የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥትን የሰልፍ ክልከላ እንደማትቀበል አስታወቀች

የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በከፊል

የፎቶው ባለመብት, eotc

የምስሉ መግለጫ, የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በከፊል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የሚጠበቅበትን አስካላከናወነ ድረስ የፀጥታ እና ደኅነት የጋራ ግብረ ኃይል ያስተላለፈውን የሰልፍ ክልከላ እንደማትቀበለው አስታወቀች።

ቤተ ክርስቲያኗ ይህን ያለችው ዛሬ ሐሙስ የካቲት 02/2015 ዓ.ም. ባለፉት ቀናት ስላጋጠሙ ጉዳዮች እና በመንግሥት በኩል የተላለፈውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ በቅዱስ ሲኖዶሱ በኩል በተሰጠው መግለጫ ነው።

ሲኖዶሱ የሰልፍ ክልከላ መግለጫው መንግሥት አሁንም “ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማውደም እና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት የታወጀ አዋጅ መሆኑን በጽኑ እንድናምን አድርጎናል” ብሏል።

የፀጥታ እና ደኅነት የጋራ ግብረ ኃይል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰሞኑ ከተከሰተው ችግር ጋር ተያያይዞ ለየካቲት 05/2015 ዓ.ም. የተጠራው ሰልፍ ፍቃድ እንደሌለው ረቡዕ ዕለት ማስታወቁ ይታወሳል።

ሲኖዶሱ ሕገ-ወጥ ካለው የጵጵስና ሹመት እና አዲስ ሲኖዶስ መመስረት ጋር ተያይዞ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ በመግባት እንዲሁም ለሕገ-ወጥ ቡድን ድጋፍ በመስጠት በቤተ ክርስቲያን ላይ ወረራዎች እየፈጸመ ይገኛል፣ እንዲሁም በሃይማኖት አባቶች በምዕመናን ላይ እስሮች፣ ማዋከቦች እና ግድያዎች ፈጽሟል በሚል ሰልፍ ጠርታለች።

ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች በሚል የተቋቋመውም አዲሱ ሲኖዶስ በተመሳሳይ ቀን ሰልፍ ጠርቷል።

መንግሥታዊው ግብረ ኃይል ግን “በተመሳሳይ ቀን እና ቦታ ሕገ-ወጥ የሰልፍ ጥሪ በማድረግ የዜጎች ሕይወት የሚቀጠፍበት አጋጣሚ እንዲፈጠር ቅስቀሳዎች እየተደረጉ እና ሌሎችም ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት እየተፈፀሙ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል” ካለ በኋላ ሰልፎቹ ፍቃድ እንዳልተሰጣቸው ገልጾ ሰልፍ የሚያስተባብሩ እና የሚሳተፉ ለሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂ ይሆናሉ ሲል አስጠንቅቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሲኖዶሱ በበኩሉ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገሪቱ ሕግ የተረጋጋጠ መሠረታዊ የሆነ ሰብዓዊ መብት ነው ያለ ሲሆን፣ ቤተ ክርስቲያኗ በመንግሥት የተሰጠውን መግለጫ ሕጋዊ መብትን የሚገፍ ሕገ-ወጥ በመሆኑ አልቀበለውም ብላለች።

“ጉዳዩ ግልፅ የሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሆኖ እያለና መፍትሄውም በመንግሥት እጅ የሚገኝ ብቻ መሆኑ እየታወቀ፣ የፖለቲካ ቅርፅ ለማስያዝ መሞከር ችግሩን ያባብሰው እንደሆን እንጂ አይፈታውም” ብሏል ሲኖዶሱ።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በቤተክርስቲያኗ እና በአባላቷ ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ያመለከተው መግለጫው መሣሪያ የታጠቁ አካላት እና የመንግሥት የፀጥታ አባላት በኃይል እና በጉልበት አብያተ ቤተክርስቲያናት ተወረዋል ብሏል።

ሊቃነ ጳጳሳት እንዳይንቀሳቀሱ፣ ከሚያገለግሉበት አካባቢ መባረራቸውንና እንዳይገቡ መከልከላቸውን፣ ካህናት እና ምእመናን መታሰራቸውን፣ በፀጥታ ኃይል መደብደባቸውን በዚህም የተነሳ የሞት፣ የከባድ እና ቀላል አካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

መግለጫው በተለይ በሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተወሰደ ባለው “ሰቃቂ እርምጃ እስከ አሁን ቁጥራቸው ከ30 በላይ የሚሆኑ ካህናትን እና አገልጋዮችን ጨምሮ ምዕመናን” መሞታቸውን አስታውቋል።

ሲኖዶሱ በዛሬው መግለጫው መንግሥት ያለው አማራጭ የካቲት 05/2015 ዓ.ም. ለተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ሰልፉ እንዲደረግ መፍቀድ፣ አሊያም ለቤተ ክርስቲያኗ ጥያቄ መልስ መስጠት አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን እናሳስባለን ብሏል።

“ቤተ ክርስቲያን ከምትፈርስ ሞት፣ ስደት እና መከራን በደስታ እንቀበላለን” ያለው ሲኖዶሱ፣ መንግሥት በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ሕገ-ወጥ ካላቸው ግለሰቦች ጋር መተባበሩን እንዲያቆም፣ ሕግ እና ሥርዓትን እንዲያስከብር ጠይቋል።

በተጨማሪም በኃይል የተያዙ መንበረ ጵጵስና እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለቤተክርስቲያኒቱ እንዲያስረክብ፣ የታሰሩ ካህናት እና ምዕመናን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ተፈጽሟል ላለው በደል በአደባባይ ይቅርታ እንዲጠይቅ እንዲሁም ለደረሰውንም ጉዳት እንዲክስ በጥብቅ ጠይቋል።

ቤተ ክርስቲያኗ ይህ ጥያቄዋ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ መብቷን ለማስከበር እንቅስቃሴዋን በማስፋት የካቲት 05/2015 ዓ.ም. የተጠራውን ሰልፍ ያለማንም ከልካይነት “በራሴ አደባባይ አከናውናለሁ” ብላለች።

ሲኖዶሱ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጪ ያሉ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደር “የቤተ ክርስቲያኗን ጥሪ በመከተል በአግባቡ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር” ለወሰዱት እርምጃ ምስጋና አቅርባለች።