በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተጠራው ሰልፍ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማቲያስ

የፎቶው ባለመብት, EOTC

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መሪዎች ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት የቤተክርስቲያኗ አቋም ተቀባይነት በማግኘቱ ለእሁድ ታቅዶ የነበረው ሰልፍ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተገለጸ።

በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ ውጥረት በነገሰበት ጊዜ በቤተክርስቲያኗ እና በመንግሥት መሪዎች መካከል አርብ ከሰዓት በኋላ በተደረገው ውይይት፣ መንግሥት ቤተክርስቲያኗ ያቀረበችውን ቅድመ ሁኔታ መቀበሉ ተገልጿል።

ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 04/2015 ዓ.ም. የውይይቱን ውጤት በተመለከተ የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በውይይቱ በዋነኛነት ከቤተ ክርስቲያኗ ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ሕግ ውጪ ምንም አይነት ድርድር እንዳልተደረገ ተገልጿል።

በቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት በአማርኛ እና በኦሮምኛ በቀረበው መግለጫ ላይ “መንግሥት የቤተ ክርስቲያንን አቋም በመቀበል ወደፊትም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እና ሉዓላዊነትን በጠበቀ መንገድ እንደሚሠራ አረጋግጧል” ተብሏል።

በውይይቱ ላይ በፓትርያርክ አቡነ ማቲዮስ የተመሩ አሥራ ሁለት ጳጳሳት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች መገኘታቸው ተገልጿል።

በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል ከሦስት ሳምንት በፊት ጀምሮ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ በቤተክርስቲያኗ አባላት ላይ የሕይወት እና የአካል ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ጉዳይ በውይይቱ ላይ ተነስቶ መንግሥት የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለይቶ በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በተጨማሪም አሁን ላይ እስር፣ እንግልት እየተፈጸመባቸው ያሉት አባቶች እና የቤተክርስቲያኗ አባላት ላይ የሚደርሰው ችግር በአስቸኳይ እንዲቆምና የታሠሩትም እንዲፈቱ እና አገልግልታቸውን በሰላም እና በነጻነት መስጠት እንዲችሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት መንግሥት የቤተ ክርስቲያኒቱን አቋም ሙሉ በሙሉ የተቀበለ በመሆኑ ይህንን ለማስፈጸም ጊዜ የሚያስፈልግ በመሆኑ እሁድ የካቲት 05/2015 ዓ.ም. ሊካሄድ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉ ተገልጿል።

በቤተክርስቲያን በኩልም በሕግ የተያዙት ጉዳዮች የሕግ ሂደታቸውን ተከትለው የሚቀጥሉ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ መንግሥትም የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ተቀብሎ ለውይይት ፈቃደኛ መሆኑን የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በማክበር በውሳኔው መሠረት የሚፈጸም መሆኑን በማረጋገጡ ምስጋና አቅርበዋል።

ጥር 14/2015 ዓ.ም. ሦስት ጳጳሳት ቤተክርስቲያኗ ሁሉን አሳታፊ አይደለችም እንዲሁም በቀሪው የአገሪቱ ክፍል ያሉ ምእመናንን በቋንቋቸው እያገለገለች አይደለም በሚል ለ26 ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ከሰጡ በኋላ ነበር ቀውሱ የተጀመረው።

የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ደግሞ ሹመቱ ከቤተክርስቲያኗ ቀኖና፣ ዶግማ እና አስተዳደራዊ ሂደት የተቃረነ በመሆኑ ሿሚዎቹ እና ተሿሚዎቹ በይቅርታ እስኪመለሱ ድረስ ተወግዘው እንዲለዩ ወስኗል።

ይህንንም ተከትሎ በቤተክርስቲያኗ አገልጋዮች እና ምእመናን ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በካቢኔ ስብሰባ ላይ በሰጡት አስተያየትም በመንግሥት እና በቤተክርስቲያኗ መካከል መካረር ተፈጥሮ ቆይቷል።

መንግሥት ቢያስተባብልም ቤተክርስቲያኗ በተደጋጋሚ በሰጠችው መግለጫ መንግሥት ወገንተኛ ሆኗል ሕግንም እያስከበረ አይደለም በማለት የቤተክርስቲያኗ ተከታዮች እሁድ የካቲት 05/2015 ዓ.ም. አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ ቀርቦ ነበር።

ነገር ግን መንግሥት የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ በወሰደው እርምጃ ከቤተክርስቲያኗ መሪዎች ጋር በመወያየት ከስምምነት በመድረሱ ሰልፉ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ እና የቤተክርስቲያኗ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ መወሰኑን ቤተክርስቲያኗ በሰጠችው መግለጫ ላይ አሳውቃለች።

ሰላማዊ ሰልፍ ይካሄድበታል በተባለው እለት ምዕመናን ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው በመሄድ እንዲጸልዩ እና ትምህርት እንዲማሩ ቤተክርስቲያኗ የገለጸች ሲሆን ምዕመናን ቤተ ክርስቲያኒቱን መጠበቃቸውን እንዲቀጥሉም አሳስባለች።

እስካሁን ስለውይይቱም ሆነ ተደርሷል ስለተባለው ስምምነት ከመንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም።