ሩሲያ እና ዩክሬን: በዩክሬን ተማሪ የሆነችው ኢትዮጵያዊት፡ "የሚሳኤል ፍንዳታው ርችት መስሎኝ ነበር"

የፎቶው ባለመብት, Eleni Abrom
በዩክሬን መዲና ኪዬቭ ተማሪ የሆነችው ኢትዮጵያዊት፣ ሩሲያ በዋና ከተማ ላይ ጥቃት ስትከፍት የነበረው የሚሳኤል ፍንዳታ "ርችት" መስሎኝ ነበር ስትል ለቢቢሲ ተናገረች።
የኪዬቭ ነዋሪዋ እሌኒ አብሮም ሐሙስ የካቲት 17/2014 ዓ.ም ንጋት ከእንቅልፏ የቀሰቀሳት የሩሲያ ሚሳኤሎች ከባድ የፍንዳታ ድምጽ ነው ትላለች።
"እዚህ ርችት መተኮስ የተለመደ ነው። ድምጹ ከአንቅልፌ ሲቀሰቅሰኝ ርቸት መስሎኝ ነበር" በማለት ሁኔታውን ታስረዳለች።
ሕዝቡ በድንገተኛው የሩሲያ ጥቃት እጅጉን ተደናግጦ እንደሚገኙ የምትናገራው እሌኒ፤ "ያለው ሁኔታ ያስፈራል። የዩክሬን ዜጎች ሻንጣቸውን ይዘው ሲወጡ ነበር። እኛ ደግሞ የት ነው የምንሄደው ብለን ግራ ገብቶናል። ታክሲ ማግኘት አይቻልም። ሱፐርማርኬትም የለም። ባንክ በጣም ብዙ ወረፋ አለ። ቅድሚያ የሚሰጡት ለራሳቸው ዜጋ ነው። እንደ ሌላ አገር ዜጋ ከባድ ነው" በማለት ያሉበትን ሁኔታ ገልጻለች።
ከዛሬ ንጋት ጀምሮ ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመራቸው ይታወቃል። ይህን ተከትሎም በሩሲያ ሚሳኤሎች በመዲናዋ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ ወታደራዊና የደኅንነት ተቋማት ላይ የሚሳኤል ድብደባ ተፈጽሟል።
"ሙሉ ወረራ ተፈጽሞብናል" የሚሉት የዩክሬን ባለሥልጣናት፤ እስካሁን በሞስኮ ጥቃት ከ40 ያላነሱ ወታደሮች መገደላቸውን ገልጸዋል።
በዩክሬን ኪዬቭ ተማሪ እንደሆነች የምትናገረው እሌኒ በአገሪቱ ውስጥ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አለመኖሩንና እንደሌሎች ተማሪዎች አስፈላጊውን መረጃና ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉ ለቢቢሲ ተናግራለች።
"ማንም ክትትል አያደርግልንም። የኢትዮጵያ ኤምባሲ እዚህ የለም። ሩሲያ ነው ያለው። የሌሎች አገራት ዜጎች ከኤምባሲዎቻቸው የሚሰሙትን ሲነግሩን ነበር። ኤምባሲዎች ዜጎቻቸውን 'ውጡ' ሲሉ ነበር። ይሄ ለእኛ ደንገተኛ ነገር ነው የሆነብን። ተዘናጋን" ትላለች።
በኪዬቭ ብዙ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ባይኖሩም የተወሰኑ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ተማሪዎችን እንደምታውቅ እሌኒ ትናገራለች።
"ብዙ ኢትዮጵያዊ የለም ግን የማውቃቸው ተማሪዎች አሉ። ኪዬቭ ሰላም ላይሆን ስለሚችል ለፖላንድ ድንበር ወደምትቀርብ ሌቪቭ ወደምትባል ከተማ የሄዱ አሉ። 'ከምንቸኩል እዚሁ እንቆይ' ብለው ኪዬቭ የቆዩም አሉ።"

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አምስት የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወደ ሌቪቭ ከተማ መሄዳቸውንና ሌሎቹ ግን እንደእሷ ኪዬቭ ውስጥ መቅረታቸውን ገልጻ፣ ጥቃቱ መከፈቱን ተከትሎ ሁሉም ቤቱ ውስጥ ሆኖ የሚመጣውን እየተጠባበቀ ነው ስትል ያሉበትን ሁኔታ ትገልጻለች።
እሌኒ ይህ የሩሲያ ጥቃት በአገሪቱ ከፍተኛ ድንጋጤ የመፍጠሩን ያክል፤ ሁኔታው ምንም ያልመሰላቸው ዩክሬናውያን መኖራቸውን ትናገራለች።
"አንዳንድ ቸልተኛ ደግሞ አለ። ምንም የማይመስለው አለ። ውሻውን መንገድ ላይ የሚያናፍስ አለ። ሌላኛው በጣም ሰግቶ ሻንጣ ይዞ ሲወጣ ታያለህ" በማለት የሩሲያ ጥቃት በኪዬቭ ነዋሪዎች ላይ የፈጠረውን የሰሜት ልዩነት ታስረዳለች።
ጦርነቱ ሊባባስ ይችላል በሚል ምዕራባውያን አገራት ዲፕሎማቶቻቸውንና ዜጎቻቸው ከዩክሬን ከቀናት በፊት ሲያስወጡ የቆዩ ሲሆን፣ ጥቃቱ ሊከሰት እንደሚችል ሲጠበቅ ቆይቷል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወረራ ምዕራባውያንን አስቆጥቷል። በዚህም ሳቢያ ወደ ወታደራዊ ፍጥጫ የሚገቡ ከሆነ ከአውሮፓ ባሻገር መላው ዓለምን ከባድ ቀውስ ውስጥ ይከታል ተብሎ ተሰግቷል።
በዋና ከተማዋ ኪዬቭ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች በከተማዋ ከባድ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ተከትሎ ባገኙት መጓጓዣዎች ሁሉ በመጠቀም ወደሌሎች አካባቢዎች ሲሸሹ ታይተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥት በዩክሬን ያለው ሁኔታ በፍጥነት እየተቀያየረ ስለሆነ ጎረቤት አገራት ለስደተኞች በሮቻቸውን ክፍት እንዲያደርጉ ጠየቀ።
የተመድ የሰደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ፤ "ገና ከአሁኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች እየተመለከትን ነው። በርካታ ሰዎችም ከጥቃት ለመዳን ቤቶቻቸውን ጥለው እየሸሹ ነው" ብለዋል።
በርካታ የዩክሬን ጎረቤት አገራት የሩሲያን ወረራ ተከትሎ መኖሪያቸውን ጥለው የሚሰደዱ ሰዎችን ለመቀበል በዝግጅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የፖላንድ ጤና ሚኒስትር በአገሪቱ ድንበር አቅራቢያ የስደተኞች መቀበያ ስፍራ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ በተመሳሳይ ስደተኞችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ለማስተናገድ ጦራቸውን ወደ ድንበር እንደሚልኩ አስታውቀዋል።
ጀርመን በበኩሏ ስደተኞችን ለሚቀበሉ አገራት የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጻለች።












