በምሥራቅ ባሌ ማዕድን እናወጣለን ያሉ ሰዎችን ለሞት የዳረገው አደጋ እንዴት ተከሰተ?

በቁፋሮ ላይ ያሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, East bale communication

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ባሌ ዞን፣ ጎሎልቻ ወረዳ፣ ቡላላ ካጃዋ በምትሰኝ ቀበሌ ውስጥ ማዕድን እናወጣለን ባሉ ሰዎች ላይ ባጋጠመ የመሬት መደርመስ ቢያንስ የሰባት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተነገረ።

የጎሎልቻ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሸለመ ተጫነ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አደጋው ያጋጠመው ማክሰኞ የካቲት 15/2014 ዓ.ም. ነው።

በመሬት መሸራተት አደጋው ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ የማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ መሆናቸውንም ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።

"በዚህ አካባቢ ቀደም ሲል የማዕድን ሚኒስቴር ጥናት አድርጎ ስለነበር ይህንን መሠረት አድርገው ሰዎች በቦታው ተፈላጊ 'ማዕድን አለ' ብለው ሲቆፍሩ ነበር። የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑት እነዚህ ሰዎች፣ ለዚህ ሥራ ከመንግሥት ፍቃድም ሆነ እውቅና አላገኙም ነበር" ሲሉ አቶ ሸለመ ተናግረዋል።

ማክሰኞ ዕለት በተከሰተው በዚህ አደጋ በቁፋሮ ላይ ከነበሩት ሰዎች መካከል ስድስቱ ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ አንድ ሰው ደግሞ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ ሳለ ሞቷል።

በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ በቁፋሮ ላይ ሳሉ አፈር ተደርምሶባቸው ጉዳት የደረሰባቸው 11 ሰዎች ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ጃራ እና ጊንዲር ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አደጋው የደረሰባቸው ሰዎች ማዕድን እናወጣለን ብለው ጥንቃቃቄ በጎደለው ሁኔታ ቁፋሮ ያካሂዱ እንጂ እስካሁን ድረስ ምንም ያገኙ ነገር አለመኖሩን ኃላፊው ገልጸው "በአካባቢው ማዕድን ስለመኖሩ የተረጋገጠ ነገርም የለም" ብለዋል።

አስካሁን ባለው መረጃ መሠረት በቁፋሮ ምክንያት በተከሰተው የመሬት መደርመስ የሰባት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ አስራ አንድ ሰዎች ደግሞ የተለያየ ደረጃ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሕክምና ተወስደዋል።