የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በፖላንድ መመታታቸውን ተከትሎ ኔቶ መከላከያውን አጠናከረ

የፖላንድ ጦር አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፖላንድ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ አየር ክልሏ መግባታቸውን ማሳወቋን ተከትሎ የኔቶ አባል አገራት ጥበቃውን ለማጠናከር በሚል በርካታ ወታደሮችን፣ መድፍ እና የአየር መከላከያዎችን እየላኩ ነው።

ረቡዕ ረፋድ ላይ ሦስት የሩስያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ ፖላንድ አየር ክልል ከገቡ በኋላ ተመትተዋል።

ሌሎች ሰው አልባ አውሮፕላኖች መሬት ላይ ከወድቁ በኋላ በፖላንድ ምሥራቃዊ አካባቢ ተገኝተዋል።

ፖላንድ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንዲመከር የጠየቀች ሲሆን ስብሰባ አርብ እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዟል።

ኔዘርላንድስ እና ቼክ ሪፐብሊክ መከላከያ ወደ ፖላንድ እንደሚልኩ ሲገልጹ ሊትዌኒያ ደግሞ የጀርመን ብርጌድን እንደምትቀበል እና የሩሲያ ጥቃቶች በዩክሬን ላይ ሊሻገሩ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ደርሷታል።

ጀርመን በኔቶ ምሥራቃዊ ድንበር ላይ ግንኙነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል እና በፖላንድ የአየር ጥበቃውን እንደምታሰፋም አስታውቃለች።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው የፖላንድን የአየር ክልል ለመጠበቅ ሦስት ራፋሌ ተዋጊ ጄቶች እንደምትልክ አስታውቀዋል።

ማክሮን "ለተጧጧፈው የሩሲያ ማስፈራሪያ አንንበረከክም" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አጋጣሚው በስህተት የተፈጠረ ሊሆን እንደሚችል ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"ከሁኔታው ጋር በተያያዘ ምንም ደስተኛ አይደለሁም። ጉዳዩ ግን ያበቃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል ትራምፕ።

የፖላንድ መከላከያ ሚኒስትር ቭላዲስላውቭ ኮሲኒያክ-ካሚዝ ሐሙስ ዕለት በፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የፖላንድ አጋሮችን ድጋፍ ዘርዝረዋል።

በዚህም ኔዘርላንድስ የአየር መከላከያ፣ መድፍ እና 300 ወታደሮችን ልታሰማራ መሆኑን እና ቼክ ሄሊኮፕተሮችን እና 100 ወታደሮችን እንደምትልክ ተናግረዋል።

ፈረንሣይ እና እንግሊዝ የኔቶን ምስራቃዊ ድንበር ለመጠበቅ አውሮፕላኖችን ሊያሰማሩ እንደሚችሉም አክለዋል።

"ፖላንድ በታሪኳ ውስጥ የአብሮነት እና ባዶ ቃላቶችን ደጋግማ ሰምታለች። ዛሬ ግን ተጨባጭ መግለጫዎች አሉን" ብለዋል ኮሲኒያክ-ካሚዝ።

ምንም እንኳን የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች ወደ አንዳንድ የኔቶ አባል አገራት ዘልቀው የገቡ ቢሆንም፣ ይህ ሞስኮ እአአ በ2022 ክሬንን ከወረረች በኋላ ያጋጠመ ከፍተኛ ክስተት ነው።

ሩሲያ ሆን ብላ በፖላንድ ውጥረት ለመፍጠር ፈልጋለች ለሚለው ውንጀላ ምንም ተጨማሪ አስተያየት የለኝም ብሏል ክሬምሊን።

ሆኖም በርካታ የፖላንድ እና የአውሮፓ መሪዎች ወረራው ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው ብለው ያምናሉ።

የፖላንድ ፕሬዝዳንት ካሮል ናውሮኪ በጀርመን እና በፈረንሣይ አቻዎቻቸው የተሰጡ አስተያየቶችን በማስተጋባት "ይህ የሩሲያ ትንኮሳ… አቅማችንን ለመፈተሽ ከመሞከር ያለፈ አይደለም" ብለዋል።

ሞስኮ ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን ወደ ፖላንድ አየር ክልል በማስገባቷ ዙሪያ የባለሙያዎች አስተያየት ተከፋፍሏል።

የፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኔቶ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ የሆኑት አሌክስ ግሪንኬዊች ሐሙስ ዕለት ድርጊቱ ሆን ተብሎ ይሁን አይሁን እስካሁን የታወቀ ነገር አለመኖሩን ገልጸው ወደ ፖላንድ አየር ክልል የተሻገሩ ድሮኖችን ቁጥር እንኳን አይታወቅም ብለዋል።

ከሩሲያ ጋር በሚያዋስኑት አገራት ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ ኔቶም ሆነ ፖላንድ ምንም አይነት ጥርጣሬ አልገባቸውም።

ዋርሶው ከቤላሩስ እና ዩክሬን ጋር በምትዋሰንበት በምሥራቃዊ ድንበሯ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና አነስተኛ የአየር ትራፊክ ላይ ገደብ የምታስቀምጥ ሲሆን ላትቪያ የምሥራቃዊ የአየር ክልሏን ለአንድ ሳምንት እንደሚዘጋ አስታውቃለች።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የዩክሬን መከላከያ በየምሽቱ እንደሚያደርገው የሩሲያ የአየር ላይ ጥቃትን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ለምዕራባውያን ጦር መመሪያ እና ስልጠና ለመስጠት ሃሳብ አቀርበዋል።

ለሩሲያ "አሳፋሪ" ባህሪ ምላሽ ለመስጠት የጋራ የአየር መከላከያ ስርዓት በአውሮፓ ላይ እንደ አየር መከላከያ ጋሻ ሆኖ እንዲያገለግል ዜለንስኪ ጠይቀዋል።

በአንዳንድ የምሥራቅ አውሮፓ አካባቢዎች የሚሰማውን ጭንቀት የሚያንረው ደግሞ በቤላሩስ እና ሩሲያ መካከል ዛፓድ 2025 የሚል ስያሜ የተሰጠው ታላቅ ወታደራዊ ልምምድ አርብ ሊጀመር መሆኑ ነው።

ፖላንድ ከሐሙስ ጀምሮ "በብሔራዊ ደህንነት እና ከዛፓድ ጋር በተያያዘ" ድንበሯን ዘግታለች።

ሩሲያ በበኩሏ የፖላንድ ባለስልጣናት ከቤላሩስ ጋር ያላቸውን ድንበር እንዲከፍቱ አሳስባለች። ድንበሩ መዘጋቱ በንግድ እና በእንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ብላለች።

"ዋርሶ እንደዚህ አይነት አጥፊ እርምጃ የሚያስከትለውን ውጤት እንድታስብ እና ውሳኔውን በተቻለ ፍጥነት እንደገና እንድታጤነው እንጠይቃለን" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ተናግረዋል።

የቀደመው የዛፓድ ወታደራዊ ልምምድ የዩክሬን ጦርነቱ ከመጀመሩ ከበርካታ ወራት በፊት የተካሄደ ሲሆን 200 ሺህ ወታደሮችን አሳትፏል።

የሊቱዌኒያ ወታደራዊ የስለላ ሃላፊ ሚንዳውጋስ ማዞናስ እንዳሉት ከሆነ የዘንድሮው ልምምድ በመጠኑ ያነሰ ሲሆን እስከ 30 ሺህ ወታደሮችን ብቻ ያሳትፋል።