ዘለንስኪ ሩሲያ በኪዬቭ ዋነኛ የመንግሥት መስሪያ ቤት ህንጻ ላይ የፈጸመችውን ጥቃት አወገዙ

የፎቶው ባለመብት, Telegram/svyrydenkoy
ሩሲያ በዩክሬን መዲና የሚገኘው ዋነኛ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚገኙበት ህንጻ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት መፈጸሟን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አታወቁ።
በጥቃቱ የህንጻው የላይኛው ፎቆች እና ጣሪያው መጎዳቱን እንዲሁም እሳት መነሳቱን ዩሊያ ስቭርይዴንኮ ተናግረዋል።
በዚህ ጥቃት የተጎዳው የመንግሥት ህንጻ የዩክሬን ዋና ሚኒስትሮች ጽህፈት ቤት ስለሚገኙበት የሚኒስትሮች ካቢኔ በመባል ይታወቃል።
በጨማሪም ስቭቶሽይንስኪ በተሰኘች ግዛት በሚገኝ ባለ ዘጠኝ ፎቅ የመኖሩያ ህንጻ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ህጻንን ጨምሮ ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸውን የግዛቲቱ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
ሩሲያ በነዚህ ጥቃቶች ከ800 በላይ ሚሳኤሎች እና ድሮኖች መጠቀሟን የዩክሬን አየር ኃይል አስታውቋል።
እንደ አየር ኃይሉ ገለጻ ከሆነ 9 ሚሳኤሎች እና 56 ሰው አልባ አውሮፕላኖች 37 ስፍራዎችን መምታታቸውን ነው።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው በዚህ ጥቃት የዛፖሪዚህዚያ፣ ክሪቪ ሪ፣ ኦዴሳ እንዲሁም ሱሚ እና ቼርኒቭ ክልሎች መመታቸውን አክለዋል።
"ዲፕሎማሲ መጀመር ባለበት ወቅት እንዲህ አይነት ግድያዎች ሆን ተብሎ የሚፈጸም ወንጀል እንዲሁም ጦርነቱን ለማራዘም የሚደረግ ሙከራ ነው" ሲሉ በማህበራዊ ገጻቸው ያሰፈሩት ዘለንስኪ ፤ጥቃቱን ለማስቆም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ጥቃቶቹ የተፈጸሙት በዩክሬን ወታደራዊ ይዞታዎች እና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ ሲሆን ይህም በጦር መሳሪያዎችና ማከማቻዎቻቸው ላይ ጉዳት ያደረሰ ነው ብሏል።
የኪዬቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊትሽኮ በበኩላቸው ድሮኑ ከተጠለፈ በኋላ የሚኒስትሮች ካቢኔ ህንጻውን በስህተት መትቶ ሊሆን እንደሚችል አስተያየት ቢሰጡም ዝርዝሩን አልገለጹም።
ለሶስት ዓመት በዘለቀው ጦርነት ሩሲያ የትኛውንም የዩክሬን የመንግሥት ህንጻ ላይ ጥቃት ፈጽማ አታውቅም። በተጨማሪም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በጥብቅ ከመጠበቃቸው አንጻር የአሁኑ ጥቃት በርካቶችን መረበሹ የማይቀር ነው።
በተጨማሪም ጥቃቱ ተምሳሌታዊ ነው ተብሏል። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለሰላም ዝግጁ ስለመሆናቸው የተናገሩት ሁሉ የይስሙላ ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነም ተነግሯል።
ፑቲን ጥቃቱን ለማቆም ሳይሆን አጠናክረው እየቀጠሉ ነው።
ቢቢሲ ወደዚህ ህንጻ እንዲጠጋ አልተፈቀደለትም።
ፓርላማና የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤትን ጨምሮ ሁሉም መንግሥታዊ ቢሮዎች በዚህ ህንጻ ላይ የሚገኙ ከመሆኑ አንጻር በአሁኑ ወቅት በጥብቅ ተከልሎ ይገኛል።
ዩክሬን በተመሳሰይ መልኩ በሩሲያ ላይ ጥቃት ፈጽማለች።
የሩሲያ መካላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የአየር መቃወሚያው 69 የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትቶ እንደጣለ ወይም አቅጣጫ ማስቀየር እንደቻለ አስታውቋል።
ዩክሬን በሩሲያዋ ቤልጎሮድ ግዛት በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ቭያስቼስላቭ ግላድኮቭ እሁድ ዕለት አስታውቀዋል።















