ሩሲያ የኔቶ ወታደሮች በጦርነቱ ተሳትፈዋል ትላለች፤ ምን ያህል እውነት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኔቶ ወታደሮች “በምዕራባውያን አማካሪዎች ዕዝ ሥር” ባሉ ክፍሎች ውስጥ በዩክሬን ጦር ሜዳዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሩሲያ ቴሌቪዥንም እንዲሁ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወታደሮች በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ እንደሆኑ ዘግቧል።
ይኸው መረጃ በሩሲያ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተጋራ ይገኛል።
የኔቶ አባል አገራት የጦር መሣሪያ እና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ለዩክሬን ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ ነገር ግን የኅብረቱ አባል ላልሆነችው ዩክሬን ወታደሮቻቸውን አንልክም ብለዋል።
ሩሲያ እንደምትለው በጦርነቱ የኔቶ ወታደሮች ተሳታፊ ሆነዋል? ያሉትን መረጃዎች እንፈትሽ።
ሩሲያ ምን እያለች ነው?
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን መስከረም 11/2015 ዓ.ም. ባደረጉት ንግግር “የኪዬቭ አገዛዝ አዳዲስ ወሮበሎችን፣ የውጭ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮችን እና ፅንፈኞችን አሰማርቷል። እነዚህ ወታደራዊ ክፍሎች በኔቶ ደረጃ የሰለጠኑ እና በምዕራባውያን አማካሪዎች ዕዝ ሥር የሚመሩ ናቸው” ብለዋል።
የውጭ አገር ተዋጊዎች የዩክሬን ጦርን መቀላቀላቸው የሚታወስ ነው።
ነገር ግን የኔቶ ወታደሮች ለዩክሬን ወግነው በጦርነቱ እየተሳተፉ መሆናቸውን ነው የሩሲያ ባለሥልጣናት እና መገናኛ ብዙኃን እየተናገሩ ያሉት።
ከሳምንት በፊት በሩሲያ ቴሌቪዥን ‘ቭረምያ ፖካዝኸት’ የተሰኘው ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው ሩስላን አስታሽኮ “ነገሮችን ሰፋ አድርገን ስናያቸው፤ የዩክሬን ወታደሮች ፎቶዎችን ለመነሳት፣ ቪዲዮዎችን ቀርጾ በቲክቶክ ላይ ለመለጠፍ በአጠቃላይ ለዕይታ ነው የመጡት። ነገር ግን በዚህ ጦርነት በዋነኝነት የሚዋጉት የኔቶ ወታደሮች ናቸው” ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Channel One
በዚህ ፕሮግራም ላይ በዩክሬን እየተዋጉ ናቸው የተባሉ የውጭ ዜጎችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ተወስደው የኔቶ ወታደሮች በዩክሬን መሬት ላይ እየተዋጉ እንዳሉ “በማስረጃነት” ቀርበዋል።
በዩክሬን ራሱን ምሥራቃዊ የሉሃንስክ ሕዝቦች ሪፐብሊክ ብሎ የሚጠራው ቡድን ወታደራዊ ቃል አቀባይ አንድሬ ማሮችኮ፣ ለሩሲያ መንግሥት የዜና ወኪል አርአይኤ ኖቮስቲ እንደተናገሩት “የእኛ የስለላ ደኅንነት ተቋም መደበኛ የኔቶ የጦር መኮንኖች በኻርኪቭ ግዛት በኩል መግባታቸውን ይፋ አድርጓል” ብለዋል።
“እነዚህ የጦር መኮንኖች ወደዚህች ግዛት የመጡበት ዓላማም በውጭ እና በዩክሬን ወታደራዊ ክፍሎች መካከል መስተጋብር ለመፍጠር ነው” ሲሉም አስረድተዋል።
አንድሬ የኔቶ የጦር መኮንኖች በዩክሬን ዶኔትስክ ግዛት በምትገኘው ክራማቶርስክ ከተማ መድረሳቸውን ለሩሲያ መንግሥት ቴሌቪዥን በተጨማሪ ተናግረዋል።
ሌሎች እየተባሉ ያሉ ጉዳዮች የውጭ ተዋጊዎች መኖራቸውን የሚመለከት ቢሆንም በቀጥታ ከኔቶ ጋር ግንኙነት አላቸው ባይባልም ጥያቄዎችን ግን አጭረዋል።
ሪአይኤ ኖቮስቲ ለተባለው መገናና ብዙኃን አምደኛ የሆነው ቭላድሚር ኮርኒሎቭ “የኢዚዮምን ግዛት ነፃ ለማውጣት መጣን የሚሉና እንግሊዝኛ የሚናገሩ ግለሰቦች ቪዲዮዎች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል” ብሏል።
የቀረቡ ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?
ወደ ዩክሬን ራሳቸውን ችለው በበጎ ፈቃደኝነት በተጓዙት የውጭ አገር ተዋጊዎች እና በኔቶ አባል አገራት ተሰማርተዋል በተባሉ ወታደሮች መካከል ግልፅ የሆነ ልዩነት መኖሩን ማወቅ ይገባል።
የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን የኔቶ ወታደሮች በዩክሬን መሬት እየተዋጉ ስለመሆናቸው ምንም ማስረጃ አላቀረቡም፤ ነገር ግን እየጠቆሙ ያሉት የውጭ አገር ዜጋ የሆኑ ተዋጊዎች በጦር ሜዳዎች መኖራቸውን ነው።
በቭረምያ ፖካዝኸት ቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ከሚታዩት ተዋጊዎች አንዱ ማልኮልም ናንስ የተባለ የቀድሞ የአሜሪካ ባሕር ኃይል መኮንን ሲሆን፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ በዩክሬን ያለውን ቆይታ የራሱን ቪዲዮዎች በየጊዜው ይለጥፋል።
በቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ላይ አፅንኦት ከተሰጣቸው ቪዲዮዎች መካከል ማልኮልም ከኋላው ከባድ መሣሪያ ሲተኮስ የሚያሳይ ነው።
በዚህ ቪዲዮም ላይ ማልኮልም በከባድ መሣሪያ የደረሱ ስኬታማ ጥቃቶችን ያብራራል።
በትዊተር ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት የማልኮልም ዩክሬን ውስጥ መገኘት ድብቅ ወታደራዊ ዘመቻ ነው ለማለት አይቻልም።
በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ጦር ውስጥ እያገለገለ አይደለም። ማልኮልም በሚያዝያ ወር የዩክሬን የውጭ ጦር መቀላቀሉን ይፋ አድርጓል።
የሩሲያ መንግሥት ደጋፊ በሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ሌላ የተጠቀሰው ግለሰብ፣ በአሜሪካ ኢዳሆ ግዛት ያደገው ሮብ ሮይ ሌን የተባለው አሜሪካዊ ነው።
ሮብ በዩክሬን ወታደራዊ ክፍሎች ውስጥ የራሱን ቪዲዮዎች በመደበኛነት ይለጥፋል፤ እንዲሁም በዩክሬን ጦር ውስጥ ያሉ ሌሎች በርካታ የውጭ በጎ ፈቃደኛ ተዋጊዎችን ሰምም ይጠራል።
እነዚህ ቪዲዮዎች የሩሲያ መንግሥት ደጋፊ በሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ በሰፊው ተጋርተዋል።
ከዚህ ቀደም ወታደራዊ ልምድ እንዳለው የሚጠቁም ምንም የበይነ መረብ ማስረጃ ግን የለም።
የአሜሪካ መንግሥት የመከላከያ መሥሪያ ቤት ግለሰቡ ከአሜሪካ ጦር ኃይሎች ጋር ስላለው ግንኙነት አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ሮብ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ሁለት የብሪታኒያ ዜጎችን ጨምሮ በእሱ ወታደራዊ ክፍል ውስጥ ያሉትን ሌሎች የበርካታ አባላትን ስምም ጠቅሷል።
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር የቀድሞ ሠራተኞቹን የአገልግሎት መረጃ ወይም በጦርነት ዞኖች ውስጥ ስለሰጡት አገልግሎት ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጥም ብሏል።
ኔቶ ለዩክሬን ምን ድጋፍ እያደረገ ነው?
የኔቶ አባል አገራት ከፍተኛ መጠን ያለው የተራቀቀ የጦር መሣሪያ እና የሎጅስቲክስ ድጋፍ ለዩክሬን እየሰጡ ሲሆን፤ አሜሪካ ከፍተኛውን ድጋፍ በማድረግ የመሪነት ስፍራውን ይዛለች።
እነዚህ የጦር መሣሪያዎች በጦርነቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል ተብለው የሚታመኑትን እንደ የረዥም ርቀት ሮኬት ማስወንጨፊያዎች፣ ፀረ-ታንክ መሣሪያዎችና ሌሎችንም ያጠቃልላሉ።
እንዲሁም የኔቶ አባል አገራት በስለላ እና ወታደራዊ ዒላማዎችን በመምረጥ ረገድ እገዛ እያደረጉ ነው በሚልም የምዕራባውያን ሚዲያዎች መላምታቸውን አስቀምጠዋል።
ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ የኔቶ ወታደሮች በባልቲክ ግዛቶች እና ፖላንድ በመሳሰሉት የኅብረቱ አባል አገራት ውስጥ ሰፍረው የሚገኙ ሲሆን፤ ሌሎች 300 ሺህ ወታደሮች ደግሞ ለሩሲያ ወረራ ምላሽ ለመስጠት በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ።
በኔቶ አባል አገራት አማካኝነት የዩክሬን ጦር ኃይል ሰፊ ሥልጠና ከአገር ውጪ ሲደረግ ቆይቷል።
ነገር ግን የትኛውም የኔቶ አባል አገር ዩክሬን ውስጥ ለመዋጋት ወታደሮችን አበርክቻለሁ ብሎ የተናገረ የለም።
“የኔቶ ወታደሮች በዩክሬን መሬት ላይ በጦርነቱ ስለመሳተፋቸው ምንም ማስረጃ የለም” በማለት በሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት (ሩሲ) የመከላከያ እና የፀጥታ ጥናት ተቋም ሠራተኛ የሆኑት ኤድዋርድ አርኖልድ ተናግረዋል።
አክለውም “የዩክሬን ወታደራዊ ክፍሎችን በጦር ሜዳ የሚመሩ የኔቶ አዛዦችም የሉም። ኔቶ የግጭቶችን የመባባስ አደጋዎችን ለመቅረፍ በሚፈልግበት በአሁኑ ወቅት ቀርቶ ለወደፊቱም ቢሆን ይህ የመከሰት ዕድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው” ብለዋል።












