በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ማን እያሸነፈ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩክሬን ኃይሎች በቅርብ ቀናት ውስጥ በሩሲያ የተይዘውባቸው የነበሩ ሰፊ ቦታዎችን መልሰው በመቆጣጠር ፈጣን ግስጋሴን አሳይተዋል።
ሩሲያ ኃይሏን እያሰባሰበች እንደሆነና በአሁኑም ወቅት የዩክሬንን አንድ አምስተኛው በቁጥጥሬ ስር ነው ብላለች።
ጦርነቱ እንዴት ተቀየረ?
ሩሲያ የካቲት 17/2014 ዓ.ም. ዩክሬንን በመውረር ዋና ከተማዋን ኪዬቭን ከበበች። በተጨማሪም በዩክሬን ደቡብ፣ ምሥራቅ እና ሰሜን ምሥራቅ ክፍሎች ውስጥ ጥቃት ከፈተች።
ሩሲያ ወደ ዋና ከተማዋ የምታደርገውን ግስጋሴ ከተወች በኋላ በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ የዩክሬን ኃይሎች በኪዬቭ ዙሪያ ሰፋፊ ስፍራዎችን መልሰው ተቆጣጠሩ።
ሩሲያም ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን በዩክሬን ደቡባዊ፣ ምሥራቃዊ እና ሰሜን ምሥራቃዊ ክፍል ላይ በማተኮር ግዛቶቿን በመቆጣጠር ላይ ነበረች።
ነገር ግን በባለፉት ሳምንታት ሁኔታዎች በከፍተኛ ሁኔታ መለዋወጥ ጀምረዋል።
የዩክሬን ጦር በሰሜን ምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ባካሄደው ወሳኝ ጥቃት፣ የሩሲያን ኃይል ማስወጣት ችሏል። በኻርኪቭ ከተማ ዙሪያ ብቻ 3 ሺህ ካሬ ኪሎሜትር (300 ሺህ ሄክታር) ግዛት መልሶ መቆጣጠሩን አስታውቋል።
በአጠቃላይ ዩክሬን ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ8 ሺህ ካሬ ኪሎሜትር (800 ሺህ ሄክታር) በላይ የሚሆን ግዛት ከሩሲያ መልሳ እንደገና መቆጣጠሯን ገልጻለች። ይህም ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም ዩክሬን ያስመዘገበችው ከፍተኛ ስኬት ነው ተብሏል።
ዩክሬን ጳጉሜ 5/2014 ዓ.ም. ተቆጣጥሬያቸዋለሁ ያለቻቸው የኢዚየም እና የኩፒያንስክ ከተሞቿ ለሩሲያ ኃይሎች ቁልፍ የአቅርቦት ማዕከላት ነበሩ።
በዚህም ዩክሬን ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታዎች ያላቸውን ስፍራዎቿን መልሳለች።
በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በኬርሶን ግዛትም ዩክሬን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ናት።
የጦርነት ጥናት ተቋም የሆነው አይኤስደብሊው የዩክሬን ኃይሎች በሩሲያ ጦር ላይ “ከፍተኛ ሽንፈት” አድርሰዋል ብሏል።
የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ጀስቲን ብሮንክ በበኩላቸው ሩሲያ በኻርኪቭ የነበራት ይዞታዎች “አጠቃላይ ውድመት” ደርሶባቸዋል ብለዋል።
ሩሲያ ከእነዚህ ይዞታዎች መውጣት “በእርግጠኝነት ሩሲያውያን በሚያዝያ ወር ከኪዬቭ ካፈገፈጉ በኋላ ያየነው እጅግ አስደናቂ ነገሮችን የቀለበሰ” ሁኔታ ነው ይላሉ።
ሩሲያ ምን ምላሽ ሰጠች?
ሩሲያ ጦሯ ከኢዚየም እና ከኩፒያንስክ ከተሞች ማፈገፉን አረጋግጣለች። ይህም “እንደገና ለመሰባሰብ” እና ስልታዊ መውጣት ነው ብላለች።
በተጨማሪም በእነዚህ ይዞታዎች ላይ የምትፈጽማቸውን ወታደራዊ ጥቃቶች እንደምትቀጥልም አስታውቃለች።
ሆኖም የሩሲያ ጦር በሚያፈገፍግበት ወቅት ከፍተኛ መጠን ያላቸውን መሳሪያዎች ትቶ የወጣ ይመስላል።
በሩሲያ እጅ ያሉ ግዛቶች
እንደ አይኤስ ደብሊው ከሆነ ሩሲያ በአሁኑ ወቅት 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛቶች እንደተቆጣጠረች ነው።
እነዚህ በሩሲያ ይዞታ ስር ያሉ አካባቢዎች በአብዛኛው በምሥራቃዊ ዶንባስ ክልል፣ በደቡባዊ ዩክሬን እና ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2014 በኃይል ወደ ግዛቷ ባጠቃለለችው በክሪሚያ የሚገኙ ስፍራዎች ናቸው።
የዶንባስ ግዛት በዋነኝነት የሩሲያኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው። ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2014 ክሪሚያን ወደ ራሷ ግዛት ማቃጠላሏን ተከትሎ የሩሲያ ደጋፊ ኃይሎች አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን የዶንባስ ግዛት ተቆጣጠሩ። በሁለቱም ግዛቶች የሕዝባዊ ሪፐብሊኮች የሚልም ተገንጣይ ግዛቶችን መስርተዋል።
ሊቪቭን ጨምሮ በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኙ ስፍራዎች የሚሳኤል ጥቃት ቢደርስባቸውም ነገር ግን የሩሲያ ኃይሎች እነዚህን ስፍራዎች ለመቆጣጠር ሙከራ አላደረጉም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ የምትፈልገው ምንድን ነው?
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ጦርነት በሚል አትጠራውም በተቃራኒው “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” እያካሄድኩ ነው ትላለች።
የሩሲያ መንግሥት “በመጀመሪያ የታቀዱ ሁሉም ተግባራት እስኪከናወኑ ድረስ” ዘመቻው እንደሚቀጥል ተናግሯል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በየካቲት ወር በዩክሬን ወረራ ሲፈፅሙ “ዩክሬንን ከጦረኝነት ማላቀቅ” ነው ብለዋል።
አንደኛው አላማም የምዕራባውን የመከላከያ ጥምረት የሆነውን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) እንዳትቀላቀል ማድረግ ነው።
የሩሲያ የመጀመሪያ ዓላማ ዩክሬንን በመውረር መንግሥቷን ከሥልጣን ማውረድ ነበር።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት በዩክሬን ምሥራቃዊ እና ደቡባዊ ክፍሎች ውስጥ የተቆጣጠረችውን ይዞታዎች ወደ ማስጠበቅ የተወሰነ ይመስላል።
ዩክሬን የምትፈልገው ምንድን ነው?
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እንዳሉት ዋነኛ አላማቸው ሁሉንም የሩሲያ ወታደሮችን አስወጥቶ “ግዛታችንን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር” ነው።
ዜሌንስኪ ሩሲያ የተቆጣጠረቻቸውን ይዞታዎች ለመመለስ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እና መሳሪያ ጠይቀዋል።
የዩክሬን ኃይሎች ከምዕራባውያን የተለገሳቸውን የጦር መሳሪያዎች በገፍ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጦርነቱ ምን ያህል ሰዎች ሞቱ?
ሁለቱም አገራት ያጧቸውን ሰዎች ቁጥር ይፋ ባያደርጉም ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው እርግጥ ነው።
ዩክሬን ከ50 ሺህ በላይ የሩሲያ ወታደሮችን ገድያለሁ ያለች ሲሆን፣ ነሐሴ መጨረሻ ላይም ዘጠኝ ሺህ ወታደሮቼን አጥቻለሁ ብላለች።
ለሩሲያ የወታደሮቿን ሞት ይፋ ማድረግ የተለመደ አይደለም።
የሟቾችን ቁጥር ለመጨረሻ ጊዜ ይፋ ያደረገችው መጋቢት ወር ላይ ሲሆን፣ በጦርነቱ ጀምሮ ወቅት 1351 የሩሲያ ወታደሮች መሞታቸውን ገልጻለች።
በሐምሌ ወር የአሜሪካ ባለሥልጣናት ወደ 15 ሺህ የሚጠጉ የሩሲያ ወታደሮች እንደሞቱ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በዚህ ጦርነት ሲቪሎችም ሞተዋል። በዚህ በመስከረም ወር የተባበሩት መንግሥታት ከ5700 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጧል።
ይሁን እንጂ ትክክለኛው ቁጥር በጣም ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁሟል።












