ሩሲያ እና ዩክሬን: ሩሲያ ስለምን ጦሯን ወደ ዩክሬን ለማዝመት ፈለገች? ፑቲንስ ፍላጎታቸው ምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, EPA
ለወራት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን ለመውረር ስለማቀዳቸው ሲያስተባብሉ ነበር። አሁን ግን የሠላም ስምምነትን አፍርሰው ጦራቸውን በአማፂያን ቁጥጥር ስር በሚገኙ ሁለት የምስራቃዊ ዩክሬን ክልሎችን እንዲዘምቱ አዘዋል።
ምክንያታቸው ደግሞ "ሠላምን ለማስፈን" የሚል ነው።
ሩሲያ ባለፉት ጥቂት ወራት ቢያንስ 150 ሺህ ወታደሮቿን በዩክሬን የድንበር አካባቢዎች አሰማርታለች። የአሁኑ እርምጃ ለአዲሱ ወረራ የመጀመሪያ ምልክት ነው ተብሎም ተሰግቷል። ቀጥሎ የሚሆነው ነገር የአውሮፓን የደህንነት መዋቅር አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።
የሩስያ ወታደሮች ወደ የት ተላኩ? ለምን?
በአውሮፓውያኑ 2014 ሩሲያ ዩክሬንን ወርራ ነበር። በወቅቱ በፕሬዚዳንት ፑቲን የሚደገፉ አማፂያን በምስራቅ አቅጣጫ ቦታዎችን ከመያዝ ባለፈ ከዩክሬን ጦር ጋር እየተዋጉ ነው።
ዓለም አቀፉ የሚኒስክ የሠላም ስምምነት ቢኖርም ግጭቱ እንደቀጠለ ነው። የሩሲያው መሪ ሠላም አስከባሪ ያሏቸውን ወታደሮች በአማፂያን ቁጥጥር ስር ወዳሉ ሁለት አካባቢዎችን እየላኩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምዕራባውያን ሃሳቡን ከንቱ ያሉት ሲሆን ሞስኮ በቅርቡ በዩክሬን አዲስ ወረራ ለማድረግ አቅዳለች ብለው ያምናሉ።
ዩክሬን 44 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሲሆን ከሩሲያ እና የአውሮፓ ህብረት ጋር ድንበር ትጋራለች። አማጺያን በሚቆጣጠሯት ዶኔስክ ታንኮች መግባታቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች አሉ። የቅርብ ጊዜ የሳተላይት ፎቶዎች ደግሞ የሩስያ ጦር ከዩክሬን ድንበር ከ15-30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሰማራቱን ያሳያሉ።
ዩክሬን በምስራቅ ያለውን ጦርነት ካላቆመች ለሚኖረው ደም መፋሰስ ተጠያቂ እንደምትሆን ፕሬዝዳንት ፑቲን አስጠንቅቀዋል። ቀደም ሲልም ተከታታይ የውሸት ክስተቶች የነበሩ ሲሆን አንዱን ምክንያት በመጠቀም ሩሲያ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች።
የፑቲንና የዩክሬን ቁርሾ ምንድነው?
ዩክሬን ወደ አውሮፓ ተቋማት ማለትም ወደ ኔቶ እና አውሮፓ ህብረት የምታደርገውን እርምጃ ሩሲያ ስትቃወም ቆይታለች። አሁን ደግሞ ዩክሬን የምዕራቡ ዓለም አሻንጉሊት እንደሆነች እና በማንኛውም ሁኔታ ትክክለኛ ሃገር እንዳልነበረች ፑቲን ገልጸዋል ።
ዋና ፍላጎታቸው ደግሞ ዩክሬን የ 30 ሃገሮች የመከላከያ ሃይል ጥምረት የሆነውን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶን) እንደማትቀላቀል ምዕራባውያን ዋስትና እንዲሰጡ ነው።
እንደቀድሞዋ የሶቪየት ሪፐብሊክ አካል ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ጥልቅ ማህበራዊ እና ባህላዊ ግንኙነት አላት። ሩስኪ በሰፊው የሚነገርባት ቢሆንም ሩሲያ እአአ በ 2014 ከወረረቻት ጊዜ ጀምሮ ግንኙነቶቹ ተበላሽተዋል።
እአአ በ 2014 መጀመሪያ ላይ የሩሲያ ደጋፊ የነበሩት ፕሬዚዳንቷ ከስልጣን ሲወገዱ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት ፈጸመች። ከዚያ ወዲህ የምስራቁ ጦርነት ከ 14 ሺህ በላይ ሰዎችን ገድሏል ።
ለአማፂያኑ አካባቢዎች ዕውቅና መስጠት ለምን አደገኛ ሆነ?
እነዚህ የዶኔስክ እና የሉሃንስክ የሕዝብ ሪፐብሊኮች በሩሲያ ድጋፍ ባላቸው ሰዎች ይተዳደሩ ነበር።
ፑቲን ራሳቸውን የቻሉ መሆናቸውን ዕውቅና መስጠታቸው የሩስያ ወታደሮች ለመጀመሪያ ጊዜ እዚያ እንዲሰፍሩ ከማድረግ ባሻገር የጦር ሰፈር መገንባትም ይችላሉ።
በየቀኑ የተኩስ አቁም ጥሰቶች በሚታዩበት አካባቢ የሩሲያ ወታደሮችን ማስፈር ጦርነት የመከሰቱን አጋጣሚ ከፍተኛ ያደርገዋል። በሚንስክ የሠላም ስምምነት መሠረት ሁለቱ አማፂ ክልሎች የዩክሬን አካል ሆነው ልዩ ጥቅም ይኖራቸው ነበር። የፑቲን እርምጃ ግን ይህ እንዳይሆን ይከለክላል።
የበለጠ አሳሳቢው ደግሞ ሁለቱ አማፂ መንግስታት የያዙትን ውስን ግዛት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የዩክሬን ዶኔስክ እና ሉሃንስክ ክልሎችን ለመጠቅለል መመኘታቸው ነው።
"እኛ ዕውቅና ሰጥተናቸዋል። ይህም ለመመስረቻ ሰነዶቻቸው በሙሉ ዕውቅና እንሰጠዋለን ማለት ነው" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ዩክሬን በምስራቅ አቅጣጫ "የዘር ማጥፋት ወንጀል" ፈጽማለች በሚል የውሸት ውንጀላ ሩሲያ ለጦርነት ከተዘጋጀች ሰነባብታለች።
በአማፅያኑ በሚተዳደሩ አካባቢዎች ከ700 ሺህ በላይ ፓስፖርቶችን በመስጠትም የትኛውም እርምጃ የራሷን ዜጎች ከመጠበቅ አንፃር ነው በሚል ልትጠቅስ ተዘጋጅታለች።
ሩሲያ ምን ያህል ርቀት ትጓዛለች?
ፕሬዝዳንት ፑቲን በምስራቅ ያለውን የሠላም ስምምነቶች ላያፈርሱ ይችላሉ። የሚፈልጉትን ካላገኙ "ወታደራዊ-ቴክኒካዊ" እርምጃዎች ብቻ እንደሚኖሩ ገልጸዋል። ሞስኮ ቀደም ሲል "ሩሲያ ወረራ አትፈጽምም" ስትል አስታውቃለች።
ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ፍሬ የሚያፈሩ አይመስልም። ምዕራባውያን ሁኔታው ይጋጋላል ብለው ይሰጋሉ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው "2.8 ሚሊዮን ዜጎች መኖሪያ ሆነችው የዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ እናምናለን" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ካየነው የሩስያ ኃይሎች በምስራቅ፣ በሰሜን እና በደቡብ ዩክሬንን በማጥቃት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን መንግሥት ለማስወገድ ሊሞክሩ ይችላሉ። በክሬሚያ፣ ቤላሩስ እና ዩክሬን ምስራቃዊ ድንበሮች አካባቢ ያሉ ወታደሮችን ሊያስተባብሩም ይችላሉ።
ዩክሬን በቅርብ ዓመታት የጦር ኃይሏን የገነባች ሲሆን ሩሲያም ይህንን ልትጋፈጥ ትገደዳለች።
የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊ የሆኑት ማርክ ሚሌይ እንዳሉት የሩስያ ጦር ሃይሎች መጠን ሲታይ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባላቸው ከተማዎች ግጭቱ "አሰቃቂ" ሊያደርገው ይችላል።
የሩስያው መሪ ሌሎች አማራጮችም አሏቸው። ምናልባት ከበረራ የተከለከለ ቀጠና መፍጠር ቀዳሚው ነው። የዩክሬን ወደቦች መዘጋት ሌላኛው ነው። ወይም ደግሞ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ወደ ጎረቤት ቤላሩስ ማንቀሳቀስ ሊሆን ይችላል።
የሳይበር ጥቃትም ሊሰነዝሩ ይችላሉ። በጥር ወር የዩክሬን መንግስት ድረ-ገጾች ተቋርጠዋል። በየካቲት ወር አጋማሽ ደግሞ ሁለቱ የዩክሬን ትላልቅ ባንኮች ጥቃት ተሰነዘረባቸው።
ምዕራባውያንስ ምን ማድረግ ይችላሉ?
ምዕራባውያን የሩስያን እርምጃ ህገወጥ ነው ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እርምጃው የዩክሬንን ግዛት እና ሉዓላዊነት የጣሰ ነው ሲሉ አውግዘዋል።
የኔቶ አባል ሃገራት ወደ ዩክሬን ጦር የመላክ ዕቅድ እንደሌለ አስታውቀዋል። ከዚህ ይልቅ ለዩክሬን አማካሪዎችን፣ የጦር መሳሪያዎችን እና የመስክ ሆስፒታሎችን አቅርበዋል።
ስለዚህ ዋነኛውው ምላሽ ሩሲያን በእገዳዎች መቅጣት ነው፡
• ጀርመን በሩሲያ እና በአውሮፓ ኩባንያዎች ትልቅ መዋዕለ ንዋይ ፈሶበት ለተጠናቀቀው የሩሲያው ኖርድ ሰትሪም 2 ለተባለው የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ይሁኝታ መስጠቷ አቁማለች
• የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ በአማፂያኑ ቁጥጥር ስር ለሚገኙት ክልሎች ዕውቅና መስጠቷን በመቃወም ለእርምጃው ድጋፍ የሰጡ 351 የፓርላማ አባላትን ጨምሮ ሰፊ ማዕቀብ እንዲጣል ተስማምቷል።
• ዩናይትድ ኪንግደም አምስት ታላላቅ የሩሲያ ባንኮችን ላይ አነጣጥራለች
ትላልቅ ማዕቀቦች በይደር ተቀምጠዋል።
አሜሪካ የሩስያ የፋይናንስ ተቋማትን እና ቁልፍ ኢንዱስትሪዎች ላይ እያነጣጠረች ነው። የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ የፋይናንስ ገበያ ላይ አተኩሯል። ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ "በክሬምሊን እና በዙሪያው ያሉ የሚደበቁበት ቦታ አይኖራቸውም" በማለት አስጠንቅቃለች።
ዋነኛው የኢኮኖሚ ዒላማ የሩስያ የባንክ ሥርዓትን ከዓለም አቀፉ የስዊፍት የክፍያ ሥርዓት ማለያየት ነው። ይህ ግን መልሶ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኢኮኖሚ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
5 ሺህ የኔቶ ጦር አባላት በባልቲክ ግዛቶች እና በፖላንድ ተሰማርተዋል። 4,000 ጦር ደግሞ ወደ ሮማኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ሊሰማራ ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፑቲን ምን ይፈልጋሉ?
ሩሲያ ከኔቶ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደገና ለማደስ "እውነቱን አውጥታ" ተናግራለች። ሦስት ፍላጎቶቿ ደግሞ ጉልህ ናቸው።
የመጀመሪያው ኔቶ ከዚህ በላይ እንደማይስፋፋ ህጋዊ አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ ትፈልጋለች። "ዩክሬን መቼም የኔቶ አባል እንደማትሆን ማረጋገጥ ሙሉ ግዴታችን ነው" ሲሉ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ሪያብኮቭ ተናግረዋል።
ፑቲን ደግሞ ሩሲያ "ከዚህ በላይ ማፈግፈግ የምትችልበት ቦታ የላትም። ዝም ብለን የምንቀመጥ ይመስላቸዋል?" ብለዋል።
ሩሲያ እአአ በ 1994 የዩክሬን ነፃነት እና ሉዓላዊነት ለማክበር ስምምነት ተፈራረመች።
ባለፈው ዓመት ግን ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያውያንን እና ዩክሬናውያንን "አንድ ሀገር" ናቸው በማለት ዘለግ ያለ ፅሑፍ አሰፈሩ። አሁን ደግሞ ዘመናዊቷ ዩክሬን ሙሉ በሙሉ በኮሚኒስት ሩሲያ የተፈጠረች ነች ብለዋል። እአአ ታህሳስ 1991 የሶቪየት ህብረት ውድቀትን እንደ "ታሪካዊ የሩሲያ መበታተን" አድርገው ይመለከታሉ።
ዩክሬን ኔቶን ከተቀላቀለች ህብረቱ ክሬሚያን መልሶ ለመያዝ ሊሞክር ይችላል ሲሉም ፕሬዝዳንት ፑቲን ተከራክረዋል።
ሌላኛው አንኳር ጥያቄ ናቶ "በሩሲያ ድንበር አቅራቢያ የጦር መሳሪያ እንዳያሰማራ" እና ከ1997 ጀምሮ ህብረቱን ከተቀላቀሉ አባል ሃገራት ጦሩን እና ወታደራዊ መሰረተ ልማቶችን እንዲያስወግድ ነው።
ይህም መካከለኛው አውሮፓ፣ ምስራቅ አውሮፓ እና ባልቲክስ ማለት ነው። ይህ የሚያሳየው ናቶ ወደ ቅድመ 1997 ድንበሩ እንዲመለስ ሩሲያ መፈለጓን ነው።
ኔቶስ ምን አለ?
ኔቶ የመከላከያ ጥምረት ሲሆን ለአዳዲስ አባላት በሩን ክፍት የማድረግ ፖሊሲ ያለው ነው። 30ዎቹ አባል ሃገራትም በዚህ ዙሪያ ምንም ለውጥ እንደማይኖር ጽኑ አቋም አላቸው።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ኔቶን ለመቀላቀል ግልፅ የሆነ የጊዜ ገደብ እንዲኖራቸው ጥሪ ቢያቀርቡም የጀርመኑ ቻንስለር በግልፅ እንዳስቀመጡት ግን በረዥም ጊዜ ሊከሰት የሚችልበት ዕድል የለም።
በፕሬዚዳንት ፑቲን እይታ ምዕራባውያን እአአ በ1990 ናቶ "ወደ ምሥራቅ አንድ ኢንች" እንደማይሰፋ ቃል ቢገቡም አልተገበሩትም።
ይህ የተባለው ከሶቪየት ህብረት መፍረስ በፊት ነበር። በወቅቱ ለሶቪየት ህብረት ፕሬዚዳንት ሚካኤል ጎርባቾቭ የተገባው ቃል የሚያመለክተው ምሥራቅ ጀርመንን ከግምት በማስገባት እንደገና ስለተዋሃደችው ጀርመን ነው።
ጎርባቾቭ በኋላ ላይም "ስለናቶ መስፋፋት ርዕስ ጉዳይ በጭራሽ አልተነጋገረም ነበር" ብለዋል።
ዲፕሎማሳዊ መፍትሄስ ይኖራል?
ንግግሮች ቢቀጥሉም የፈረንሳይ ፑቲንና ባይደንን ለማሸማገል ያደረገችው ሙከራ ለአሁኑ የተሳካ አይመስልም።
ማንኛውም ስምምነት በምስራቅ ያለውን ጦርነት እና የጦር መሳሪያ ቁጥጥርን ያካትታል።
አሜሪካ የአጭር እና የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤሎችን በመገደብ እንዲሁም በአህጉር አቀፍ ሚሳኤሎች ላይ አዲስ ስምምነት ላይ መነጋገር መጀመር ሃሳብ አቅርባ ነበር።። ሩሲያ ደግሞ ሁሉም የአሜሪካ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ከግዛቷ ውጭ እንዳይሆኑ ትፈልጋለች።
ሩሲያ አክላም ሁለት በሩሲያ፣ ሁለት በሮማኒያ እና ፖላንድ በሚገኙ የሚሳኤል ማዕከሎች ላይ በጋራ ለመፈተሽ የተያዘው "ግልጽነት" ላይ አዎንታዊ ሃሳብ አላት።












