ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አውግዛ የለየቻቸው አባቶች ወደ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይገቡ ፍርድ ቤት አገደ

ቤተክርስቲያን

የፎቶው ባለመብት, sm

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕገወጥ ሹመት ሰጥተዋል ባለቻቸው ጳጳሳት እና ተሿሚዎች ላይ ለፍርድ ቤት ያቀረበችው የእግድ አቤቱታ ዛሬ የካቲት 03/2015 ዓ.ም. ተቀባይነት ማግኘቱን ጠበቆቿ ለቢቢሲ ገለጹ።

የቤተክርስቲያኗን ቀኖና እና ሥርዓትን በጣሰ መልኩ የጵጵስና ሹመት እና ሲኖዶስ በሟቋቋማቸው ያወገዘቻቸው አባቶች ወደ የትኛውም የቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር እንዳይገቡ ጊዜያዊ እግድ መጣሉን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አንዷለም በዕውቀቱ ገዳ ተናግረዋል።

እግዱ የተጣለው ሹመት በሰጡት ጳጳሳት፣ በአቡነ ሳዊሮስ፣ በአቡነ ዜና ማርቆስ፣ በአቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና በተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት ላይ ሲሆን፣ በአጠቃላይም 28 እንደሆኑም ጠበቃ አንዷለም ተናግረዋል።

“በሁሉም የቤተክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ መግባት አይችሉም። በአሁኑ ወቅት በየአካቢው ባሉ አብያተ ክርስቲያናት እንሂድ እያሉ አቀባበል እየተደረገላቸው ሲሆን፣ እሱ ለጊዜው ታግዷል። በዚህ እግድ ከቤተክርስቲያን ተገለዋል” ብለዋል።

እግዱን የተላለፈ ማንኛውም አካል የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚኖርበትና እንዲሁም በሃገሪቱ የሚገኙ የህግ አስፈጻሚ አካላት እግዱን እንዲያስፈጽሙ ትዕዛዝ እንደተሰጠም ተገልጿል።

ቤተ ክርስቲያኗ የእግድ አቤቱታውን ባለፈው ዓርብ ጥር 26/2015 ዓ.ም ያቀረበች ሲሆን፣ ከሁለት ቀጠሮዎች በኋላ ዛሬ አርብ ጊዜያዊ ዕግድ ተወስኗል።

በአሁኑ ቀጠሮ እና በባለፈው ቀጠሮ መካከል የሁለት ሰው ህይወት ተቀጥፏል ያሉት አቶ አንዷለም፣ ቀጠሮ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር “የማይተካ ጉዳት በዜጎች ላይ በምዕመናን ላይ ይደርሳል በሚል ጊዜያዊ እግድ ነው የተሰጠው።”

በዛሬው ችሎት የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች በሚል ሲኖዶስ ያቋቋሙት የአቡነ ሳዊሮስ፣ የአቡነ ዜና ማርቆስ እና የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ጠበቆች የተገኙ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ 25 የተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት የጥብቅና ስላላለቀላቸው አለመወከላቸውንም ነው የተናገሩት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከተጠሪዎቹ ሦስቱ ጠበቆች አንዱ ቃለ አቀባያቸው ኃይለሚካኤልም ተገኝተዋል ብለዋል።

የፍርድ ቤቱን እግድ ውሳኔ ተከትሎ አዲስ የተቋቋመውን ሲኖዶስ በፍርድ ቤት የወከሉትን ጠበቃ በማግኘት ቢቢሲ አስተያየታቸውን ለማካተት ቢሞክርም አልተሳካም።

በቀጣይነትም የቤተ ክርስቲያኗን ንብረትን መጠቀምን ጨምሮ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ ክርክሩ እንደሚቀጥልም ነው አቶ አንዷለም ያስረዱት።

በቀጣይም ፍርድ ቤቱ ለየካቲት 08/2015 ዓ.ም የተቀጠረ ሲሆን፣ ከሰሞኑ በደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ላይ ክስ እንደሚመሰረት እና በእርቅም እንደማያልቅ አስረድተዋል።

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ ግድያዎች፣ እስሮች፣ እንግልቶች እና ማዋከቦች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ አስታውቋል።

ቤተክርስቲያኗ ሕገወጥ ነው ባለችው ሹመት አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመናል ያሉ ጳጳሳት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አገረ ስብከቶችን መያዛቸውን የተቃወሙ ምዕመናን ላይ ላይ በመንግሥት የፀጥታ አባላት ተመጣጣኝ ባልሆነ ኃይል በጥይት እና በድብደባ ግድያዎች ተፈጽሟል ብሏል - ኢሰመኮ።

አዲስ ቤተ ክህነት ማቋቋማቸውን ያሳወቁ ጳጳሳት በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚገኙ አገረ ስብከቶችን መያዛቸውን ያስታወቀው ኢሰመኮ፣ በአንዳንድ ቦታዎች በባለሥልጣናት ጭምር ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጿል።

ከፓርትርያርኩም ሆነ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጭ 26 ጳጳሳት መሾማቸውን ተከትሎ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት እና ቀኖና የሚጥስ ነው በማለት የጵጵስና ማዕረጉን የሰጡትን እንዲሁም የተሾሙትን የማውገዝና ሹመታቸውም ተሽሮ እንዲለዩ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።

የቤተ ክርስቲያኗ አካሄድ አካታች እንዳልነበረ እና ምዕመናን በቋንቋቸው መገልገል እንዳልቻሉ በመግለጽ አዲስ ሲኖዶስ መቋቋሙን የገለጹት ጳጳሳት ውሳኔውን በማውገዝ በእርምጃቸው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተከስቶ ሦስት ሳምንት ሊሞላው የተቃረበው ይህ ክስተት በአባቶች፣ በምዕመናን እና በመንግሥት መካከል ከባድ ፍጥጫን አስከትሎ ቆይቷል።