በቡርኪና ፋሶ የወርቅ ማዕድን ስፍራ በደረሰ ፍንዳታ የ60 ሰዎች ሕይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በደቡብ ምዕራብ ቡርኪና ፋሶ በምትገኝ መንደር የወርቅ ማዕድን ማውጫ ስፍራ በደረሰ ፍንዳታ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግሩ።
አደጋው የደረሰው በወርቅ ማዕድን ማውጫ ስፍራው በሚገኝ ገበያ ውስጥ የተከማቸ ደማሚት በእሳት ከተያያዘ በኋላ በመፈንዳቱ መሆኑን እማኞች ተናግረዋል።
አንድ የህግ ባለሙያ ለሮይተርስ እንደተናገሩት "በአካባቢው የተበታተኑ አስከሬኖች ነበሩ። ዛፎችን መንቀል እና ቤቶችን ማፍረስ የቻለ ፍንዳታ ነው።"
በፍንዳታው ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወስደዋል።
እንደ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ከሆነ ከሟቾቹ መካከል ሴቶች እና ህጻናት ይገኙበታል።
ዓቃቤ ህግ በጋኦዋ ከተማ አቅራቢያ የደረሰውን አደጋ ከጎበኘ በኋላ በሰኞው ክስተት ላይ ምርመራ ጀምሯል።
አንድ ሰው ለጥያቄ በቁጥጥር ስር ውሏል።
እንደቡርኪና ፋሶ የዜና ወኪል ኤአይቢ ከሆነ የወርቅ ማዕድን ማውጫው እንዲዘጋ ተደርጓል።
የአርቲቢ ቲቪ እንደዘገበው ፍንዳታው "ያገኘውን ሁሉ" አውድሟል።
በስፍራው ከሚገኙት የማዕድን አውጭዎች መካከል አብዛኛዎቹ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል ተፈናቅለው በስፍራው የከተሙ መሆናቸውን የአካባቢው መሪ ሳንሳን ኡርባይን ካምቡ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ቡርኪና ፋሶ ከአፍሪካ ቀዳሚ የወርቅ አምራቾች አንዷ ናት። ብዙ ማዕድን ማውጫ ስፍራዎች በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚተዳደሩ ሲሆን ኢመደበኛ የሆኑና ቁጥጥር የማይደረግባቸው ማዕድን ማዕድን ማውጫ ስፍራዎችም አሉ።
ከእአአ 2009 ጀምሮ ጥጥን በመቅደም ወርቅ ቡርኪና ፋሶ ለውጪ ገብያ የምታቀርበው ግንባር ቀደም ምርቷ ሆኗል።
እአአ በ2020 ሃገሪቱ 54 ቶን ወርቅ ያመረተች ሲሆን ይህም በ2019 ካመረተችው በ20 በመቶ ብልጫ እንዳለው የሃገሪቱ የማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከጠቅላላው ምርት ሩብ ያህሉ ህጋዊ ካልሆኑ ማዕድን አውጪዎች የተገኘ ሲሆን ይህም ለ1.5 ሚሊዮን ሕዝብ የሥራ እድል መፍጠሩን ሚኒስቴሩ ግምቱን አስቀምጧል።
ኢመደበኛ ማዕድን አውጪዎች ዘንድ የጉድጓድ ጣሪያ መደርመስን የመሳሰሉ አደጋዎች በብዙ የአፍሪካ አገራት ይከሰታሉ።
ባለፈው ወር በጎረቤት ጋና በደረሰ ከፍተኛ ፍንዳታ በትንሹ 13 ሰዎች ሞተዋል።












