የሩሲያ ጦር የቼርኖቤል የኒውክሌር ጣቢያን ተቆጣጠረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያ ወታደሮች የቼርኖቤል ኒውክሌር ጣቢያን መቆጣጠራቸውን የዩክሬን ባለሥስልጣናት አስታወቁ።
የዩክሬን ፕሬዝደንት አማካሪ ማይክሃሎ ፖዶሊአክ በአገሪቱ ላይ "የተቃጣው ዓላማ የሌለው ጥቃት በአውሮፓ ላይ ከፍተኛ ስጋትን ደቅኗል" ብለዋል።
እአአ 1986 ላይ በቼርኖቤል ኒውክሌር ጣቢያ ላይ የደረሰው ፍንዳታ በሰው ልጅ ታሪክ ከፍተኛ ውድመት እና የሕይወት መጥፋት አስክትሎ ነበር።
የዩክሬን ፕሬዝደንት የሩሲያ ወታደሮች በወረራቸው የሚቀጥሉ ከሆነ ተመሳሳይ ጉዳት ይደርሳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በተመሳሳይ የሩሲያን ወረራ ተከትሎ በኒውክሌር ጣቢያ ሌላ አደጋ ሊከሰት ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
እአአ 1986 ከኒውክሌር ጣቢያው ጋር በተያያዘ ፍንዳታ ካጋጠመ በኋላ በጣቢያው 32 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ሰዎች እንዳይኖሩ ተከልክሎ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ የሩሲያ ወታደሮች ወደተከለለው ቀጠና ትናንት ዘልቀው መግባታቸው ተገልጿል።
ዋይት ሐውስ በቼርኖቤል ኒውክሌር ጣቢያ ውስጥ የነበሩ ሰዎች በሩሲያ ወታደሮች ታግተው ስለመያዛቸው መረጃው አለኝ ብሏል።
ቼርኖቤል ከኪዬቭ በሰሜን አቅጣጫ 130 ኪሎ ሜትር ርቆ ይገኛል። የሩሲያ ወታደሮች ይህን ስፍራ መያዛቸው ወደ ኪዬቭ ለሚያደርጉት ጉዞ መተላለፊያ ይሰጣቸዋል ሲሉ የደኅንነት አማካሪዋ ሳማንታ ተርነር ይናገራሉ።
ሳማንታ ተርነር በኒውክሌር ጣቢያው አካባቢ የሚደረገው ውጊያ ለሰው ልጆች ጠንቅ የሆነ ራዲዮአክቲቭ አፈትልኮ እንዲወጣ ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በሼፊልድ ዩኒቨርሲቲ የራዲዮአክቲቭ ብክለት ተመራማሪ የሆኑት ክሌር ኮርክሂል ግን መሰል የኒውክለር ብክለት ያለበትን አካባቢ በመቆጣጠር ረገድ ከሩሲያውያን የበለጠ ልምድ ያለው የለም በማለት ይከራከራሉ።
ተመራማሪዋ ይልቁን አሳሳቢው ነገር ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ያጋጠመውን ብክለት ለማጽዳት የሚደረገውን ጥረት ይህ ጦርነት ያዘገየዋል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተይናገራሉ።
"አደጋው ካጋጠመ 30 ዓመታት አልፈዋል። እስካሁን አጽድተን አልጨረስንም። ይህ የ50 ዓመታት ሥራ ነው" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሄነሪ ጃክሰን ሶሳይቲ በተባለ ተቋም ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ታራስ ኩዚኦ በበኩላቸው የሩሲያ ጦር የቼርኖቤል ኒውክሌር ጣቢያን መቆጣጠሩ ለፑቲን የድል ምልክት ተደርጎ ሊታይ ይችላል ይላሉ።
ምንም እንኳ ሶቪዬት ሕብረት ከ30 ዓመታት በፊት ብትበታተንም፤ ፑቲን ይህን አምነው የሚቀበሉ ሰው አይደሉም ይላሉ።
የሶቪዬት መፈራረስ የጀመረው በቼርኖቤል ኒውክሌር ማብላያ ጣቢያን ከደረሰው አደጋ በኋላ በመሆኑ ሩሲያ ይህን ጣቢያ መያዟ ለፑቲን ትርጉም እንደሚኖረው ያስረዳሉ።
ፑቲን የኒውክሌር መሳሪያን እንደማስፈራሪያ ተጠቀው ምዕራባውያንን ለመገዳደር አሰበውም ሊሆንም ይችላል ይላሉ ዶ/ር ኩዚኦ።












