ሩሲያ እና ዩክሬን፡ ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ውስጥ የማንን ምክር ይሰማሉ?

ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቭላድሚር ፑቲን ቁልፍ ጉዳይ ላይ ሲወስኑ ማንን ያማክራሉ?

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ስትፈጽም ፕሬዝዳንቷ ቭላድሚር ፑቲን በሁለቱ አገራት ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ላይ ግዙፍ ተጽዕኖ ያላቸው ውሳኔዎችን ሰጥተዋል።

ፑቲን እነዚህን ውሳኔዎችን ሲያሳልፉ ከማን ጋር ነው የሚማከሩት? አንዳንዶች እንደሚሉት ለዚህ የፑቲን ወታደራዊ ውሳኔ ሚኒስትሮችና የደኅንነት ኃላፊዎች ያሉበት 'ሲሎቪኪ' የተባሉው ኃያል ቡድን ተጽእኖ ይኖረው ይሆን?

line

በሩሲያ ሁሉ ነገር የሚወሰነውና የሚታዘዘው በዋናነት በፕሬዝዳንቱ ነው። በዚህም ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያን የሚመለከቱ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ይሰጣሉ።

ምንም እንኳን ፑቲን በአገራቸው ጉዳይ ላይ ሰፊ የመወሰን ሥልጣን ቢኖራቸውም የሚያማክሯቸው ሰዎች በዙሪያቸው አሉ።

እነዚህም ለረጅም ጊዜ አብረዋቸው የሰሩና የሚያምኗቸው ሰዎች ናቸው። ከእነዚህም መካከልም በደኅንነት ተቋማት ውስጥ ያገለገሉት በፑቲን ዘንድ ከፍ ያለ ተደማጭነት አላቸው።

ቭላድሚር ፑቲን ራሳቸው በሶቪየት ዘመን በዓለማችን ግዙፍ የስለላ ተቋማት አንዱ የነበረውና አሁን የሩሲያ ፌደራል የደኅንነት አገልግሎት ወይም ኤፍኤስቢ በተባለው የተተካው ኬጂቢ ውስጥ ነው ሥራ የጀመሩት።

ታዲያ ፑቲን የሩሲያን የመሪነት መንበር ሲረከቡ የአገሪቱ የደኅንነት ተቋማት ኮሚቴ የሆነው 'ሲሎቪኪ' በሩሲያ ውስጥ ኃያል ሆኗል።

አምስቱ ኃያላን

የሩሲያን የአገር ውስጥ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በሚመለከት በጣም ቁልፍ ውሳኔዎች በአብዛኛው የሚወሰኑት በአገሪቱ የደኅንንት ምክር ቤት ነው።

ይህ ምክር ቤት (ሲሎቪኪ) 30 አባላት ያሉት ሲሆን በዋናነት የአገሪቱ የስላላ ድርጅት እና የውጭ ስለላ ቡድን፣ የአገር ውስጥ፣ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስትሮች እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈጉባኤዎች ይገኙበታል።

ኒኮላይ ፓትሩሼቭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፑቲን የቅርብ አማካሪ ናቸው የሚባሉት ኒኮላይ ፓትሩሼቭ

የደኅንነት ምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ኒኮላይ ፓትሩሼቭ፣ የሰለላ ተቋሙ ኃላፊ አሌክሳንደር ቦርትኒኮቭ እና የውጭ ስለላ ኃላፊው ሰርጌይ ናሪይሽኪን የረጅም ዘመን የፑቲን ወዳጆች ናቸው። ሁሉም ከፑቲን ጋር በ1970ዎቹ ሌሊንግራድ ውስጥ ከፑቲን ጋር አብረው ለኬጂቢ ሰርተዋል።

በተጨማሪም የመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭም ፑቲን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዙሪያ በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ላይ ከሚሰሟቸው አምስት ሰዎች መካከል ይገኙበታል።

ፑቲን የሚመሩት የደኅንነት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ የሆኑት ኒኮላይ ፓትሩሼቭ ከፕሬዝዳንቱ የቅርብ ሰዎች መካከል ኃያሉ እንደሆኑ ይነገራል።

ፓትሩሼቭ እና ፑቲን በ1970ዎቹ ኬጂቢ ውስጥ አብረው የሰሩ ሲሆን ከዚያም በ1999 (እአአ) ፑቲን ወደ ፖለቲካው ሥልጣን ሲሸጋገሩ ፓትሩሼቭ ፑቲንን ተክተው የሩሲያ የስለላ ድርጅት ኃላፊ ሆኑ።

በዚህም ሁለቱ ግለሰቦች የጠበቀ ቅርበት አላቸው ፑቲንም ከማንም በላይ ፓትሩሼቭ የሚሉትን ይሰማሉ ይባላል።

ሌላው ቁልፍ ግለሰብ ደግሞ የሩሲያው የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሹይጉ ናቸው። የፑቲን ታማኝ እና አማካሪ የሆኑት ሚኒስትሩ፣ በተጨማሪም የፑቲንን ተቃዋሚዎች ባሉበት አገር እያሳደደ መርዟል የሚባለው የሩሲያ ወታደራዊ የደኅንንት ተቋም ኃላፊ ናቸው።

የሩሲያ ፌደራል የደኅንንት ተቋም የሆነው ኤፍኤስቢ አዛዥ የሆኑት አሌክሳንደር ቦርትኒኮቭ በተመሳሳይ ከፑቲን ጋር ከአስርት ዓመታት በፊት ኬጂቢ ውስጥ ሰርተዋል።

የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሹይጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሹይጉ

የረጅም ጊዜ የደኅንነት ሥራ ልምድ ያላቸው ቦርትኒኮቭ በየዕለቱ የሚያቀርቡት የደኅንነት ሪፖርት ለፕሬዝዳንት ፑቲን የመረጃ ምንጭና ለሚሰጡት ውሳኔ እጅግ በጣሙን ወሳኝ ነው።

የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ በአገሪቱ የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያለው ሲሆን፣ ከፍ ያለ ብቃት ያለው የራሱ ልዩ ኃይል የሚያዝ ተቋም ነው።

ሌላው የፑቲን የቅርብ ሰው ሩሲያ ካሏት ጉምቱ ዲፕሎማቶች መካከል አንዱ የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ ናቸው። ላቭሮቭ በሚኒስትርነት ቦታው ላይ 20 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ አገልግለዋል።

ከፑቲን ጋር የመማርም ሆነ የመሥራት ዕድል ባይገጥማቸውም ላቭሮቭ በፕሬዝዳንቱ ዘንድ ተደማጭነትንና አክብሮትን አትርፈዋል።

ላቭሮቭ ከሌሎቹ የፑቲን የቅርብ ሰዎች በተለየ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በገነቡት የረጅም ጊዜ ቅርበት ሳይሆን በታታሪነታቸውና በሙያ ብቃታቸው ለመከበር የበቁ ባለሥልጣን ናቸው።

ሌላው ኬጂቢ ውስጥ ከፑቲን ጋር የሰሩት የውጭ የደኅንነት ኃላፊው ሰርጌይ ናሪይሽኪን ተደማጭ ከሆኑት የሩሲያ ባለሥልጣናት አንዱ ናቸው።

ናሪይሽኪን ከሌሎች የስለላ ተቋማት ኃላፊዎች በተለየ በሕዝብ የሚታወቁና ቢቢሲን ጨምሮ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው ቃለ ምልልስ የሚያደርጉ የደኅንነት ኃላፊ ናቸው።

ናሪይሽኪንን የሚያውቋቸው ሰዎች እንደሚሉት ለፑቲን ታማኝና የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ የሚወጡ ናቸው ይሏቸዋል።

በደኅንነት ሥራው ዘርፍ ያዳበሩት ልምድ ናሪይሽኪንን በሥልጣን ማማው ላይ በጥበብ ለመረማመድ ያስቻላቸው ሲሆን፣ ፑቲንም በሚያቀርቡላቸው የደኅንነት መረጃ ፍጹም ይተማመኑባቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ

የደኅንነት ምክር ቤቱና ፑቲን

በቅርቡ የተደረገውና በቀጥታ ለሕዝብ የተላላፈ ነው የተባለው የሩሲያ የደኅንነት ምክር ቤት ስብሰባ በአባላቱ ዘንድ ያለው ግንኙነትና አቋምን ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል።

በዚህ ስብሰባ ላይ ከዩክሬን ተለይተው በአማጺያን ቁጥጥር ስር ላሉት ሁለት ሪፐብሊኮች እውቅና መስጠትን የተመለከተው ውሳኔ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ቀርበው ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።

በስብሰባው ላይ በግማሽ ክብ ጠረጴዛ ላይ ከፑቲን ፊት የተቀመጡት የደኅንት ምክር ቤቱ አባላት አንድ በአንድ በፑቲን እየተጠሩ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም እንዲገልጹ ሲጠየቁ ነበር።

ይህ ስብሰባ ፑቲን በደኅንነት ምክር ቤቱ ላይ ምን ያህል ቁጥጥር እንዳላቸው ያሳየ ነው ተብሏል። በተለይ የውጭ የደኅንነት ኃላፊው ናሪይሽኪን ከፑቲን የገጠማቸውን ፈተናን አንዳንዶች እንደ ጥሩ ምሳሌ ይጠቅሱታል።

ቀደም ሲል በምስጢር የሚካሄደው የደኅንነት ምክር ቤቱ ስብሰባ ባልተለመደ ሁኔታ በሩሲያ ቴሌቪዥን መተላላፉ የተለየ አድርጎታል ተብሎ ነበር።

ምንም እንኳን ስብሰባው በቀጥታ የተላለፈ ነው ቢባልም በቪዲዮው ላይ በተደረገ ምርመራ ከተሳታፊዎቹ አንዱ ባሰረው የእጅ ሰዓት ላይ የታየው የጊዜ ልዩነት ተቀድቶ የቀረበ መሆኑን አመልክቷል።

የውጭ ስለላ ኃላፊው ሰርጌይ ናሪይሽኪን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የውጭ ስለላ ኃላፊው ሰርጌይ ናሪይሽኪን

ሌሎች

ከእነዚህ የደኅንት ምክር ቤቱ ባለሥልጣናት በተጨማሪ ፑቲን በተለያዩ የሩሲያ ተቋማት ውስጥ ካሉ ቁልፍ ግለሰቦችና ከሌሎችም ጋር እንደሚማከሩ ይነገራል።

የሩሲያን ቁልፍ ሰዎች ለዓመታት በቅርበት በማጥናት የሚታወቀው የፖለቲካ ተንታኙ ይቭጌኒይ ሚንቼንኮ፣ ከተጠቀሱት የፑቲን የቅርብ ሰዎች በተጨማሪ ባለፈው ዓመት ባወጣው ሪፖርት ሌሎችም እንዳሉ አመልክቷል።

ከእነዚህም መካከል የዋና ከተማዋ ሞስኮ ከንቲባ የሆኑት ሰርጌይ ሶቢያኒን እንዲሁም የመንግሥታዊው የነዳጅ ዘይት ተቋም ሮስኔፍት ኃላፊ የሆኑት ኢጎር ሴቺን ከፕሬዝዳንት ፑቲን የቅርብ ሰዎች መካከል እንደሚገኙ ጠቅሷል።

ቢሊየነሮቹ ወንድማማቾች ቦሪስ እና አርካዲ ሮተንበርግ የቭላድሚር ፑቲን የልጅነት ጓደኞች ከመሆናቸው ባሻገር በአሁኑ ጊዜ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ሰዎች እንደሆነ ይነገራል።

ከሁለት ዓመት በፊት ፎርብስ መጽሔት ባለሐብቶቹን በሩሲያ ውስጥ የናጠጡ ቤተሰቦች ሲል ጠቅሷቸው ነበር።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎም ዩናይትድ ኪንግደም በአገሪቱ ላይ ማዕቀብ ስትጥል የሁለቱ ወንድማማች ቢሊየነሮች ስም ማዕቀቡ ከሚመለከታቸው ሰዎች መካከል ተካቷል።

ከፑቲን ቢሊየነር ወዳጆች መካከል አርካዲ ሮተንበርግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከፑቲን ቢሊየነር ወዳጆች መካከል አርካዲ ሮተንበርግ