ፖላንድ የአየር ክልሌን ጥሰዋል ያለቻቸውን አራት የሩሲያ ድሮኖችን መትታ መጣሏን አስታወቀች

ሩሲያ በኪየቭ ላይ የድሮን ጥቃት ስትፈፅም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሩሲያ ትናንት ምሽት በኪየቭ ላይ የድሮን ጥቃት ፈፅማለች

አውሮፓዊቷ አገር ፖላንድ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት በምትፈፅምበት ጊዜ የአየር ክልሏን ከጣሱት 19 ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) መካከል አራቱን መትታ መጣሏን ገለጸች።

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ሩሲያ በምስራቃዊ የዩክሬን ጥቃት በምትፈጽመበት ወቅት 19 የሰው አልባ አውሮፕኖቿ የአየር ክልሏን ጥሰው መግባታቸውን ገልጸዋል።

አራት ድሮኖች በፖላንድ እና ኔቶ የአየር መቃወሚያዎች መመታቸውን ተናግረዋል።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ( ኔቶ) አባል የሆነችው ፖላንድ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት የዩክሬን ጦርነት ከጀመረ ወዲህ በአየር ክልሏ ውስጥ የሩሲያ ድሮኖችን መትታ መጣሏን ስትገልጽ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ስለተፈጠረው ሁኔታ እና አገራቸው የአየር ክልሏን ጥሰው በገቡ አካላት ላይ ስለወሰደችው እርምጃ ለኔቶ ዋና ኃላፊ ማርክ ሩት ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።"አሁንም እየተነጋገርን ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም ኦፕሬሽኑ መቀጠሉንና ከኔቶ ኃላፊ ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን እንዲሁም ከካቢኔያቸው ጋር ልዩ ስብሳባ እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል።

ፕሬዚደንት ካሮል ናውሮኪ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚሳተፉበት ብሔራዊ የጸጥታ ቢሮ ስብሰባ ላይ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

" የአገራችን ደኅንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ሲሆን ጥብቅ ትብብር ይጠይቃልም" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአገሪቷ ጦር በበኩሉ ክስተቱ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የፖላንድን የአየር ክልል የጣሰ መሆኑን በመጥቀስ "ድርጊቱ ለዜጎቻችን ደኅንነት ስጋት የሆነ ነው" ብሏል።

ክስተቱን ተከትሎ የአገሪቷ መዲና ዋርሶው የምትገኝበትን ማዞዌኬን ጨምሮ ከዩክሬን ጋር የሚዋሰኑ ሦስት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በቤታቸውና መጠለያ ውስጥ እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል።

ከዚህም ባሻገር የአገሪቷ ዋና አየር ማረፊያ የሆነውን ቾፒን አየር ማረፊያ፣ በአገሪቷ የአየር ክልል በመዘጋቱ ምክንያት የአራት አውሮፕላን ማረፊያዎች አገልግሎት ለጊዜው እንዲቆም መደረጉን አሳውቆ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ዋናው አየር ማረፊያ መከፈቱን ገልጿል።

የአገሪቷ ጦር ምሽቱን የአገሪቷን የአየር ክልል ጥሶ የገባውን ድሮን መትቶ ከጣለ በኋላ ወታደራዊ ኦፕሬሽኑን ማጠናቀቁን ገልጿል።

ጦሩ በኤክስ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ " ከፖላንድ የአየር ክልል ጥሰት ጋር በተገናኘ ሲካሄድ የነበረው የፖላንድ እና አጋር አቪየሽኖች ኦፕሬሽን ተጠናቋል፤ ተመትቶ የተጣለውን ድሮን ፍለጋ እና ያደረሰው ጉዳት ካላ የማጣራቱ ሥራ እንደቀጠለ ነው" ብሏል።

ጦሩ ጨምሮም ዜጎች ለደኅንነታቸው ሲባል ስብርባሪ ወይም ምንነቱን የማያውቁት አካል ካዩ እንዳይቀርቡ፣ እንዳይነኩ እና እንዳያንቀሳቅሱ አሳስቧል።

"እንዲህ ዓይነት ነገሮች ጉዳት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ክትትል ሊደረግባቸውና ሊወገዱ የሚገባው በትክክለኛው ባለሙያዎች ነው" ሲልም አፅንኦት ሰጥቷል።

ፖላንድ አሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት ራሳቸውን በጋራ ለመከላከል የተቋቋመው ኔቶ አባል አገር ናት። ኔቶ በፖላንድ ያለው ሥራው የሚመራው በአሜሪካ ጦር ነው።

የፖላንድ የአየር ክልል የተጣሰው ሩሲያ ምሽቱን በዩክሬን ላይ የድሮን ጥቃት በፈፀመችበት ወቅት ነው።