የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ምንድነው? አባላቱስ እነማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰሞኑ ዶናልድ ትራምፕ ሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አገራት ማኅበር የሆነው ኔቶ አባላትን አስቆጥተዋል። የኔቶ አባል አገራት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ የማይፈጽሙ ከሆነ ሩሲያ “ልክ እንድታስገባችሁ አበረታታለሁ” ብለዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አስተያየት አውሮፓ እና አሜሪካን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ የቃል-ኪዳኑ ፕሬዝዳንት ብስጭታቸውን ገልጸዋል።
የኔቶ አባል አገራት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርታቸው (ጂዲፒ) 2 በመቶውን ለመከላከያ አቅም እንዲውሉ ይጠበቃሉ።
ከሰሜን አሜሪካ እና ከአውሮፓ የተውጣጡ አገራትን ያሰባሰበው ኔቶ፤ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ አዳዲስ አገራትን መመልመልና አቅሙን ማጠናከር ጀምሯል።

ኔቶ ምንድነው? መቼስ ተቋቋመ?
ኔቶ - የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት ነው። የተቋቋመው ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1949 ነበር።
በወቅቱ ድርጅቱን ያቋቋሙት 12 አገራት ሲሆኑ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና ፈረንሳይ ይገኙበታል።
ሲቋቋም ዓላማው የነበረው ሩሲያ አባል ከነበረችባት ሶሻሊስቷ ሶቪዬት ኅብረት በኩል የሚቃጣባቸውን ጥቃት ለመመከት ነው።
አባላቱ ስምምነታቸው እንዲህ ይላል - “አንድ አባል ተነካ ማለት ኅብረቱ ተነካ ማለት። አስፈላጊ ከሆነ አንድ አባል ለሚደርስበት ጥቃት በጋራ ወታደራዊ ምላሽ እንሰጣለን።”
ኔቶ የራሱ ጦር ሠራዊት የለውም። ነገር ግን አባል አገራት ችግር ሲያጋጥም ወታደራዊ አቅም አሰባስበው እርምጃ መውሰድ ይችላሉ። ወታደራዊ ዕቅድ ማውጣት እና ልምምድ ማድረግ ደግሞ በየጊዜው የሚያደርጉት ነው።
በአውሮፓውያኑ 2022 ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር ነው ኔቶ “አባሎቼ ቀጥተኛ እና አደገኛ የሆነ ስጋት ላይ ናቸው” ሲል መግለጫ ያወጣው።
የኔቶ አባል አገራት እነማን ናቸው?
ኔቶ ከአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ የተውጣጡ 31 አባል አገራት አሉት።
በ1991 (እአአ) የሶቪዬት ኅብረት ስትፈራርስ አብዛኞቹ የምሥራቅ አውሮፓ አገራት የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅቱን ተቀላቀሉ።
አልቤኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ሃንጋሪ፣ ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ስሎቫኪያ፣ ሩሜኒያ፣ ሉቲዌኒያ፣ ላትቪያ እና ኢስቶኒያ በወቅቱ ኔቶን የተቀላቀሉ የቀድሞ ሶሻሊስት አገራት ናቸው።
ስዊድን እና ፊንላንድ ደግሞ ግንቦት 2022 የእንቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል። ሁለቱ አገራት ይህን ያደረጉት ሩሲያ እንዳትተነኩሳቸው በመፍራት ነው።
ከሩሲያ ጋር 1340 ኪሎ ሜትር ድንበር የምትጋራው ፊንላንድ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የኔቶ አባል ሆናለች።
ስዊድን የኔቶ አባል ለመሆን ከሃንጋሪ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ይሁንታ እየተጠባበቀች ነው።
ቦስኒያ እና ሄርዜጎቭኒያ እንዲሁም ጆርጂያ ኔቶን መቀላቀል የሚፈልጉ አገራት ናቸው።

የኔቶ አገራት ምን ያህል ያዋጣሉ?
ኔቶ አባል አገራቱ ከብሔራዊ ገቢያቸው ቢያንስ 2 በመቶውን ለመከላከያ ወጪ እንዲያውሉ ይጠይቃል።
ዩናይትድ ስቴትስ ከአጠቃላይ ገቢዋ 3.5 በመቶውን ስታፈስ፣ ከሩሲያ ጋር ድንበር የሚጋሩ እንደ ፖላንድ እና የባልቲክ አገራት ደግሞ ከ2 በመቶ በላይ ለወታደራዊ አቅማቸው ማጠናከሪያ ያውላሉ።
ዩናይትድ ኪንግደምም እንዲሁ ከ2 በመቶ ትንሽ ከፍ ያለ ወጪ ለመከላከያዋ ታወጣለች።
ነገር ግን እንደ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን እና ስፔን ያሉ አገራት ከሚፈገለው 2 በመቶ በታች ለመከላከያቸው እንደሚያውሉ በ2023 የወጣ መረጃ ያሳያል።
ዩክሬን መቼ ነው የምትቀላቀለው?
ኔቶ ዩክሬን አባል አገር መሆን ትችላለች ቢልም፣ ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ለሚለው ጥያቄ እስካሁን ቁርጥ ያለ ምላሽ አልሰጠም።
መስከረም 2022 የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ “ይፍጠንልኝ” ብለው ላቀረቡት ጥያቄ ኔቶ የሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም።
ሩሲያ፤ ዩክሬን ኔቶን መቀላቀል የለባትም ስትል ተቃውሞዋን ከማሰማት ቦዝና አታውቅም። ይህ የምትለው የቃል-ኪዳኑ ጦር ወደ ደንበሯ እንዳይጠጋ በመስጋት ነው።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ጦርነት ላይ እያለች ኔቶን መቀላቀል እንደማትችል ብታውቀውም፣ ጦርነቱ እንዳበቃ ወዲያው መቀላቀል ትሻለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኔቶ አገራት ለዩክሬን ምን እያደረጉ ነው?
ኔቶ እንደ ቡድን ለዩክሬን የጦር መሣሪያ እርዳታ አላደረገም። ነገር ግን የኔቶ አባል የሆኑ በርካታ አገራት በግላቸው ድጋፍ አድርገዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን እና ቱርክ ፀረ-ታንክ እና የሚሳዔል መከላከያን ጨምሮ የተለያዩ ታንኮች እንዲሁም ወታደራዊ ድሮኖች አበርክተዋል።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ረዥም ርቀት የሚጓዙ ሚሳዔሎችንም ሰጥተዋል።
አሜሪካ የኔቶ አገራት ኤፍ-16 የተባሉትን ተዋጊ ጄቶችን ለዩክሬን እንዲሰጡ እና አብራሪዎችን እንዲያሰለጥኑ ፈቅዳለች።
ኔዘርላንድስ 18 ኤፍ-16 ተዋጊ የጦር ጄቶችን በቅርቡ ለዩክሬን ለመስጠት ቃል ገብታለች።
ቢሆንም የኔቶ አባል አገራት ወደ ዩክሬን ወታደሮቻቸውን አይልኩም። አሊያም አየር ኃይላቸውን ተጠቅመው በአገራቸው ሰማይ ላይ መብረር እንዳይቻል ማገድ አይፈልጉም። ይህ ሩሲያ ላይ የሚቃጣ ትንኮሳ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።
ኔቶ እየጠነከረ ነው?
በአውሮፓውያኑ 2023 የኔቶ ጦር አዛዦች የመልሶ ማጥቃት ዕቅድ ነደፉ። ይህ ዕቅድ ሩሲያ የአርክቲክ እና የሰሜን አትላንቲክ፣ የማዕከላዊ አውሮፓን አሊያም የሜዲትራኒያንን ግዛት ብታጠቃ ምን እናደርጋለን የሚለውን የሚያስስ ነው።
የካቲት 2024 ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ትልቁ የተባለውን ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል።
በምሥራቃዊ አውሮፓ የሚካሄደው ወታደራዊ ልምምድ ከ31 የኔቶ አባል አገራት የተውጣጡ 90 ሺህ የወታደሮች የሚሳተፉበት ነው።
ዩናይትድ ኪንግደም 20 ሺህ ወታደሮቿን ለመላክ ቃል ገብታለች።
ኔቶ በአውሮፓ በተጠንቀቅ የሚቆሙ ወታደሮቹን ቁጥር ከ40 ሺህ ወደ 300 ሺህ ለማሳደግ ያለውን ዕቅድ ይፋ አድርጓል።
በምሥራቅ በኩል ያለውን ጦርም ማጠናከር ጀምሯል። ይህ አካባቢ ከሩሲያ ጋር ድንበር የሚጋራ ነው።
ኔቶ በአሁኑ ወቅት ቡልጋሪያ፣ ሃንጋሪ፣ ሩሜኒያ፣ ስሎቫኪያ እና የባልቲክ አገራት ውስጥ 8 መቀመጫዎች አሉት። ከጦርነቱ በፊት አራት ብቻ ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












