ አንቀጽ 1፣ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል . . . የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል ይላል።
የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት በአገሪቱ ሕግ መሠረት አማኞችን ጥቁር ልብስ እንዳይለብሱ ማድረግ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ነው።
አንዷለም ጥቁር ልብስ አትለብሱ ባሉ የግል እና የመንግሥት ተቋማት ላይ ክስ ለመመስረት ከተበዳዮች መረጃዎችን እያሰባሰቡ እንደሆነም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ከ20 የማያንሱ ሰዎች ተከልክያለሁ [ጥቁር ልብስ እንዳለብስ] ያሉ ሰዎች መልዕክት ልከውልኛል” ያሉት የሕግ ባለሙያው ክልከላ አድርገዋል የተባሉት መሥሪያ ቤቶች ከፌደራል እስከ የግል ተቋማት ድረስ እንደሚገኙበት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።












