በርካታ የኦርቶዶክስ ምዕመናን መታሰራቸውን እና አብዛኛዎቹ ወደ አዋሽ ሰባት መወሰዳቸው ተገለጸ

ባለፈው ሳምንት የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን በአብያተ ክርስቲያናት በመገኘት የጸሎት ሥነ ሥርዓቶች ተካሂደዋል

የፎቶው ባለመብት, EOTC

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ሳምንት የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን በአብያተ ክርስቲያናት በመገኘት የጸሎት ሥነ ሥርዓቶች ተካሂደዋል

ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ክስተት ጋር በተያያዘ የእምነቱ ተከታዮች መታሰራቸውን እና አብዛኞቹም ወደ አዋሽ ሰባት የጦር ካምፕ መወሰዳቸውን የቤተ ክርስቲያኗ ጠበቆች ለቢቢሲ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕግ ባለሙያዎች ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አያሌው ቢታኔ እስካሁን ባላቸው መረጃ ከ200 በላይ ምዕመናን መታሰራቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም በተጨባጭ ደረጃ ቁጥሩ በትክክል እንደማይታወቅ እና በሚቀጥሉት ቀናትም ለዚህ ተግባር የተዋቀረው የመረጃ አካልም ዝርዝሩን ያቀርባል ብለዋል።

እስሩ በአብዛኛው የተከናወነው በአዲስ አበባ እና በአጎራባች አካባቢዎች ሲሆን ወደ አዋሽ ሰባት የተወሰዱ ምዕመናን ቁጥርም በርካታ ስለመሆናቸው መረጃ አለን ብለዋል።

አዋሽ ሰባት ውስጥ ምን ያህል ግለሰቦች እንደታሰሩ በትክክል ባያውቁም ከ100 አስከ 200 የሚሆኑ የዕምነቱ ተከታዮች ወደ ስፍራው መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ውስጥ ከታሰሩት መካከል የተወሰኑት ሰኞ የካቲት 06/2015 ዓ.ም. ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ ‘በሽብር ተግባር እና ሕገ መንግሥቱን ለመናድ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ’ ተጠርጥረው መያዛቸው ተገልጿል።

ከእነዚህም ውስጥ በእነመምህር ምህረተ አብ አሰፋ እና ኪሩቤል አሰፋ መዝገብ እንዲሁም በእነ ፌቨን ዘሪሁን እና ብሩክታዊት ነብዩ መዝገብ አስራ ሁለት ሰዎች ሰኞ ከዋለው ችሎት መቅረባቸውን የሕግ ባለሙያው አስረድተዋል።

ከመካከላቸውም ሰባት ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢለቀቁም ሌሎቹ የስምንት ቀን ቀጠሮ ተሰጥቶ ጉዳያቸው የካቲት 14/2015 ዓ.ም. እንደሚታይ ተገልጿል።

በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩት መካከል የቤተክርስያኗ የወጣቶች እና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ሰብሳቢ ፌቨን ዘሪሁን፣ የኅብረቱ ዋና ጸሐፊ ብሩክታዊት ነብዩ እንዲሁም መሳይ ተፈራ፣ ተካልኝ ኢቲቻ፣ ወንደሰን ንጉሴ፣ ረ/ሳጅን ሠራዊት ፀጋ እና ፋሲል አግደው እንደሚገኙበት ማኅበረ ቅዱሳን ገልጿል።

በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያኗ በሰባኪ ወንጌልነት የሚያገለግለው መምህር ምህረተአብ አሰፋን ጨምሮ አማኑኤል አያሌው፣ ኪሩቤል አሰፋ፣ ሰይፉ አለማየሁ እና እጅጋየሁ ዳርጌ እንደተካተቱበት ተገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ግለሰቦቹ የራሳቸውን ዓላማና የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት፣ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በመናድ መጠርጠራቸውም ሰፍሯል።

ግለሰቦቹ ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ እንደታሰሩ የተናገሩት አቶ አያሌው፣ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ካሉት እንደ ለገጣፎ፣ ሰበታ፣ አሸዋ ሜዳ በነበሩ እስሮች ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄዱ የነበሩ የታሰሩ ካህናት መኖራቸውን አመልክተዋል።

ባለፉት ሳምንታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሕገወጥ ነው ካለችው የጵጵስና ሹመት እና የሲኖዶስ ምሥረታ ጋር በተያያዘ እስሮቹ መፈጸማቸውን የተናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ በተለይም የሃይማኖት አባቶች ከመንግሥት ጋር ከተወያዩ በኋላ እስሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አመራሮች ባለፈው ሳምንት አርብ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ስለተፈጠረው ክስተት መወያየታቸውን እና የቤተ ክርስቲያኗንም ጥያቄ ሙሉ በሙሉ መንግሥት መቀበሉን ማሳወቋ ይታወሳል።

ሆኖም ጠበቃው እንደሚሉት ቤተ ክርስቲያኗ በራሷ ሃይማኖታዊ ቀኖና እና አስተዳደራዊ ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ጉዳዩን እልባት እንድትሰጥ መንግሥት ከተስማማ በኋላ እስሮች እና ውክቢያዎች መፋፋማቸውን መረጃዎች ያሳያል ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ በሽማግሌዎች እንዲሁም በሃይማኖት አባቶች በሚመራ ኮሚቴ ጥያቄውን ለመንግሥት ያቀረበች ሲሆን፣ በልዩ ሁኔታም ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከፌደራል ፖሊስ እንዲሁም ለዚህ ተግባር ከተቋቋመው የአዲስ አባበ ኮማንድ ፖስት ጋር ቤተ ክርስቲያኗ ውይይት እያደረገች እንደሆነና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠትም ጥረት እየተደረገም እንደሆነ ተገልጿል።

እስሮቹን በተመለከተ ቢቢሲ የአዲስ አበባ ፖሊስን ለማናገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ስለ እስሮቹ የጠየቀ ሲሆን፣ ክትትል እያደረጉ እንደሆነ እና ምርመራም ሲጠናቀቅ እንደሚያሳዉቁ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ ግድያዎች፣ እስሮች፣ መዋከቦች እና እንግልቶች መፈጸማቸውን ኢሰመኮ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመናል ያሉ ጳጳሳት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን መያዛቸውን የተቃወሙ ምዕመናን ላይ የመንግሥት የፀጥታ አባላት እና ተባባሪዎቻቸው ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል መጠቀማቸው ተገልጿል።

በዚህም በጥይት እና በድብደባ ስምንት ሰዎች ሻሸመኔ ውስጥ መግደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያስታወቀ ሲሆን፣ ቤተ ክርስቲያኗ በበኩሏ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ያለ ነው ብላለች።

በተለያዩ ቦታዎችም አዲሱን “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል ያሉትን ጳጳሳት በተቃወሙ ምዕመናን እና የሃይማኖት መሪዎች ላይ ድብደባ፣ ማዋከብ፣ ከቤተ ክርስቲያናት ማባረር፣ የመንቀሳቀስ መብትን በኃይል መገደብ እና ከሕግ ውጪ እስራት ተፈጽሟል ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያኗ ለጥበቃ የወሰደችውን የጦር መሳሪያ እንድታስረክብም መጠየቋን አቶ አያሌው ይናገራሉ።

የተደራጁ ኃይሎች ከ20 በላይ በሚበልጡ አብያተ ክርስቲያናት በመዘዋወር የጥበቃ የጦር መሳሪያዎችን እንዲያስረክቡ የተጠየቁ ሲሆን፣ አምስት ወይም ስድስት ከሚሆኑ የአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት የጥበቃ የጦር መሳሪያዎች ተወስዷል ብለዋል።

ይህም “ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ” በሚል እንደተነገራቸው የገለጹት የሕግ ባለሙያው፣ ከማን ነው የሚለው ግን ግልጽ አይደለም ብለዋል።

ከፓርትርያርኩም ሆነ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅ እና ውጪ 26 ጳጳሳት መሾማቸውን ተከትሎ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት እና ቀኖና የሚጥስ ነው በማለት የጵጵስና ማዕረጉን የሰጡትን እንዲሁም የተሾሙትን የማውገዝና ሹመታቸውም ተሽሮ እንዲለዩ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።

የቤተ ክርስቲያኗ አካሄድ አካታች እንዳልነበረ እና ምዕመናን በቋንቋቸው መገልገል እንዳልቻሉ በመግለጽ አዲስ ሲኖዶስ መቋቋሙን የገለጹት ጳጳሳት ውሳኔውን በማውገዝ በእርምጃቸው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።