የዩክሬን ፕሬዝዳንት ራሳችንን እንከላከላለን ሲሉ ሩሲያን አስጠነቀቁ

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ በማንኛውም ቀን "አውሮፓ ውስጥ ትልቅ ጦርነት" ልትጀምር እንደምትችል የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ አስጠንቅቀው ሩሲያውያን እርምጃውን እንዲቃወሙት ጠይቀዋል።

ምሽት ላይ ባደረጉት ንግግር ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመነጋገር ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱን አስታውቀዋል።

"ከሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጋር የስልክ ንግግር ለማድረግ ሞከርኩ። ውጤቱ ዝምታ ሆነ" ብለዋል ዜለንስኪ።

ሩሲያ ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የውጊያ መኪናዎች በዩክሬን ድንበር እንዳሏት ተናግረዋል።

ዜለንስኪ ንግግራቸውን ከዩክሬን ቋንቋ ወደ ሩስኪ በመቀየር ሩሲያውያን በዩክሬን ጉዳይ እየተዋሹ መሆኑን ጠቅሰው ጥቃትን እንዲቃወሙ በስሜት ተሞልተው ተማፅነዋል።

"(ጦርነቱን) ማን ሊያቆመው ይችላል? ሰዎች። እርግጠኛ ነኝ እነዚህ ሰዎች ከእናንተ መካከል ናቸው" ብለዋል።

የዩክሬኑ መሪ አገራቸው ለሩሲያ ጥቃት ዝግጁ መሆኗን ተናግረው "እነሱ [ሩሲያ] ጥቃት ካደረሱ፤ አገራችንን፣ ነፃነታችንን፣ ሕይወታችንን፣ የልጆቻችንን ሕይወት ሊወስዱ ከሞከሩ ራሳችንን እንከላከላለን" ሲሉ ቃል ገብተዋል።

ፕሬዝደንቱ አክለውም "ስታጠቁን የምታዩት ፊታችን እንጂ ጀርባችን አይሆንም" ሲሉ ለመጋፈጥ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን አማፂያን ቁጥጥር ስር ወደሚገኙት አካባቢዎች እንዲገቡ ከታዘዙ በኋላ ወታደሮቹ ወደ ድንበር መጠጋታቸውን ተከትሎ ነው ይህን ያሉት።

የምሥራቅ ዩክሬን ተገንጣይ ክልሎች ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸውን ሞስኮ ገልጻለች።

በዩክሬን የአየር ክልል መገደብ

ዩክሬን በአየር ክልሏ "ሊደርስ በሚችል አደጋ" ምክንያት የሲቪል በረራዎችን መገደቧን ሐሙስ አስታውቃለች።

የግጭት ቀጠና ተቆጣጣሪው ሴፍ ኤርስፔስ አውሮፕላኖች በስህተት ሊመቱ ወይም በሳይበር ጥቃት ሊጎዱ ይችላሉ ሲል ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ተከትሎ ነው እርምጃው የተወሰደው።

እርምጃው የሲቪል በረራዎችን ሙሉ በሙሉ ያገደ ስለመሆኑ መጀመሪያ ላይ ግልጽ አልነበረም። ማስጠንቀቂያው ለተጨማሪ ጊዜ ካልተራዘመ ሐሙስ የሚያበቃ ይሆናል።

ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ የሚገኘውን የዩክሬን አየር ክልል ከሞላ ጎደል በመዝጋቷ የሲቪል አቪዬሽን ማስጠንቀቂያ አውጥታለች።

ኦፕን ሶርስ ኢንተለጀንስ ሞኒተር እንዳለው ከሆነ ሞስኮ እርምጃው ስላለው "ገደብም ሆነ የማብቂያ ጊዜ" ተጨማሪ መረጃ አልተሰጠችም።

ዩክሬን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጅ ባለፈ በሩሲያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጠይቃለች።

ለ30 ቀናት የሚዘልቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለሥልጣናት የሰዓት እላፊ ገደቦችን ጨምሮ ከፍተኛ የደኅንነት እርምጃዎችን እንዲወስዱ ያስችላቸዋል።

ሩሲያ እአአ በ2014-2015 ለምሥራቅ ዩክሬን የተደረሰውን የሠላም ስምምነት በመጣስ የሉሃንስክ እና የዶኔስክ ህዝባዊ ሪፐብሊኮች ራሳቸውን የቻሉ መንግሥታት አድረጋ ዕውቅና ከሰጠች በኋላ ምዕራባውያን አገራት ተከታታይ ማዕቀቦች መጣላቸውን አስታውቀዋል።

ሞስኮ ወታደሮቿ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ይሰማራሉ ማለቷን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ውድቅ ሲያደርጉት ምዕራባውያን ደግሞ የማይረባ ብለውታል።

ሩሲያ ላለፉት ስምንት ዓመታት በምስራቅ ዩክሬን ደም አፋሳሽ በነበረው ግጭት አማጽያን ስትደግፍ ቆይታለች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተካሄደው ጦርነት 14,000 (አብዛኞቹ ሲቪሎች ናቸው) ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

አሜሪካ የሞስኮን ድርጊት የወረራ መጀመሪያ ምልክት አድርጋ ገልጻዋለች።

አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የመከላከያ ባለስልጣን ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት የሩሲያ ወታደሮች "ለመነሳት ዝግጁ ናቸው" በማለት በማንኛውም ጊዜ መጠነ ሰፊ ወረራ ሊኖር ይችላል ብለዋል።

እንደ አሜሪካ ግምት ከሆነ የሩስያ ጥቃት ስጋት ከሆነ ወራት የተቆየጠሩ ሲሆን ከ150,000 በላይ ወታደሮቿም በዩክሬን ድንበሮች አቅራቢያ ተሰማርተዋል።

የዩክሬን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕግ አውጭዎች ከፍተኛ ይሁንታ ያገኘ ሲሆን በመላ አገሪቱ ተግባራዊ ሆኗል።

ዩክሬን ዜጎቿ ሩሲያን ለቀው እንዲወጡ እያዘዘች ሲሆን "የሩሲያ ጥቃት እየተባባሰ በመምጣቱ" የቆንስላ ድጋፍ ሊገድብ ይችላል የሚል ምክንያት አቅርባለች።

ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ዩክሬናውያን በቋሚነት በሩሲያ ይኖራሉ ተብሎ ይታመናል። ከአንድ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ በስደተኛነት ይኖራሉ ይቆያሉ ይገመታል።

በኪዬቭ የሚገኘው ጦር ከ18 እስከ 60 ዓመት የሆናቸው ተጠባባቂዎችን ኃይሎች ቢበዛ ለአንድ ዓመት እንዲያገለግሉ እየጠራ ነው።

ረቡዕ ዕለት በመንግስት ድረ ገጾች እና ባንኮች ላይ ያነጣጠረ መጠነ ሰፊ የሳይበር ጥቃት ደርሷል።

እስካሁን ድረስ የሩስያ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ድንበር መግባታቸው ግልጽ አይደለም።

ሆኖም የአሜሪካ የሳተላይት ምስሎች በምዕራብ ሩሲያ በርካታ ወታደሮችን እና መሳሪያዎችን ማሰማራታቸውን እና ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎች በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው የቤላሩስ የአየር ማረፊያ ላይ እንደተሰማሩ ያሳያሉ።

ረቡዕ ምሽት ዲኔስክ እና ሉሃንስክ የዩክሬን ጥቃት ነው ብለው የገለፁትን የሩሲያ ኃይሎች እንዲከላከሉላቸው መጠየቃቸውን ክሬምሊን ገልጿል።

ጥያቄው ለወረራ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች ጠቁመዋል።

የተገንጣዩ መሪ ዴኒስ ፑሺሊን ባለፈው ሳምንት ዩክሬንን በቅርቡ ጥቃት ለመሰንዘር አቅዳለች በማለት ክስ አሰምቶ ሲቪሎች እንዲወጡ አዟል።

ዩክሬን ምንም ዓይነት ጥቃት አልታቀደም ያለች ሲሆን በኋላም የፑሺሊን መግለጫ ከሁለት ቀናት በፊት መቀረጹ ታውቋል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአገራቸው ጥቅም እና ደህንነት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ጠቅሰው ሞስኮ "ለቀጥታ እና ታማኝ ውይይት በሯ ክፍት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሩሲያ አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ሊያደርጉት የነበረውን ስብሰባ በመሰረዛቸው ተጨማሪ ውይይት አይጠበቅም።

የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ሐሙስ ለሚካሄድ አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ዓለም "አደጋ" እያጋጠማት እንደሆነ አስጠንቅቀው ችግሩ እንዲረግብ እንዲሠራም ጠይቀዋል።

በቀውሱ ምክንያት ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ለማቋረጥ ማሰባቸውን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ተናግረዋል።