ኢትዮጵያን በተመለከተ በአሜሪካ የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ ኤችአር 6600 ምን ይዟል?

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አዲስ ኤችአር 6600 የተባለ ረቂቅ ሕግ አስተዋውቀዋል።
ይህ በኒው ጀርሲው የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖወስኪ ለአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተዋወቀው ረቂቅ ሕግ ተፈጻሚ የሚሆን ከሆነ "በኢትዮጵያ ላይ የሚያርፈው ጠንካራ የአሜሪካ ክንድ" ይሆናል ተብሎለታል።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥት አጥብቀው የተቃወሙት ይህ ረቂቅ ሕግ በፕሬዝደንት ባይደን የሚጸድቅ ከሆነ አሜሪካ በደኅንነት፣ በፋይናንስ/በኢንቨስትመንት እና በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ አዲስ ማዕቀብ ትጥላለች።
የዚህ ረቂቅ ሕግ ይዘት ምንድን ነው?
ይህ ረቂቅ ሕግ ለአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 'የኢትዮጵያ የመረጋጋት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ሕግ' (Ethiopia Stabilization, Peace, and Democracy Act) በሚል ስያሜ ቀርቧል።
ረቂቅ ሕጉን ለምክር ቤቱ ያስተዋወቁት የኮንግረስ አባላት ሕጉ ተፈጻሚ ቢሆን በኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ሰላም እና የዲሞክራሲ ግንባታ ጥረቶችን ለመደገፍ ያስችላል ይላሉ።
ይህ ረቂቅ ሕግ ጥር 27 2014 ዓ.ም. ለውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ፣ ለሕግ ጉዳዮች ኮሚቴ፣ ለፋይናንስ አገልግሎቶች እና ለመከላከያ አገልግሎቶች ተመርቷል።
የቪዛ እና የንብረት እግድ
ይህ ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ መረጋጋት እና የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዳይኖር ምክንያት ናቸው በተባሉ ግለሰቦች ላይ ተጠያቂነትን ለማምጣት ፕሬዝደንት ባይደን ማዕቀብ እንዲጥሉባቸው የሚጠይቅ ነው።
ግለሰቦች ላይ የሚያነጣጥሩት ማዕቀቦች የንብረት እግድ እና የቪዛ ማዕቀቦችን ያጠቃልላሉ። በተጨማሪም፦
- በትግራዩ ጦርነትም ሆነ በአገሪቱ ባሉ ሌሎች ግጭቶች ዙሪያ የተኩስ አቁም ወይም ድርድር እንዳይደረግ እንቅፋት የሆነ ወይም ስምምነት እንዳይደረስ ጥረት ያደረገ፤
- የትግራዩ ግጭትም ወይም ሌሎች በአገሪቱ ያሉ ግጭቶች እንዲስፋፉ ምክንያት የሆነ ወይም የተባበረ፤
- የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸመ፣ የጦር ወንጀል፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ የዘር ማጥፋት እና ሌሎች በደሎችን የፈጸመ፤
- የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት የሆነ እና በሰብዓዊ እርዳታ ሥራ ላይ የተሰማሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ሕብረት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ጥቃት የሰነዘረ፣ ለመሰንዘር ያቀደ፣ የመራ፤
- በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት የተሳተፈ ወይም በፋይናንስ የደገፈ፤
ንብረቱ እንዳይንቀሳቀስ በፕሬዝደንት ባይደን ይወሰናል። ከንብረት እግዱ በተጨማሪ ከላይ የተጠቀሱትን ወንጀሎች ፈጽመዋል የሚባሉ ግለሰቦች የጉዞ እገዳ ይጠብቃቸዋል።
ክልከላዎቹን ተላልፈው የሚገኙ ሰዎች ቀድሞ በነበራቸው ቪዛ አሜሪካ መግባት አይችሉም፤ አዲስ ቪዛ አመልክተው ማግኘት አይችሉም እንዲሁም ይዘው የሚገኙት ቪዛ ይሰረዛል።
እግዱ በላይ በተጠቀሱት ግለሰቦች ላይ ተፈጻሚ ለማድረግ የአሜሪካ መንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት፣ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) አባል አገራት ጋር፣ ከአውሮፓ እና ከአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይተባበራሉ ይላል ረቂቅ ሕጉ።

የፎቶው ባለመብት, congress.gov
የደኅንነት እና ፀጥታ ድጋፍ ላይ የሚጣለው ገደብ
ይህ ረቂቅ ሕግ በፕሬዝደንቱ ከጸደቀበት ዕለት አንስቶ አሜሪካ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የምታደርገው የደኅንነት እና የፀጥታ ድጋፍ እንዲቋረጥ ይጠይቃል።
ይህ የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ መልሶ የሚቀጥለው አሜሪካ ያስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸው በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ተረጋግጦ ለሚመለከተው የኮንግረስ ኮሚቴ ከቀረበ በኋላ ነው።
አሜሪካ ካስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል፡-
- የኢትዮጵያ መንግሥት በእርስ በርሱ ጦርነትም ሆነ በሌሎች ግጭቶች የማጥቃት ወታደራዊ ኦፕሬሽን ሙሉ በሙሉ ሲያቆም፤
- የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ድርድር፤ ሕጋዊ እና ሁሉን አካታች ወደ ሆነ ብሔራዊ ምክክር ለመግባት እርምጃዎችን ሲወስድ፤
- መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለመጠበቅ ጥረት ማድረጉ እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ መፍቀዱ ሲረጋገጥ፤ የሚሉት ቅድመ ሁኔታዎች ይገኙበታል።

የፎቶው ባለመብት, Pool
በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኩል የሚጣለው ገደብ
ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግሥታት የሚሰጡ ብድሮች ወይም የብድር ማራዘሚያዎች እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፎች እንዳይፈቀዱ አሜሪካ ተሰሚነቷን እና ድምጽ የመስጠት መብቷን ትጠቀማለች ይላል ረቂቅ ሕጉ።
ከዚህ በተጨማሪም በኤርትራ እና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ለማጠናከር እና ሰላምን ለማምጣት አሜሪካ ከሌሎች ቁልፍ ድጋፍ አድራጊዎች ጋር ፖሊሲ ታበለጽጋለች።
ረቂቅ ሕጉ ይህ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን እና ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚደረጉ ድጋፎችን አይመለከትም።
ይህ የአሜሪካ መንግሥት የፋይናንስ እና ቴክኒካል ድጋፍ ክልከላ የሚቆመው በተመሳሳይ ከላይ የተጠቀሱት የአሜሪካ መንግሥት ቅድመ ሁኔታዎች ሲረጋገጡ ነው።
ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚደረግ ጥረት
ረቂቅ ሕጉ በትግራዩ የእርስ በርስ ጦርነት እና በሌሎች ግጭቶች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊነት መብት ጥሰቶችን እና ለወንጀሎቹ ተጠያቂዎች ናቸው የተባሉትን ለመለየት ፕሬዝደንት ባይደን የገንዘብ፣ የፋይናንስ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን ማድረግ እንዳለባቸው ይጠይቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ረቂቅ ሕጉ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለሚመረምሩ ተዓማኒነት ላላቸው ድርጅቶች የአሜሪካ መንግሥት መረጃ እንዲያጋራ ያስገድዳል።
ረቂቅ ሕጉ ዓላማው ምንድን ነው?
ይህን ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የኒው ጀርሲው የኮንግረስ አባል፤ ሕጉ ተፈጻሚ ቢሆን በኢትዮጵያ መረጋጋት እንዲመጣ የሚደረገውን ጥረት ያጠናክራል፤ የሰብዓዊ እርዳታ እና የዲሞክራሲ ግንባታን ያጠናክራል ይላሉ።
በተጨማሪም ረቂቅ ሕጉ ተፈጻሚ ቢሆን፤ የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ጨምሮ የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት እርስ በርስ በመተባበር በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እና ሌሎች ግጭቶች እንዲቆሙ ስትራቴጂ ይነድፋሉ።
እነዚህ የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በሰብዓዊነት ላይ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀሎች እና ለሌሎች በደሎች ተጠያቂነትን እንዲኖር ያደርጋሉ።
በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲያብብ፣ የሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ እና እርቅ እንዲወርድ ሌላው የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት ተልዕኮ እንደሚሆን በዚህ ረቂቅ ሕግ ላይ ሰፍሯል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ አሜሪካ በግጭቱ ውስጥ ሚና አላቸው በሚባሉ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ባለሥልጣናት እንዲሁም በአማራ ክልል እና በህወሓት መሪዎች ላይ ከዚህ በፊት የቪዛ ዕቀባ ጥላ ነበር።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ደግሞ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ ሆነው የተለያዩ ጥሰቶችን ፈጽመዋል የተባሉ ወገኖች ላይ ያነጣጠረ ዕቀባን ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መፈረማቸው ይታወሳል።
ይህ በሂደት ላይ የሚገኘው ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ በተለያዩ መስኮች ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖን ሊያስከችል እንደሚችል ይታመናል።















