ኔቶ ምን ያህል ኃያል ነው? ለሩሲያ ለምን ራስ ምታት ሆነ?

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty
ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯ ለኔቶ በ73 ዓመት ታሪኩ አይቶትና አጋጥሞት የማያውቅ ፈተና ሆኖበታል።
አሁን ላይ ጦርነቱ እየተካሄደ የሚገኘው የኔቶ አባል አገራት በሚጋሩት የዩክሬን ድንበር በኩል ሲሆን ጥቂት የማይባሉ አባል አገራት በቀጣይ ሩሲያ ልትወረን ትችላለች የሚል ስጋት አላቸው።
አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና በርካታ የአውሮፓ አገራትን በአባልነት የያዘው ኔቶ በምሥራቃዊ አውሮፓ በኩል ተጨማሪ ወታደሮችን እያንቀሳቀሰ ይገኛል።
ዩናይትድ ኪንግደምና አሜሪካ ግን ወታደሮችን ወደ ዩክሬን የማስገባት ምንም አይነት እቅድ እንደሌለ ገልጸዋል።
ኔቶ ምንድነው?
የሰሜን አትላቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ወይም ኔቶ በአውሮፓውያኑ 1949 ላይ በ12 አገራት ነበር የተመሰረተው። በወቅቱ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ያካትት ነበር።
አባል አገራት ወታደራዊ ጥቃት ከደረሰባቸው እርስ በርሳቸው ለመደጋገፍ ነው ይህንን ስምምነት የተፈራረሙት።
አባል አገራት ከዚህ ስምምነት የደረሱት የሶቪየት ሕብረት አውሮፓ ውስጥ የመስፋፋት እቅድን ለመከላከል ያለመ ነበር።
እአአ 1955 ላይ ሶቪየት ደግሞ ለዚህ ስምምነት ምላሽ በሚመስል መልኩ የምሥራቅ አውሮፓ ኮምዩኒስት አገራት ጥምረት የሆነውን 'የዋርሶ ስምምነት' የተሰኘ ስብስብ አቋቋመች።
ነገር ግን እአአ 1991 ላይ የሲቪየት ሕብረት መፍረስን ተከትሎ በርካታ የዋርሶ ስምምነትን የፈረሙ አገራት ድርጅቱን እየለቀቁ ኔቶን መቀላቀል ጀመሩ።
በአሁኑ ወቅት ኔቶ 30 አባል አገራት አሉት። እነዚም የሚከተሉት ናቸው፡
አልባኒያ፣ ቤልጂየም፣ ቡልጋሪያ፣ ካናዳ፣ ክሮሺያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ኢስቶኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ሃንጋሪ፣ አይስላንድ፣ ጣሊያን፣ ላቲቪያ፣ ሊቱዌኒያ፣ ላክሰዘምበርግ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሰሜን መቄዶኒያ፣ ኖርዌይ፣ ፖላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ሩሜኒያ፣ ስሎቫኪያ፣ ስሎቬኒያ፣ ስፔን፣ ቱርክ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty
ሩሲያ ከኔቶ እና ከዩክሬን ጋርለምን ተፋጠጠች?
ዩክሬን የቀድሞ የሶቪየት ሕብረት አባል ስትሆን ሩሲያንና የአውሮፓ ሕብረትን ታዋስናለች።
የዘር ግንዳቸው ከሩሲያ የሚመዘዝ በርካታ ሚሊየኖች የሚኖሩባት ዩክሬን ከሩሲያም ጋር ጠንከር ያለ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ቁርኝት አላት።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዩክሬን ወደ ምዕራባውያኑ እያማተረች ነው። በተጨማሪም የአውሮፓ ሕብረት እና ኔቶን የመቀላቀል ፍላጎቷ በይፋ በሕገ-መንግሥቷ ላይ ሰፍሯል።
በአሁኑ ወቅት ዩክሬን የኔቶ 'አጋር አገር' ትባላለች። ይህ ማለት ዩክሬን ወደፊት ጥምረቱን እንድትቀላቀል ማግባባት መኖሩን ያመለክታል።
ሞስኮ ግን ይህ ፈጽሞ እንደማይሆን ከምዕራባውያኑ ማረጋገጫን ትፈልጋለች።
ይሁን እንጂ ዋሽንግተን እና አጋሮቿ ዩክሬንን ከኔቶ ማገድን አይፈልጉም፤ እንደ አንድ ሉዓላዊት አገር ዩክሬን በደኅንነት ጉዳዮቿ ላይ የራሷን ውሳኔ የመስጠት መብት አላት በማለት።
ፑቲንን ያሳሰባቸው ሌላው ነገር ምንድነው?
ፕሬዝደንት ፑቲን ምዕራባውያኑ የኔቶን ጥምረት በመጠቀም ሩሲያ ላይ ከበባ ይፈጽማሉ ይላሉ። በዚህም ፑቲን ኔቶ በምሥራቅ አውሮፓ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲቆም ይፈልጋሉ።
ፑቲን እአአ 1990 ላይ ኔቶ ወደ ምሥራቃዊ አውሮፓ አይስፋፋም በሚል የተቀመጠውን የስምምነት ሰነድ አሜሪካ እየጣሰችው እንደሆነ በመግለጽ ይከራከራሉ። አሜሪካ ደግሞ እንደዚህ አይነት ቃል አልገባሁም ትላለች።
ኔቶ በበኩሉ ከሩሲያ ጋር የሚዋሰኑ አባል አገራት በቁጥር አነስተኛ መሆናቸውን እና እነዚም አገራት ከጥምረቱ የሚፈልጉት ወታደራዊ ድጋፍ ብቻ እንደሆነ ይገልጻል።
ሩሲያ እና ኔቶን በተመለከተ ምን ነበር?
ዩክሬናውያን እአአ 2014 ላይ አፍቃሪ ሩሲያ የሆኑት ፕሬዝዳንታቸውን ከሥልጣን ሲያባርሩ ሩሲያ ደግሞ በደቡባዊ ባሕረ ሰላጤ የምትገኘው ክሪሚያን በቁጥጥሯ ስር አደረገች። ሩሲያ በምሥራቃዊ ዩክሬን የሚገኙ የዩክሬን መንግሥት ተቃዋሚዎችንም መደገፏን ቀጥላለች።
በዚህ ሁሉ መካከል ኔቶ እርምጃ አልወሰደም፤ በበርካታ የምሥራቅ አውሮፓ አገራት ግን ወታደሮችን በማሰማራት ምላሽ ሰጥቷል።
ምናልባት ሩሲያ የኔቶ አባል አገራትን ለመውረር ሃሳብ ካላት ቀድሞ ለመከላከል እንዲያስችል ታስቦ ነው ይህ የተደረገው።
ኔቶ ኢስቶኒያ፣ ላቲቪያ፣ ሊዊቲኒያ፣ ሩሜኒያ እና ፖላንድ ውስጥ ነው ወታደሮቹን ያሰፈረው።
ከዚህ በተጨማሪም ኔቶ የሩሲያ አውሮፕላኖች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ለመከላከል በባልቲክ አገራት አካባቢ ያለውን አየር ጥበቃን በእጅጉ አጠናክሯል።
ሞስኮ በበኩሏ እነዚህ ኃይሎች ለቅቀው መውጣት እንዳለባቸው ስታሳስብ ቆይታለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሁኑ ጦርነት ኔቶ ምን አደረገ?
አሜሪካ በምሥራቃዊ ድንበሮች በኩል የኔቶን ኃይል ለማጠናከር በሚል ተጨማሪ 3ሺህ ወታደሮቿን ወደ ፖላንድና ሩሜኒያ ልካለች።
ከዚህ በተጨማሪም ለውጊያ ዝግጁ የሆኑ 8500 ወታደሮቿ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አዛለች። ነገር ግን ዩክሬን ውስጥ ምንም አይነት ወታደር የማስፈር እቅድ እስካሁን የለም።
ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን እና ፀረ ታንክ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን የላከች ሲሆን፣ የኔቶ አባል አገራትም ቢሆኑ አሜሪካ ሰራሽ መሳሪያዎችን ለዩክሬን እንዲያቀርቡ ፈቃድ ሰጥታለች።
ዩናይትድ ኪንግደም በበኩሏ 2 ሺህ ፀረ ታንክ አጭር ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን የላከች ሲሆን፣ 350 ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ፖላንድ ልካለች። በኢስቶኒያ በኩልም ተጨማሪ 900 ወታደሮችን ለመላክ አስባለች።
የደቡባዊ አውሮፓ እና የሮያል ናቫል መርከብን በመጠቀም ዩናይትድ ኪንግደም 1ሺህ ወታደሮች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አዛለች።
ምናልባት ከባድ የሆነ ሰብአዊ ቀውስ የሚከሰት ከሆነ ይህ መርከብ እርዳታ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
ዴንማርክ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድስ ደግሞ ተዋጊ ጀቶችን ወደ ምሥራቃዊ አውሮፓ እና ምሥራቃዊ ሜዲትራኒያን ባሕር ልከዋል።
ኔቶ ምን ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው?
ኔቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋጊ አውሮፕላኖችን እና መርከቦችን በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ያደረገ ሲሆን በሩሲያና በዩክሬን ድንበር አካባቢ ደግሞ ያሉትን የወታደሮች ቁጥር እንደሚጨምር ይጠበቃል።
40 ሺህ የሚደርሱ የተዘጋጁ ወታደሮቹን ሊያሰማራ ይችላል እየተባለ ነው።
በተጨማሪም በሩሜኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ተጨማሪ የውጊያ ቡድኖችን ሊያዘጋጅ እንደሚችልም የሚጠበቅ ሲሆን በፖላንድና ባልቲክ አገራት ያለውም እንቅስቃሴ ተመሳሳይ ነው።















