ሩሲያ እና ዩክሬን: የሩሲያው ኃያል መሪ ቭላድሚር ፑቲን ማን ናቸው?

ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቭላድሚር ፑቲን

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምንም እንኳን ዩክሬንን በመውረር ዓለምን ቢያነጋግሩም በአውሮፓውያኑ 2014 ክሪሚያን የሩሲያ አካል ካደረጉ በኋላ ግን አገራቸው በአካባቢው እንዲሁም በመላው ዓለም እንዲኖራት የሚፈልጉትን ተጽእኖ ደብቀው አያውቁም።

ፑቲን ከእአአ 2000 ጀምሮ ስልጣን ላይ የነበሩ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት በፕሬዝዳንትነት እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።

ከጆሴፍ ስታሊን በቀመጠልም ለረጅም ዓመታት አገራቸውን ያገለገሉ መሪ ናቸው ፑቲን።

ፑቲን በ2020 ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ በሚል የተካሄደው ብሔራዊ የድምጽ አሰጣጥ ከሥራ ዘመናቸው በላይ የሥልጣን ጊዜያቸውን አርዝሟል።

ፑቲን ገና እስከ 2036 ድረስ በሥልጣን ላይ የመቆየት እድል እንዲኖራቸው ያደርጋል።

ቭላድሚር ፑቲን እንዴት እዚህ ደረሱ?

የዓለም መገናኛ ብዙኃን ትኩረት የሆኑት ፑቲን ከወጣትንት ዘመናቸው አንስቶ በፖለቲካው እንዲሁም በግል ህይወታቸው የነበራቸውን እንቅስቃሴና ተሳትፎ እንደሚከተለው ቀርቧል።

የቀድሞ ሰላይ

አንዳንድ የፑቲን ተቺዎች የፑቲን አመለካከት በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ዘመን አስተሳሰብ የተቃኘ ነው ይሏቸዋል። ፑቲን የሶቪየት ሕብረት እንዳልነበር ሆና እስከምትፈራርስበት ጊዜ ድረስ 'ኬጂቢ' በተሰኘው የአገሪቱ የስለላ ተቋም ውስጥ ሰላይ ነበሩ።

በጣም ቅርብ የሚሏቸው ወዳጆቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ጋር በይፋም ይሆን በምስጢር ጠበቅ ያለ ወዳጅነት አላቸው።

ፑቲን የፖለቲካ ህይወታቸው የጀመረው በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ውስጥ ሲሆን በወቅቱም የሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ከንቲባ ዋና አማካሪ ነበሩ። ከንቲባው ፑቲን ዩኒቨርሲቲ ሳሉ ሕግ አስተምረዋቸዋል።

ከንቲባው በ1997 ላይ ኬጂቢን ተክቶ የተቋቋመው 'ኤፍኤስቢ' የተባለው የስለላ ተቋም ኃላፊ ሆነው ክሬምሊን ገቡ። ትንሽ ቆይተውም የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብለው ተሾሙ።

በ1999 የቀድሞ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቦሪስ የልሲን ከሥልጣናቸው በመልቀቅ ፑቲንን የሩሲያ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት በማድረግ ሾሟቸው።

ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, AFP

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ታዲያ ቭላድሚር ፑቲን በሥልጣን ቆይተዋል። ለሦስተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ሞክረው ያልተሳካለቸው ፑቲን፤ ከ2008 እስከ 2012 ድረስ ደግሞ በድጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

2012 ላይ በተካሄደው ምርጫ ደግሞ 66 በመቶ ድምጽ በማግኘት ብሔራዊ ምርጫውን አሸንፊያለሁ ቢሉም በርካቶች ግን ምርጫው ተጭበርብሯል ይላሉ።

ፑቲን በሶቪየት ሕብረት ዘመን የነበረውን ወታደራዊ ፉክክር በድጋሚ በማምጣት ጭምር እንዲሁም ከዚህ በፊት ተከልክሎ የነበረውን የጆሴፍ ስታሊንን ምስል በአደባባይ መስቀል ፈቅደዋል።

ሩሲያ የሰራችው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትም ቢሆን ስያሜው 'ስፑትኒክ ቪ' እንዲሆን የተደረገው ሶቪየት ሕብረት በ1957 ላይ ያመጠቀቻትን መንኩራኩር ለማስታወስ ነው።

ተቃርኖ ከምዕራቡ ዓለም ጋር

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዩክሬን ጋር ገብተውበት የነበረው አለመግባባት እንዲሁም በሶሪያው የእርስ በርስ ጦርነት ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድን በመደገፋቸው ምክንያት የምዕራቡ ዓለም አገራት ፑቲንን ይበልጥ በጥርጣሬ እንዲመለከቷቸው አድርጓል።

ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የሩሲያና የምዕራቡ ዓለም ግንኙነት የተገደበና በመጠራጠር ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለፑቲን ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸው ትልቅ መነጋግሪያ ሆኖ ነበር።

የአሁኑ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ግን ፑቲን 'ገዳይ' ናቸው ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

2021 ላይ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረት 48 በመቶ የሚሆኑ ሩሲያውያን ፑቲን ከ2024 በኋላም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ ይፈልጋሉ።

ምንም እንኳን በርካታ የምዕራቡ ዓለም መሪዎች ይህንን ያክል ቁጥር ያለው ደጋፊ ማግኘት ቢከብዳቸውም ሩሲያውያን ግን አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር የተሻለ አማራጭ የለንም ብለው ሊያስቡ ይችላሉ።

ፑቲን አገሪቱ የተረጋጋችና ሰዎች ሰርተው መቀየር የሚችሉባትን ሩሲያ መፍጠር ችለዋል። በሥልጣናቸው ወቅትም ከፍተኛ የሆነ መካከለኛ ገቢ ያለው ሕዝብ መፍጠር ችለዋል።

ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአገር ውስጥ አለመረጋጋት

በእድሜ ገፋ ያሉ ሩሲያውያን ከሶቪየት ሕብረት ውድቀት በኋላ ፑቲን ምን አይነት ለውጦችን እንዳመጡ ስለሚያውቁ በደንብ ይደግፏቸዋል። ነገር ግን ሌላ መሪ አይቶ የማያውቀውና አዲስ እየመጣ ያለው ወጣቱ ትውልድ ለፑቲን ያለው ድጋፍ እምብዛም ነው።

2021 ላይ እንኳን የፑቲን ቀንደኛ ተቺ የሆነው አሌክሲ ናቫልኒ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሩሲያውያን ወጣቶች በአደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ናቫልኒ የመንግሥትን ሙስና በማጋለጥና ፑቲን የሚመሩትን መንግሥት የሌቦችና የአጭበርባሪዎች ስብስብ ነው ብሎ በመተቸት ይታወቃል።

ይህንን ተቃውሞ ተከትሎም መንግሥት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

ከባድ የልጅነት ጊዜ

ፑቲን አስቸጋሪ የልጅነት ጊዜ እንዳሳለፉ ይነገራል። በልጅነታቸው በሰፈራቸው ከሚገኙ ልጆች ጋር ሁሌም እንደተጣሉ ነበር። ይህንን ተከትሎ ነው እራሳቸውን ለመከላከል በሚል የጁዶ ስፖርትን በልጅነታቸው መማር የጀመሩት።

የክሬምሊን ድረ ገጽ ላይ በሰፈረ አንድ መረጃ መሰረት ፑቲን ገና ታዳጊ ሳሉ ነበር የሶቪየት ሕብረት የስለላ ተቋም ውስጥ መስራት ይፈልጉ የነበረው።

''ከ15 ዓመታት በፊት የሌኒንግራድ ጎዳና አንድ ወርቃማ ሕግ አስተምሮኛል፤ ፍልሚያው የማይቀርልህ ከሆነ የመጀመሪያውን ቡጢ ሰንዝር የሚለው'' በማለት ፑቲን 2015 ላይ ተናግረው ነበር።

ፑቲን የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ስነ-ስርዓቶች ላይ በተደጋጋሚ ሲሳተፉ ይታያሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፑቲን የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ስነ-ስርዓቶች ላይ በተደጋጋሚ ሲሳተፉ ይታያሉ።

የቤተሰብ ሁኔታ

ፑቲን በርካታ ሚሊየኖችን የሚያንቀሳቅሱ ወዳጆች ያሏቸው ሲሆን እራሳቸውም ቢሆን ቀላል የማይባል ሀብት እንዳላቸው ይነገራል። ነገር ግን የቤተሰባቸውንና የራሳቸውን ገንዘብ ነክ የሆኑ ጉዳዮች በከባድ ምስጢር ነው የሚይዙት።

ፑቲን እና ባለቤታቸው ልዩድሚላ ከ30 ዓመታት ትዳር በኋላ የተፋቱ ሲሆን፣ ልዩድሚላ "በሥራ ፍቅር የሰከረ ሰው ነው'' ስትል ፑቲንን ገልጻቸው ነበር።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደሚለው ከሆነ የፑቲን ሴት ልጅ የሆነችው ካታሪና በሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ትገኛለች።

ሩሲያ ውስጥ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም በርካቶች በተደጋጋሚ የሚገልጹ ቢሆንም የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ግን እዚህ ግባ የሚባል የሕዝቡን ጥያቄዎች የሚያስተጋቡ ዘገባዎችን ሲሰሩ አይስተዋልም።

አሁን ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ አብዛኛው ሩሲያዊ ምን ያስባል የሚለው ለበርካቶች ግልጽ አይደለም። ነገር ግን ሕዝቡ ደገፈውም አልደገፈውም ወረራው ተጀምሯል። ሁሉም አይኖች ወደ ቭላድሚር ፑቲን ሆኗል።