ዛሬ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ዝግ እንደሚሆኑ እንደተነገራቸው ወላጆች ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ አርብ የካቲት 03/2015 ዓ.ም. ትምህርት ቤቶች ዝግ እንደሚሆኑ ወላጆች ከልጆቻቸው ትምህርት ቤቶች መልዕክት እንደደረሳቸው ለቢቢሲ ገለጹ።
ቢቢሲ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸውን ከሚያስተምሩ ወላጆች ለመረዳት እንደቻለው፣ ዛሬ አርብ ትምህርት እንደሌለ የሚገልጽ መልዕክት ደርሷቸዋል።
በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ የመልዕክት መለዋወጫ መድረኮች አማካይነት ለወላጆች ከተላኩት እና ቢቢሲ የተመለከታቸው መልዕክቶች፣ “ከከተማው ትምህርት ቢሮ በታዘዘው መሠረት አርብ የካቲት 03/2015 ዓ.ም. ትምህርት እንደማይኖር” የሚገልጽ ነው።
ሌሎች ወላጆች ደግሞ በልጆቻቸው በኩል አርብ ትምህርት ዝግ መሆኑን የሚለግጽ የቃል መልዕክት እንደደረሳቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ነገር ግን ሁሉም ወላጆች ትምህርት ቤቶች ለአንድ ቀን ዝግ እንዲሆኑ የተደረገበትን ምክንያት በተመለከተ የተገለጸላቸው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
እንደሚታወቀው የመጀመሪያ የመንፈቅ ዓመት ትምህር ጊዜው ተጠናቆ ተማሪዎች እረፍት ላይ ቆይተው የሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ጊዜ የተጀመረው ከቀናት በፊት ነው።
ቢቢሲ ትምህርት ቤቶች ዝግ እንዲሆኑ የተደረገበትን ምክንያት ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ለማጣራት ያደረገው ጥረት ባይሳካለትም፣ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ ርዕሰ መምህር ግን ከመምህራን ጋር የሚደረግ ስብሰባ ይኖራል መባሉን ገልጸዋል።
ነገር ግን ስብሰባው ስለመኖሩ ቀደም ሲል የሚታወቅ ነገር አለመኖሩን እና ስለስብሰባው አጀንዳም እንደማይታወቅ ተናግረዋል።
አንድ መምህርም በበኩላቸው ስብሰባ ስለመኖሩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ፣ ከዚህ በፊት ግን ስብሰባዎች ሲኖሩ ከቀናት በፊት መምህራን እንደሚያውቁ እንደሚደረግ ልምዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንዳንድ ወላጆች ግን ትምህርት አለመኖሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተከሰተው ችግር ከመባባሱ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረው፣ ተማሪዎች ቤት እንዲቆዩ መደረጉን መልካም ነው ብለዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተከሰተው ቀውስ እየተባባሰ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች እና ምዕመናን በመንግሥት ላይ ተቃውሞ እያሰሙ መሆናቸው ይታወቃል።












