ለመንደሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጨው ኢትዮጵያዊ ተማሪ

በደቡብ ኢትዮጵያ በቦረና ዞን ለበርካታ ቤቶች ከባዮ ጋዝ ኤሌክትሪክ በማመንጨት የ14 ዓመት ታዳጊ በመንደሩ ክብርን ተጎናጽፏል።
ታዳጊው አዳን ሁሴን ዲዳ ይባላል በቱላ ድር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው።
አዳን ለዚህ ፕሮጀክት መጠንሰስ ምክንያት የሆነውም መንገድ፣ ሆስፒታልና መብራትን የመሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች የጎዶሏት ጎስቋላ መንደሩ ናት። የመንደሩ ነዋሪዎችንም ስቃይ ለማቃለልም መነሳሳሻ እንደሆነውም ተናግሯል።
በወላጆቹ ጓሮም ሁለት ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ የከብቶች እበትና የእንስሳት ፍግን ማብላላትም ጀመረ።
በዚህም ፈጠራው በመንደሩ ላሉ ስምንት ቤቶች በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ችሏል። ለእያንዳንዱ ቤትም 44 ብር ያህል በየወሩ ያስከፍላል።
በአካባቢው የሚኖሩት አብዛኞቹ አርብቶ አደሮች ሲሆኑ በዋነኝነትም የዕለት ጉርሳቸውም ሆነ የኑሯቸው መሠረት የቀንድ ከብቶቻቸው ናቸው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በዚያ አካባቢ በተከሰተው ድርቅም ምክንያት በርካቶቹ በድህነት ውስጥ ይገኛሉ።
በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና እና ሕዝቦች እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች በአራት አስርት ዓመታት ያልታየ የከፋ ድርቅ መከሰቱ ተገልጿል።
በአራቱ ክልሎች ባጋጠመው ሦስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች መጨናገፍ የተነሳ በተከሰተ ድርቅ በርካታ እንስሳት ሞተዋል፣ ሰብሎች ወድመዋል፣ የውሃና የምግብ እጥረት በርካቶችንም እያፈናቀለ መሆኑን የተለያዩ የረድኤት ተቋማት እየተናገሩ ነው።
በደቡብ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በእንስሳት መኖ እና ውሃ እጥረት ቢያንስ 267 ሺህ ከብቶች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ- ኦቻ ታኅሣሥ ወር ላይ ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

አዳን ቤተሰቦቹን ከዚህ የመብራት ፕሮጀክቱ በሚያገኘው ገንዘብ ይደግፋቸዋል።
"እስካሁን ባሳካሁት ነገር በጣም እኮራለሁ፣ የአካባቢው ሰዎች ከባትሪና ከኩራዝ ወጪዎች እንዳዳንኳቸው ይነግሩኛል። ልጆቻቸው የቤት ሥራቸውን ለመስራት እስከሚቀጥለው ቀን ድረስ ለመጠበቅ አይገደዱም። ማታ በየቤታቸው መስራትም ሆነ ማንበብ ይችላሉ" ብሏል።
መምህሩ ቦሩ ሶራ እንደሚናገሩት አዳን የመብራት ፕሮጀክቱን በመንደሯ ውስጥ ላሉ ሌሎች ቤቶች ለማዳረስ እየሰራ ነው። በመንገድ ችግር ምክንያት ወደ ከተማ ሄዶ የሚፈልገውን መሳሪያ ለመግዛት አዳጋች ቢሆንበትም እየጣረ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
"በፈጠራ የተሞላ ተማሪ ነው። ከባዮጋዝ በተጨማሪ ራዲዮዎችን እና ሌሎች ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን መጠገንና እስከ 100 ሜትሮች የሚበር አውሮፕላን እስከመሥራት ድረስ ብዙ ነገሮችን ሞክሯል" ብለዋል መምህር ቦሩ።
በአዳን በመነሳሳትም በትምህርት ቤቱ የሚገኙ በርካታ ተማሪዎች የራሳቸውን ፕሮጄክቶች ይዘው እየመጡ ነው።
የአዳን የወደፊቱ ህልም በያቤሎ አዲስ በተቋቋመው የቦረና ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና ትምህርቱን መከታተል ነው።












