በሻሸመኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተከሰተው ምንድን ነበር?

ቤተክርስቲያን

የፎቶው ባለመብት, FRANOL MOSES

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ በተፈጠረ ውዝግብ ምክንያት የሰው ሕይወት መጥፋቱ እና የአካል ጉዳት መድረሱ ተገለጸ።

ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሕግ ውጪ ነው ባለችው ሁኔታ ሹመት የተቀበሉ አባቶች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ወዳሉ አብያተክርስቲያናት በሚያቀኑበት ጊዜ ነው በተፈጠረ ግጭት ጉዳት የደረሰው።

ውዝግቡን ተከትሎ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የቤተክርስቲያኗ አባቶች፣ ሠራተኞች እና ምዕመናን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እንግልት እና እስር እየገጠማቸው መሆኑን ስትገልጽ ቆይታለች።

ባለፈው ቅዳሜ ጥር 27/2015 ዓ.ም. ደግሞ ሻሸመኔ ውስጥ በተከሰተው ሁከት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዷቸው እርምጃዎች በቤተክርስቲያኗ አባላት ላይ የሕይወት እና የአካል ጉዳት መድረሱ ቤተክርስቲያኗ አሳውቃለች።

ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በምዕራብ አርሲ አገረ ስብከት በሻሸመኔ ከተማ በደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ላይ “መንግሥትን ተገን ያደረጉ ናቸው” ያላቸው ግለሰቦች ወረራ ለመፈጸም ሙከራ ማድረጋቸውንም ገልጾ ነበር።

ጨምሮም ይህንን ለመከላከል እና ቤተ ክርስቲያኗን ለመጠበቅ በወጡ ምእመናን ላይ “ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የአደባባይ የግድያ ወንጀል ተፈጽሟል” በማለት ቁጥራቸው ያልታወቁ ምእመናን ላይ ከፍተኛ እና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን አመልክቷል።

ከቤተክርስቲያኗ በኩል በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደባቸው እርምጃ ሕይወታቸው ስላለፈ ሰዎች ቁጥር የተጠቀሰ ባይሆንም፣ ከተለያዩ ምንጮች የሚወጡ መረጃዎች ከሦስት ጀምሮ የተለያዩ አሃዞች እየተጠቀሱ ነው።

ባለፈው ቅዳሜ የፈረንሳይ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የዘገበ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተገድለዋል በሚል ምስላቸው የሚዘዋወሩ ሰዎች ቁጥር በርካታ ነው።

ነገር ግን ቢቢሲ ይህንን አሃዝ ከቤተክርስቲያኗ ለማረጋገጥ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቅዳሜው ዕለት ክስተት በሻሸመኔ ከተማ ምዕመናን በፀጥታ ኃይሎች እርምጃ መገደላቸው ቢገለጽም፣ የከተማው የፀጥታ ኃላፊዎች ግን እጃችን የለበትም ብለዋል።

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የፕሮጀክቶች መምሪያ ኃላፊ የሆኑት መላከሕይወት ቆሞስ አባ ወልደእየሱስ ሰይፉ ግን ይህንን የፀጥታ ኃላፊዎች ምላሽ ነቅፈዋል።

“የተገደሉት ሰዎች ብዙ ናቸው። እስካሁን አስክሬናቸው የተገኘው አምስት ናቸው። ግድያውን የፈጸሙት ልዩ ኃይልና የሻሸመኔ ከተማ ፖሊስ ናቸው።" በማለት የተናገሩት አባት አክለውም

“ከተገደሉት ውጭ የተጎዱ በቁጥር አልታወቁም። እግሩ የተሰበረ፣ እጃቸውና ጭንቅላታቸውን የተመቱም በሆስፒታል ህክምና እያገኙ ነው። በመንግሥት በኩል ሐሰት መናገራቸው የተለመደ ነው” ብለዋል።

ኃላፊው “ቤተ ክርስቲያን የሚሄድ ሰው ትጥቅ አለው እንዴ? እዚህ አገር ትጥቅ ያለው ፖሊስ አይደለም እንዴ? አስታጥቆ የላከው መንግሥት አይደለም እንዴ? ለምን እንዲህ ይዋሻሉ? " ሲሉም ወቅሰዋል።

ፖሊሶች ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲደብድቡ መታየታቸውን የገለጹት ኃላፊው ለዚህም የቪድዮ ማስረጃ እንዳለ ተናግረዋል።

“የገደሉት ራሳቸው ናቸው። ከቤተ ክርስቲያኑ ጀርባ ካለ አንድ ኮንዶሚንየም ሕንጻ መስኮት ከፍተው ሽጉጥ ሲተኩሱ መረጃ አለን” ሲሉ ለቢበሲ ተናግረዋል።

በዕለቱ ወንድሙ የተጎዳበት እና ስሜ አይጠቀስ ያለ የከተማዋ ነዋሪም ለተፈጠረው ጉዳት ፖሊስን ተጠያቂ አድርጓል።

“ጠዋት ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሄዶ ነው ይህ የተፈጠረው። ስለከበቡን ከቤተክርስቲያንም መውጣት ሳንችል እዛው ዋልን። ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ከቤተክርስቲያን ውጪ ወደ ውስጥ ሚሊሻና የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ተኩስ ከፈቱብን። ያኔ ወንድሜ እግሩን በጥይት ተመትቶ ወደቀ” ይላል።

እርሱ እንደሚለው የወንድሙ የሁለቱ እግሮቹ አጥንቶች ተሰባብረዋል። በመሳሪያ ከተመታው ውጪ እግሩ በዱላ ተደብድቦ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ለቢቢሲ ገልጿል።

“አሁን ሐዋሳ ነኝ። እዚህ ራሱ 11 ሰዎች እየታከሙ ነው። ወንድሜ እንደነገረኝ ግቢ ውስጥ አንድም የታጠቀ ሰው አልነበረም። በአካባቢው ካለ ፎቅ እንደተተኮሰባቸው ነው የነገረኝ” ብሏል።

የመልካ ኦዳ ሆስፒታል ኃላፊ የሆኑት አቶ ሱልጣን ሁሴን 10 የሚሆኑ ሰዎች ተጎድተው ወደ ሆስፒታሉ እንደሄዱና ከዚያ ውጪ ያሉት ምናልባት ወደ ሌላ ሆስፒታል ተወስደው ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

የሻሸመኔ ከተማ የአስተዳደርና ፀጥታ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አምቦ ጁላ በበኩላቸው በምዕመናኑ ላይ የፀጥታ ኃይሉ ተኩስ እንዳልከፈተ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“እነሱ ላይ አንድም ሰው ተኩስ አልከፈተም። ሁለት፣ ሦስትም ሰው ቢሞት እነሱ በከፈቱት ተኩስ ነው። ከዛ ውጭ የኛ የፀጥታ አካል አንድ ችግር እነሱ ላይ አላደረሰም። ከፀጥታ ኃይል መካከል ተጎድተው ሆስፒታል የገቡ ብዙ አሉ” ሲሉም ተኩስ የከፈቱትን እነማን እደሆኑ እናጣራለን ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከሁለት ሳምንት በላይ ባስቆጠረው ከዚህ ቀውስ ጋር በተያያዘ የቤተክርስቲያን አባቶች እና ምእመናኖቿ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እየተንገላቱ መሆናቸውን የገለጸው የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር ጠይቋል።

መንግሥት በበኩሉ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የተፈጠረው ችግር በራሷ በቤተክርስቲያኗ መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው በማለት እጁ እንደሌለበት በማስተባበል መግለጫ ቢሰጥም፣ የፀጥታ ኃይሎች የተወገዙትን አባቶች በማጀብ የቤተክርስቲያኗን ንብረቶች እንዲቆጣጠሩ እየተደረገ ነው ስትል በተደጋጋሚ ገልጻለች።

ጥር 14/2015 ዓ.ም. ወሊሶ አቅራቢያ የተከናወነውን የ26 ኤጲስ ቆጶሳት ሹመትን ተከትሎ ሦስት ጳጳሳት እና ሹመት የተቀበሉት በቅዱስ ሲኖዶሱ ተወግዘው ከቤተከርስቲያኗ እንዲለዩ መወሰኑ ይታወሳል።

በቋንቋ የመጠቀም ጉዳይን በቀዳሚነት አንስተው ወደ ውዝግብ እና ውግዘት የገቡት አባቶችም የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ በመቃወም የጀመሩትን ተግባራዊ በማድረግ እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል።

መንግሥት የሕጋዊቷን ቤተክርስቲያን መብት አላስከበረም በሚል ወቀሳ ያቀረበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም አስከ ረቡዕ የካቲት 01/2015 ዓ.ም. ድረስ መንግሥት ኃላፊነቱን የሚወጣ ካልሆነ ለእሁድ የካቲት 05/ 2015 ዓ.ም ምእመኑ አደባባይ ወጥቶ ድምጹን እንዲያሰማ ጥሪ ማቅረቧ ይታወቃል።